YouVersion Logo
Search Icon

2ኛ መጽሐፈ መቃብያን 1

1
ሁለተኛ መቃብያን በግብጽ ላሉ አይሁዳውያን የተጻፈ ደብዳቤ የመጀመሪያው ደብዳቤ
1የኢየሩሳሌም አይሁዳውያን፤ ወንድሞቻቸውና በአይሁድ አገር የሚገኙ ሰዎች፥ በግብጽ አገር ለሚገኙ አይሁዳውያን ወንድሞቻቸው ሰላምታ ያቀርባሉ፤ ሰላምና ብልጽግና ይመኙላቸዋል። 2እግዚአብሔር መልካሙን ነገር ያድርግላችሁ፤ ከታማኝ አገልጋዮቹ ከአብርሃም፤ ከይስሐቅና ከያዕቆብ ጋር ያደረገውን ቃል ኪዳን ያስታውስ። 3እርሱን የምታመልኩበትንና በለጋስነት፥ በመልካም ፈቃድ የእርሱን ፈቃድ የምትፈጽሙበትን ልብ ለሁላችሁም ይስጥ። 4ለእርሱ ሕግና ትዕዛዞች ልባችሁ እንዲከፈት ያድርግላችሁ፤ ሰላምም ያድርግላችሁ። 5ጸሎታችሁን ሰምቶ ይታረቃችሁ፤ በመከራ ጊዜ አይተዋችሁ፤ 6በዚህ ጊዜ ከእርሱ የምንለምንላችሁ ይህንኑ ነው። 7በዲሜጥሮስ መንግሥት ጊዜ እኛ አይሁዳውያን በመቶ ስልሳ ዘጠኝ ዓመተ ዓለም እንዲህ ስንል ጽፈንላችኋል፤ “በእነዚያ ዓመታት ኢያሶንና የእርሱ ሰዎች ከቅድስት ምድር ከመንግሥት ተለይተው ከከዱበት ጊዜ ጀምሮ በወደቀብን መከራና ስደት ዘመን፤ 8የቤተ መቅደሱን ታላቅ መዝጊያ እስከ ማቃጠልና ንጹሕ ደም እስከ ማፍሰስ ደርሰዋል፤ መሥዋዕትና የስንዴ ዱቄት አቅርበናል፤ መብራት አብርተናል፤ ኀብስትም አስቀምጠናል”። 9አሁንም የምንጽፍላችሁ በከሴሎ ወር የሚውለውን የቂጣ (የድንኳን) በዓል እንድታከብሩ ነው። 10በመቶ ሰማንያ ስምንት ዓመተ ዓለም ተጻፈ። ሁለተኛው ደብዳቤ በኢየሩሳሌምና በይሁዳ አገር የሚገኙ ሰዎች፤ የይሁዳ ምክር ቤትና የይሁዳ ንጉሥ ጰጠሎሜዎስ አማካሪ፤ ከተቀቡት የካህናት ዘር ወገን ለሆነው ለአርስጦብሎስና በግብጽ አገር ለሚገኙ አይሁዳውያን ሰላምና ጤና ይሁን።
አንጥዮኩስ በመቀጣቱ የቀረበ ምስጋና
11እኛ በአምላክ ቸርነት ከታላላቅ አደጋዎች የዳንን ከንጉሡ ጋር ባደረግነው ውጊያ ለረዳን አምላክ ትልቅ ምስጋና እናቀርባለን፤ 12ምክንያቱም የጦር መሣሪያ ይዘው በቅድስት ከተማ ላይ የመጡትን እርሱ ራሱ አባሮልናል። 13መሪያቸው የማይበገር ይመስል ከነበረው ከብዙ ሠራዊቱ ጋር ወደ ፋርስ ሄደ፤ እርሱም፥ ሠራዊቱም የጣዖቷ የናንያ ካህናት በተንኮል ባጠመዱባቸው ወጥመድ ውስጥ ገብተው በጣዖቷ በናንያ ቤት ውስጥ ተጨፈጨፉ፤ 14አንጥዮኩስ ወዳጆቹን አስከትሎ ጣዖቷን ሚስት ለማድረግ ያሰበ መስሎ የጣዖቷን ከፍተኛ ሀብት በጥሎሽ መልክ ለመውሰድ ወደ እዚያ ቦታ ሄደ፤ 15የናንያ ካህናት ወርቁንና ብሩን አወጡና አሳዩት፤ ንጉሡም አንዳንድ አጃቢዎች አስከትሎ ወደ ጣዖቷ ቤት ውስጥ ገባ፤ እነርሱ ግን አንጥዮኩስ ወደ ጣዖቷ ቤት እንደ ገባ ወዲያውኑ በሩን ዘጉ። 16በጣሪያው በኩል ያለውን የምሥጢር (ሥውር) በር ከፍተው ድንጋይ እየወረወሩ ሹሙን ቀጠቀጡት፤ ሰውነቱንና ራሱንም ቆራርጠው በውጭ ወዳሉት ሰዎች ጣሉባቸው። 17ቅዱስ ነገርን ያረከሱ ሰዎችን ለሞት አሳልፎ የሰጠ አምላካችን በሁሉ ነገር የተመሰገነ ይሁን።
የተቀደሰው እሳት ተጠብቆ የቆየበት ተአምር
18በኬሰሎ ወር በሃያ አምስተኛው ቀን የቤተ መቅደሱን መንጻት በዓል ስለምናከብር ነህምያ ቤተ መቅደሱንና መሠዊያውን ሠርቶ መሥዋዕትን ባቀረበ ጊዜ እንደታየው እሳትና እንደ ቂጣ (ድንኳን) በዓል ዓይነት እናንተም በዓሉን እንድታከብሩ ለእናንተ ማስታወቅ የተገባ ሆኖ ታየን። 19ምክንያቱም አባቶቻችን ተማርከው ወደ ፋርስ በተወሰዱ ጊዜ በዚያን ጊዜ የነበሩ እግዚአብሔርን የሚፈሩ ካህናት ከመሠዊያው እሳት ወስደው ውሃ በሌለበት ደረቅ ጉድጓድ በሚመስለው ቀዳዳ ውስጥ በስውር ደበቁት፤ ማንም ሳያውቀው እዚያ እንዲቀመጥ አደረጉት። 20ብዙ ዓመታት ካለፉ በኋላ እግዚአብሔር በፈቀደ ጊዜ ነህምያ በፋርስ ንጉሥ ተልኮ እነዚያ እሳቱን ደብቀውት የነበሩ ካህናት የልጅ ልጆቻቸው እንዲፈልጉት አዘዛቸው፤ ግን ያገኙት እሳት ሳይሆን የረጋ ውሃ መሆኑን ተናገሩ፤ እሱም ለምርመራ ቀድተው እንዲያመጡ አዘዛቸው። 21መሥዋዕት ለማቅረብ ሁሉ ነገር በተዘጋጀ ጊዜ ነህምያ በእንጨትና በቀረቡት መሥዋዕቶች ላይ ካህናቶቹ ይህን ፈሳሽ እንዲረጩ አዘዛቸው። 22ይህን ባደረጉ ጊዜ ከጥቂት ጊዜ በኋላ በደመና ተሸፍና የነበረችው ፀሐይ ወጣችና አበራች፤ ሁሉም እስኪደነቁ አንድ ትልቅ እሳት ነደደ። 23እሳቱ መሥዋዕቱን በሚያቃጥልበት ጊዜ ካህናት ይጸልዩ ነበር፤ ከካህናቱ ጋር እዚያ የነበሩት ሁሉ፥ ዮናታን እያቀነቀነ፥ ሎሎቹ ከነህምያ ጋር ሆነው እየመለሱ ይዘምሩ ነበር። 24ጸሎቱም እንዲህ ይል ነበር፥ “ጌታ እግዚአብሔር አምላካችን የሁሉ ነገር ፈጣሪ፤ አስፈሪ፥ ኃያል፥ ጻድቅ፥ መሐሪ፥ አንተ ብቻ ንጉሥ ነህ፤ አንተ ብቻ ደግ ነህ፤ 25አንተ ብቻ ለጋስ፥ አንተ ብቻ ጻድቅ፥ ሁሉን የምትችልና ዘላለማዊ እስራኤልን ከክፉ ሁሉ የምታድን፥ አባቶቻችን ለአንተ የተመረጡ እንዲሆኑ ያደረግሃቸውና የቀደስሃቸው፥ 26ስለ እስራኤል ሕዝብ ሁሉ ይህን መሥዋዕት ተቀበል፤ ርስትህን ጠብቀው፤ ቀድሰውም። 27ከመካከላችን ርቀውና ተበታትነው የሚገኙትን ሰብስባቸው፥ በአረማውያን መካከል በባርነት የሚገኙትን ነጻ አውጣቸው፤ አንተ የእኛ አምላክ መሆንህን አረማውያን እንዲያውቁ የተናቁትንና የተጣሉትን በመልካም ዐይን ተመልከታቸው፥ 28የሚጨቁኑንንና በትዕቢት የሚበድሉንን ቅጣቸው፤ 29ሙሴ እንዳለው ሕዝብህንም በቅዱስ ሀገር ላይ ትከለው።”
30ካህናቱ ይከምሩ ነበር፤ 31መሥዋዕት ተቃጥሎ ባለቀ ጊዜ የተረፈውን ውሃ በታላላቅ ድንጋዮች ላይ እንዲያፈሱ ነህምያ አዘዘ፤ 32ይህ በተደረገ ጊዜ ነበለባል ነደደ፤ ግን ከመሠዊያው የሚወጣው ብርሃን ዋጠው። 33ነገሩ በታወቀ ጊዜና ተማርከው የተወሰዱ ካህናት እሳት በደበቁበት ቦታ ነህምያና ጓደኞቹ መሥዋዕት የተቀደሱበት ውሃ መገኘቱን ለፋርስ ንጉሥ በነገሩት ጊዜ፤ 34ንጉሡ ይህን ቦታ አሳጠረና ነገሩን ካረጋገጠ በኋላ ቅዱስ ቦታ አደረገው። 35ንጉሡ ለፈቀደላቸው ሰዎች ከዚያ ከሚገኘው ግቢ ብዙ ስጦታዎች ይሰጣቸው ነበር። 36ነህምያና ከእርሱ ጋር ያሉት ሰዎች ይህን ውሃ ኔፍታር ብለው ጠሩት፤ ትርጉሙ “ንጽሕና” ማለት ነው፤ ብዙ ሰዎች ግን “ናፍታ” ይሉታል።

Highlight

Share

Copy

None

Want to have your highlights saved across all your devices? Sign up or sign in