የሐዋርያት ሥራ 5
5
ሐናንያና ሚስቱ ሰጲራ
1ሐናንያም የተባለ አንድ ሰው ሰጲራ ከተባለች ከሚስቱ ጋር መሬት ሸጠ፤ 2ሚስቱም ደግሞ ስታውቅ ከሽያጩ አስቀረና እኩሌታውን አምጥቶ በሐዋርያት እግር አጠገብ አኖረው። 3ጴጥሮስም “ሐናንያ ሆይ! መንፈስ ቅዱስን ታታልልና ከመሬቱ ሽያጭ ታስቀር ዘንድ ሰይጣን በልብህ ስለምን ሞላ? 4ሳትሸጠው የአንተ አልነበረምን? ከሸጥኸውስ በኋላ በሥልጣንህ አልነበረምን? ይህን ነገር ስለምን በልብህ አሰብህ? እግዚአብሔርን እንጂ ሰውን አልዋሸህም፤” አለው። 5ሐናንያም ይህን ቃል ሰምቶ ወደቀ፤ ሞተም፤ በሰሙትም ሁሉ ላይ ታላቅ ፍርሃት ሆነ። 6ጐበዞችም ተነሥተው ከፈኑት፤ አውጥተውም ቀበሩት።
7ከሦስት ሰዓት ያህል በኋላም ሚስቱ የሆነውን ሳታውቅ ገባች። 8ጴጥሮስም መልሶ “እስቲ ንገሪኝ፤ መሬታችሁን ይህን ለሚያህል ሸጣችሁትን?” አላት። እርሷም “አዎን፤ ይህን ለሚያህል ነው፤” አለች። 9ጴጥሮስም “የጌታን መንፈስ ትፈታተኑ ዘንድ ስለምን ተስማማችሁ? እነሆ፥ ባልሽን የቀበሩት ሰዎች እግር በደጅ ነው፤ አንቺንም ያወጡሻል፤” አላት። 10ያን ጊዜም በእግሩ አጠገብ ወደቀች፤ ሞተችም፤ ጐበዞችም ሲገቡ ሞታ አገኙአት፤ አውጥተውም በባሏ አጠገብ ቀበሩአት። 11በቤተ ክርስቲያን ሁሉና ይህንም በሰሙ ሁሉ ላይ ታላቅ ፍርሃት ሆነ።
በሐዋርያት እጅ የተደረጉ ተአምራትና ድንቅ ነገሮች
12በሐዋርያትም እጅ ብዙ ምልክትና ድንቅ በሕዝብ መካከል ይደረግ ነበር፤ ሁሉም በአንድ ልብ ሆነው በሰሎሞን ደጅ መመላለሻ ነበሩ። 13ከሌሎችም አንድ ስንኳ ሊተባበራቸው የሚደፍር አልነበረም፤ 14ሕዝቡ ግን ያከብሩአቸው ነበር፤ የሚያምኑትም ከፊት ይልቅ ለጌታ ይጨመሩለት ነበር፤ ወንዶችና ሴቶችም ብዙ ነበሩ። 15ስለዚህም ጴጥሮስ ሲያልፍ ጥላውም ቢሆን ከእነርሱ አንዱን ይጋርድ ዘንድ ድውያንን ወደ አደባባይ አውጥተው በአልጋና በወሰካ ያኖሩአቸው ነበር። 16ደግሞም በኢየሩሳሌም ዙሪያ ካለችው ከተማ ድውያንንና በርኩሳን መናፍስት የተሠቃዩትን እያመጡ ብዙ ሰዎች ይሰበስቡ ነበር፤ ሁሉም ይፈወሱ ነበር።
በሐዋርያት ላይ ስደት መነሣቱ
17ሊቀ ካህናቱ ግን የሰዱቃውያን ወገን ሆነውም ከእርሱ ጋር የነበሩት ሁሉ ተነሡ፤ ቅንዓትም ሞላባቸው። 18በሐዋርያትም ላይ እጃቸውን ጭነው በሕዝቡ ወኅኒ ውስጥ አኖሩአቸው። 19የጌታ መልአክ ግን በሌሊት የወኅኒውን ደጅ ከፍቶ አወጣቸውና 20“ሂዱና ቆማችሁ የዚህን ሕይወት ቃል ሁሉ ለሕዝብ በመቅደስ ንገሩ፤” አላቸው። 21በሰሙም ጊዜ ማልደው ወደ መቅደስ ገብተው አስተማሩ። ግን ሊቀ ካህናቱና ከእርሱ ጋር የነበሩት መጥተው ሸንጎውንና የእስራኤልን ልጆች ሽማግሌዎች ሁሉ በአንድነት ጠሩ፤ ያመጡአቸውም ዘንድ ወደ ወኅኒ ላኩ። 22-23ሌሎዎችም መጥተው በወኅኒው አላገኙአቸውም፤ ተመልሰውም “ወኅኒው በጣም በጥንቃቄ ተዘግቶ ጠባቂዎችም በደጁ ፊት ቆመው አገኘን፤ በከፈትን ጊዜ ግን በውስጡ አንድ ስንኳ አላገኘንም፤” አሉአቸው። 24የመቅደስ አዛዥና የካህናት አለቆችም ይህን ነገር በሰሙ ጊዜ “እንጃ ይህ ምን ይሆን?” እያሉ ስለ እነርሱ አመነቱ። 25አንድ ሰውም መጥቶ “እነሆ፥ በወኅኒ ያኖራችኋቸው ሰዎች እየቆሙ ሕዝቡንም እያስተማሩ በመቅደስ ናቸው፤” ብሎ አወራላቸው። 26በዚያን ጊዜ አዛዡ ከሎሌዎች ጋር ሄዶ አመጣቸው፤ በኃይል ግን አይደለም፤ ሕዝቡ እንዳይወግሩአቸው ይፈሩ ነበርና።
27አምጥተውም በሸንጎ አቆሙአቸው። 28#ማቴ. 27፥25።ሊቀ ካህናቱም “በዚህ ስም እንዳታስተምሩ አጥብቀን አላዘዝናችሁምን? እነሆም፥ ኢየሩሳሌምን በትምህርታችሁ ሞልታችኋል፤ የዚያንም ሰው ደም በእኛ ታመጡብን ዘንድ ታስባላችሁ፤” ብሎ ጠየቃቸው። 29ጴጥሮስና ሐዋርያትም መልሰው አሉ “ከሰው ሥልጣን ይልቅ ለእግዚአብሔር ልንታዘዝ ይገባል። 30እናንተ በእንጨት ላይ ሰቅላችሁ የገደላችሁትን ኢየሱስን የአባቶቻችን አምላክ አስነሣው፤ 31ይህን እግዚአብሔር፥ ለእስራኤል ንስሐን የኃጢአትንም ስርየት እንዲሰጥ፥ ራስም መድኃኒትም አድርጎ በቀኙ ከፍ ከፍ አደረገው። 32እኛም ለዚህ ነገር ምስክሮች ነን፤ ደግሞም እግዚአብሔር ለሚታዘዙት የሰጠው መንፈስ ቅዱስ ምስክር ነው።”
33እነርሱም ሲሰሙ በጣም ተቆጡ፤ ሊገድሉአቸውም አሰቡ። 34ነገር ግን በሕዝብ ሁሉ ዘንድ የከበረ የሕግ መምህር ገማልያል የሚሉት አንድ ፈሪሳዊ በሸንጎ ተነሥቶ ሐዋርያትን ጥቂት ፈቀቅ እንዲያደርጉአቸው አዘዘ፤ 35እንዲህም አላቸው “የእስራኤል ሰዎች ሆይ! ስለ እነዚህ ሰዎች ምን እንደምታደርጉ ለራሳችሁ ተጠንቀቁ። 36ከዚህ ወራት አስቀድሞ ቴዎዳስ ‘እኔ ታላቅ ነኝ፤’ ብሎ ተነሥቶ ነበርና፤ አራት መቶ የሚያህሉ ሰዎችም ከእርሱ ጋር ተባበሩ፤ እርሱም ጠፋ፤ የሰሙትም ሁሉ ተበተኑ፤ እንደ ምናምንም ሆኑ። 37ከዚህ በኋላ ሰዎች በተጻፉበት ዘመን የገሊላው ይሁዳ ተነሣ፤ ብዙ ሰዎችንም አሸፍቶ አስከተለ፤ እርሱም ጠፋ፤ የሰሙትም ሁሉ ተበታተኑ። 38አሁንም እላችኋለሁ ‘ከእነዚህ ሰዎች ተለዩ ተዉአቸውም፤ ይህ አሳብ ወይም ይህ ሥራ ከሰው እንደሆነ ይጠፋልና፤ 39#2መቃ. 7፥19።ከእግዚአብሔር እንደሆነ ግን ታጠፉአቸው ዘንድ አይቻላችሁም፤ በእርግጥ ከእግዚአብሔር ጋር ስትጣሉ ምናልባት እንዳትገኙ።’”
40ሰሙትም፤ ሐዋርያትንም ወደ እነርሱ ጠርተው ገረፉአቸው፤ በኢየሱስም ስም እንዳይናገሩ አዝዘው ፈቱአቸው። 41እነርሱም ስለ ስሙ ይናቁ ዘንድ የተገባቸው ሆነው ስለ ተቆጠሩ ከሸንጎው ፊት ደስ እያላቸው ወጡ፤ 42ዕለት ዕለትም በመቅደስና በቤታቸው ስለ ኢየሱስ እርሱ ክርስቶስ እንደሆነ ማስተማርንና መስበክን አይተዉም ነበር።
Currently Selected:
የሐዋርያት ሥራ 5: መቅካእኤ
Highlight
Share
Copy
Want to have your highlights saved across all your devices? Sign up or sign in