YouVersion Logo
Search Icon

2ኛ መጽሐፈ መቃብያን 2

2
ኤርምያስ ድንኳኑን፤ ታቦቱን፤ መሠዊያውን ደበቀ
1ነቢዩ ኤርምያስ ተማርከው የሚሄዱትን ሰዎች ከላይ እንደተመለከተው እሳት ይዘው እንዲሄዱ ያዘዛቸው መሆኑ በመጽሐፍ ይገኛል፤ 2እንዲሁም ነቢዩ የእግዚአብሔርን ሕግ ከሰጣቸው በኋላ የእግዚአብሔርን ትእዛዝ እንዳይረሱ የወርቅና የብር ምስሎችን የለበሱትንም ጌጣጌጥ በማየት ልባቸው ከእግዚአብሔር እንዳይርቅ አደራ ብሏቸዋል። 3ይህንኑ ዓይነት ምክር ከሰጣቸው በኋላ የእግዚአብሔርን ሕግ ከልባቸው እንዳያርቁ መክሯቸዋል። 4ነቢዩ እግዚአብሔር በነገረው መሠረት ድንኳኑንና ታቦቱን ይዞ ሙሴ ወደ ወጣበትና እዚያ ሆኖ የእግዚአብብሔርን ርስት ወደ ተመለከተበት ተራራ ላይ መውጣቱ በዚሁ መጽሐፍ ውስጥ ተነግሮአል፤ 5ኤርምያስ እዚያ ከደረሰ በኋላ የዋሻ ቤት አግኝቶ ድንኳኑንና ታቦቱን፥ የዕጣን መሠዊያውንም እዚያ አስቀመጠ። ከዚህ በኋላ መግቢያውን ጥርቅም አድርጐ ዘጋ። 6ከጓደኞቹ አንዳንዶቹ እርሱ በሄደበት ሄደው መንገዱን ምልክት ሊያደርጉበት ፈለጉ ግን ሊያገኙት አልቻሉም። 7ኤርምያስ ይህን በሰማ ጊዜ ገሠጻቸው፤ እንዲህም አላቸው፤ “እግዚአብሔር ሕዝቡን እስኪሰበስብና ምሕረቱን እስኪያሳያቸው ድረስ ይህ ቦታ ሥውር ሆኖ ይቆያል። 8በዚያን ጊዜ እግዚአብሔር እነዚህን ዕቃዎች ገልጾ ያሳያል፤ በሙሴ ጊዜና ሰሎሞን ቤተ መቅደሱ በክብር እንደቀደስ በጸለየ ጊዜ እንደታየው ዓይነት የእግዚአብሔር ክብርም ከደመናው ጋር ይታያል”። 9ሰሎሞን ጥበበኛ ሆኖ ቤተ መቅደሱ ሲቀደስ በጥበብ መሥዋዕቱን እንዴት እንደቀረበና የቤተ መቅደሱም ሥራ እንዴት እንደ ተፈጸመ ተነግሮአል። 10ሙሴ ወደ እግዚአብሔር በጸለየ ጊዜ እሳት ከሰማይ ወርዶ መሥዋዕቱን እንዳቃጠለ እንዲሁም ሰሎሞን ጸልዮ ከሰማይ የወረደው እሳት መሥዋዕቱን አቃጠለው። 11“በኃጢአት ምክንያት የሚቀርበው መሥዋዕት ስላልተበላ በእሳት ተቃጥሎ አለቀ” ብሎ ሙሴ ተናግሮ ነበር፤ 12እንዲሁ ሰሎሞንም ስምንት ቀን በዓል አደረገ።
የነህምያ ቤተ መጻሕፍት
13በዚሁ መጽሐፍና ነህምያ በጻፋቸው ማስታወሻዎች እነዚህ ነገሮች ተነግረዋል፤ ነህምያ ቤተ መጻሕፍት አቋቁሞ ስለ ነገሥታትና ስለ ነቢያት የሚናገሩትን መጻሕፍት፤ የዳዊትን መጻሕፍትንና ስለ መሥዋዕቶች የሚናገሩትን የነገሠታት ደብዳቤናዎች እዚያ መሰብሰቡ ተነግሮአል። 14እንዲሁም ይሁዳ በተደረገብን ጦርነት ምክንያት የተበታተኑትን መጻሕፍት ሁሉ ሰብስቧል፤ በእጃችን ይገኛሉ። 15የሚያስፈልጋችሁ ከሆነ የሚያመጡላችሁን ሰዎች ወደ እኛ ላኩ።
የተሐድሶን በዓል ለመካፈል የቀረበ ጥሪ
16ይህን ደብዳቤ የጻፍንላችሁ የቤተ መቅደሱን መንጻት በምናከብርበተ ጊዜ ነው፤ እናንተም እነዚህን ቀኖች ብታከብሩ መልካም ነው። 17ሕዝቡን የዳነና ለሁሉም ርስትን፤ መንግሥትን፤ ክህነትን፥ ቅድስናን የሰጠ አምላክ፤ 18እርሱ በኦሪት ሕግ ተስፋ ሰጥቶን እንደ ነበር ተስፋ የጣልንበትን ይህ አምላክ ይራራልናል፤ ከሰማይ በታች ካሉ አገሮች ወደተቀደሰው ቦታ ይሰበስበናል፤ ምክንያቱም እርሱ ከታላላቅ ጭንቆች አውጥቶናል። ቅዱሱንም ቦታ (ቤተ መቅደሱንም) አንጽቷል።
የአዘጋጁ መቅድም
19ስለ ይሁዳ መቃቢስና ወንድሞቹ፤ ስለ ታላቁ ቤተ መቅደስ፥ ሰለ መሠዊያው መቅደስ፤ 20እንዲሁም በአንጥዮኩስ ኤጲፋኔስና በልጁ በኤውጳጥሮስ ላይ ስለተደረጉት ጦርነቶች፤ 21ስለ አይሁድ ሕዝብ በጀግንነት ለተዋጉት ምንም እንኳን ቁጥራቸው ጥቂት ቢሆንም፤ አገሩን ሁሉ ዘርፈው አረመኔውን ሕዝብ ላባረሩ ሰዎች ስለታያቸው ብርሃንና፤ 22በመላው ዓለም የታወቀውን ቤተ መቅደስ ያስመለሱትን፤ ከተማዋን ነጻ ያወጡ እግዚአብሔር በታላቅ ምሕረቱ ራርቶላቸው ለመደምሰስ የቀረቡትን ሕጐች መልሰው ያቋቋሙ ስለእነርሱና፤ 23ቀሬናዊው ኢያሱ በአምስት መጻሕፍት ውስጥ ስለጻፋቸው ስለ እነዚህ ነገሮች ሁሉ አሳጥረን ባንድ መጽሐፍ ለማጠቃለል እንሞክራለን። 24የቁጥሩን ብዛትና ታሪኩን ለማወቅ በሚፈልጉ ሰዎች ላይ ከነገሩ ብዛት የተነሣ የሚወድቀውን ችግር በማሰብ፤ 25ሊያነቡት የሚፈልጉትን ሰዎች እንዲያስደስታቸው፤ የሚማሩት ሰዎች በቀላሉ እንዲያጠኑት፤ ለሚያነቡትም ሁሉ ጥቅም እንዲሰጣቸው በማለት ተጋንበት። 26ባጭሩ ለመጻፍ አሰቸጋሪውን ሥራ ለተቀበልነው ለእኛ ቀላል ነገር አይደለም፤ ላብ ማንጠፍጠፈንና ታላቅ ትጋትን (እንቅልፍ ማጣትን) የሚጠይቅ ጉዳይ ነው። 27ይህ አስቸጋሪ ሥራ ሰዎችን ለማገልገል ብለን ይህን ከባድ ሥራ ወደን ተቀብለናል፤ 28ነገሮቹን ሁሉ ተጠንቅቆና አሳምሮ ለጻፈው ለመጀመሪያው ጸሐፊ ትተን እኛ በአጠቃላይ በአጭሩ ለመጻፍ እንሞክራለን። 29የአዲስ ሕንፃ ሥራ በሙሉ ዋናውን አናጺ እንደሚመለከትና ቀለም ቀቢው ሕንጻውን ለማስጌጥ የሚያስፈልገውን ነገር ሁሉ መሰብሰብ እንደሚያሻው የእኛም ሥራ እንዲሁ ዓይነት ይመስለኛል። 30በጉዳዩ ጠልቆ መግባት፤ ዙሪያውን መመልከት፤ እያንዳንዱን ሥራ በጥንቃቄ መመርመር የታሪኩን ጸሐፊ የሚመለከት ነው። 31ነገር ግን ነገሩን ሳያስፋፋ ባጭሩ መግለጽ የሚመለከተው ጸሐፊውን ነው። 32አሁን እንግዲህ እስካሁን ከተባለው ይበልጥ ምንም ሳንጨምር ታሪኩን እንጀምራለን፤ ምንያቱም መቅድሙን አስፍቶ ማብራራት ፋይዳ የሌለው ከመሆኑም በላይ ታሪኩን እራሱን ያሳጥረዋል።

Highlight

Share

Copy

None

Want to have your highlights saved across all your devices? Sign up or sign in