YouVersion Logo
Search Icon

2ኛ መጽሐፈ መቃብያን 8

8
የአይሁዳውያን ድል የአሳዳጆች ሞትና የቤተ መቅደሱ መንጻት ይሁዳ መቃቢስና ተቃዋሚዎቹ
1ይሁዳ መቃቢስና ጓደኞቹ በሥውር ወደ መንደሮች ገቡ፤ የአገራቸውንም ሰዎች ጠሩ፤ በአይሁዳቹ ሕግ ተጠብቀው የኖሩትን ወደ እነርሱ አምጥተው ስድስት ሺህ የሚያህሉ ሰዎችን ሰበሰቡ። 2በሁሉም አቅጣጫ የተገፉትን ሕዝቦች እንዲመለከት፥ በአረማውያኑ የተሠራው ቤተ መቅደስ ወደ ነበረበት እንዲመለስ፥ በመውደም ላይ ስላለች 3ከተማ ምሕረት እንዲያደርግ፥ በግፍ የፈሰሰ ደማቸው ለሚያሰማው ጩኸት ምሕረት እንዲሰጥ፥ 4በክፋት የተደመሰሱትን ንጹሓን ሕፃናት እንዲያስታውስና ስሙን በተሳደቡት ሰዎች ላይ መዓቱን እንዲያወርድበባቸው ለመኑት። 5ይሁዳ መቃብስ የወታደሮች አለቃ በሆነ ጊዜ የእግዚአብሔር ቁጣ ወደ ይቅርታ ስለተለወጠ፥ ለአረማውያን የማይበገር ሰው ሆነ። 6በከተሞችና በመንደሮች ላይ በድንገት አደጋ ጥሎ አቃጠላቸው፤ ምቹ ቦታዎችን ይዞ በጠላት ላይ ከፍ ያለ ጉዳት አደረሰ። 7እንደዚህ ያለውን ውጊያ የሚያደርገው ጨለማን ተገን በማድረግ በሌሊት ነበር፤ የጀግንነቱም ዝና በሁሉ ቦታ ተሰማ።
የኒቃሮንና የጐርጊያስ ዘመቻ
8ይሁዳ መቃቢስ ጥቂት በጥቂት ከፍ ከፍ እያለና ነገሩ ሁሉ ብዙ ጊዜ እየተቃናለት በመሄድ ፊሊጶስ ለቀርለሲርያና ለፊኒቆስ መስፍን (ገዥ) ለጰጠሎሜዮስ ሰለ ንጉሡ ጉዳይ እንዲረዳው ጻፈለት። 9ጰጠሎሜዮስ የጳጥርኩልን ልጅ ኒቃኖርን በደረጀ ከንጉሡ ወዳጆች ጋር የሚቆጠረውን የአይሁድን ዘር እንዲደመሰስ ከተለያዩ የዓለም አካባቢዎች ከሃያ ሺህ በማያንሱ ወታደሮች ላይ አለቃ አድርጐ ላከው። በጦር ስልት የታወቀውን ተዋጊ ሰው ጐርጊያስንም ጨመረለት። 10ኒቃኖር የሚማረኩት አይሁዳውያን ተሽጠው ንጉሡ ለሮማውያን የሚሰጠው ሁለት ሺህ መክሊት ግብር ይከፈላል ብሎ ያስብ ነበር። 11ወዲያውኑም በባሕር አጠገብ የሚገኙትን ከተሞች አይሁዳውያን ባሮችን ለመግዛት እንዲመጡ ጥሪ አደረገላቸው፤ በአንድ መክሊት ዘጠኝ ሰዎች እንደሚሸጥላቸው ተስፋ ሰጣቸው፤ ሁሉን ከሚችል አምላክ የሚመጣበትን በቀል አላሰበም ነበር። 12ኒቃኖር ወደ እርሱ እንደሚገሠግሥ ይሁዳ ሰማ፤ የጠላት ጦር መቃረቡን ለሰዎቹ አስታወቃቸው፤ 13ፈሪዎችና በእግዚአብሔር ጽድቅ ላይ እምነት የጐደላቸው ሰዎች ሸሽተው ወደ ሌላ ቦታ ሄዱ። 14ሌሎች ያላቸውን ንብረት ሁሉ ሸጡ፤ ገና ውጊያው ከመጀመሩ በፊት ክፉው ኒቃኖር የሸጣቸውን አይሁዳውያን እንዲያድናቸው እግዚአብሔርን ይለምኑ ነበር። 15የሚያድናቸውም በእነርሱ ምክንያት ሳይሆን ከአባቶቻቸው ጋር ውል በገባው መሠረትና በእነርሱ ላይ በተጠራው ቅዱስና ታላቅ ስሙ ምክንያት ነው። 16ይሁዳ መቃቢስ ስድስት ሺህ ሰዎችን ሰብስቦ እንዲህ ሲል መከራቸው፥ “በጠላቶች ፊት አትፍሩ፤ ያለ ፍትሕ የሚወጉንን የአረማውያን ታላቅ ጦር በማየት ሐሳብ አይግባችሁ፤ በጀግንነት ተዋጉ፤ 17በቅዱሱ ቦታ ላይ የፈጸሙትን የዓመፅ ሥራ በከተማይቱ ላይ ያደረጉትን የማይገባ ተግባርና ውርደት፥ የአባቶችን ባህል መጥፋትም ተመልከቱ፤ 18እነርሱ በጦር መሣሪያዎቻቸውና በድፍረታቸው ይመካሉ፤ እኛ ግን ተስፋችን (እምነታችን) ሁሉን በሚችል እግዚአብሔር ላይ ነው፤ እርሱ በሚሰጠው በእራሱ ምልክት ብቻ ወደ እኛ የሚመጡትንና ከእነርሱም ጋር መላውን ዓለም መገልበጥ የሚችል ነው”። 19እንዲሁም ለቀድሞ አባቶቻቸው የተደረገላቸውን ድጋፍ ቆጠረላቸው። “በሰናክሬም ጊዜ መቶ ሰማንያ አምስት ሺህ ሰዎች ተደመሰሱ። 20በባቢሎን አገር በገላትያ ሰዎች ላይ በተደረገው ጦርነት ላይ ተካፋዮች የነበሩ ሰዎች ቁጥራቸው በአራት ሺህ መቄዶያናውያን ሌላ ስምንት ሺህ አይሁዳውያን ነበሩ፤ የመቄዶንያ ሰዎች ጦር ወደ ኋላ ባለ ጊዜ ስምንቱ ሺህ አይሁዳውያን መቶ ሃያ ሺህ ጠላቶች ደምስሰዋል፤ ይህንን ማድረግ የቻሉት ከእግዚአብሐር በተደረገላቸው እርዳታ ነው፤ ብዙ ምርኮም አግኝተዋል”። 21በቃሉ ካደፋፈራቸውና ስለ ሕጋቸውና ስለ ሀገራቸው እንዲሞቱ ካዘጋጃቸው በኋላ ጦሩን በአራት ክፍል ከፋፈለው፤ 22ለእያንዳንዱ ክፍል ወንድሞቹን ስምዖንን፥ ዮሴፍን፥ ዮናታንን መሪዎች አደረጋቸው፤ እያንዳንዳቸው አንድ ሺህ አምስት መቶ ሰዎችን እንዲያዝዙ አደረገ። 23አልዓዛር ቅዱሱን መጽሐፍ በከፍተኛ ድምፅ እንዲያነብ ካዘዘ በኋላ ለወታደሮቹ “የእግዚአብሔር እርዳታ” የሚል መፈክር ሰጣቸውና እሱ የመጀሪያው ጦር ሠራዊት መሪ ሆኖ ከኒቃኖር ጋር ጦርነት ገጠመ። 24ሁሉን የሚችል አምላክ ረዳታቸው ሆኖ ከዘጠኝ ሺህ በላይ ጠላቶች ገደሉ፤ የኒቃኖርን ወታደሮች አብዛኖቹን አቆሰሉ፥ ቆራረጡዋቸው፥ ሁሉንም አባረሪቸው። 25እንደ ባሮች ሊገዟቸው ከመጡት ሰዎችም ላይ ብሩን ወሰዱባቸው፤ 26ሰዎቹን ወደ ሩቅ ካባረሩዋቸው በኋላ የሰንበት ዋዜማ ስለሆነና ጊዜውም ስላልፈቀደላቸው ወደ ኋላ ተመለሱ፤ ስለዚህ እነርሱን ማበረራቸውን አልቀጠሉም፤ 27የጠላቶችን መሣሪያዎች ከሰበሰቡና ምርኮአቸውንም ከወሰዱ በኋላ የምሕረቱ መጀመሪያ ቀን በሆነው በዚህ ቀን ስለጠበቃቸው እግዚአብሔርን ብዙ እያመሰገኑና እያወደሱ የሰንበትን ቀን ያከብሩ ጀመር። 28ከሰንበት ቀን በኋላ ከምርኮ ያገኙትን ከፍለው በስደት ለተጐዱ ሰዎች፥ ባሎቻቸው ለሞቱባቸው ሴቶች፥ ለሙት ልጆች አከፋፈሉ፥ የቀረውን እነርሱ ከልጆቻቸው ተከፋፈሉት። 29ምርኮውን እንዲህ ካከፋፈሉ በኋላ የኀብረት ጸሎት አደረጉ፤ መሐሪው እግዚአብሔር አገልግጋዮቹን ለዘወትር እንዲታረቃቸው ለመኑት።
የጢሞቴዎስ እና የባቂደስ መሸነፍ
30ከጢሞቴዎስና ከባቂደስ ወታደሮች ጋር ተዋግተው ከሃያ ሺህ የሚበዙ ሰዎችን ገደሉ፤ ረዣዥም ምሽጐችንም ያዙ፤ የማረኩትንም ብዙ ምርኮ በሁለት ከፍለው ግማሹን እነርሱ ወሰዱት፤ የቀረውን ግማሽ ለስደተኞች፤ ለሙት ልጆች፥ ለመበለቶችና ለሸማግሌዎች አከፋፈሉ። 31ከጠላቶች የተገኘውን የጦር መሣሪያ ሁሉ በጥንቃቄ ለቃቅመው በልዩ ቦታዎች አስቀመጧቸው፤ የቀረውን ምርኮ ግን ወደ ኢየሩሳሌም አመጡ። 32በአይሁዳውያን ላይ ብዙ ግፍ የሠራውን፥ ከጢሞቴዎስ ጋር የነበረውን እና እጅግ ክፉ ሰው የሆነውን የጎሣ አለቃ ገደሉት። 33በሀገራቸው የድል በዓልን በሚያከበሩበት ጊዜ የተቀደሱ መዝጊያዎችን ያቀጠሉና ከካልሲስቴናውያን ጋር በአንዲት ቤት ተሸሽገው የነበሩበትን ሰዎች በእሳት አቃጠሏቸው፤ በዚህ ዓይነት የተገባ የክፋት ዋጋቸውን አገኙ።
የኒቃኖር ፍርጠጣና ምስክርነት
34ባለ ሦስት ቀለማቱ ሸፈጠኛ የነበረው አይሁዳውያንን እንደ ባሮች የሚገዙ አንድ ሺህ ነጋዴዎችን ያመጣ፤ ኒቃኖር የማይረቡ ብሎ የገመታቸው በነበሩ ሰዎችና 35በእግዚአብሔር እርዳታ ሊያዋርዳቸው ፈልጐ በነበሩት ሰዎች ተዋረደ። የክብር ልብሱን አውጥቶ ጥሎ እንዳመለጠ ባርያ ወደ ሜዳ ሸሸ። ብቻውን ተጥሎ እንደ ምንም ብሎ ወደ አንጾኪያ ደረሰ፤ ጦር ሠራዊቱም ተደመሰሰ። 36የኢየሩሳሌምን ምርኮኞች ሽያጭ ግብር እሰጣችኋለሁ ብሎ ለሮማውያን ተስፋ ሰጥቶ የነበረው ሰው አይሁዳውያን ተከላካይ እንዳላቸው አመነ፤ ይህ የሚከላከልላቸው “አምላክ” የሰጣቸውን ሕግ በመከተላቸው ምክንያት አይሁዳውያን የማይበገሩ መሆናቸውን ተረዳ።

Highlight

Share

Copy

None

Want to have your highlights saved across all your devices? Sign up or sign in