2ኛ መጽሐፈ መቃብያን 14
14
ከዲሜጥሮስ የጦር አዛዥ ከዚቃኖር ጋር የተደረገ ግጭት
የኒቃኖር ቀን
የሊቀ ካህኑ አልቂሞስ ጣልቃ መግባት
1ከአምስት ዓመት በኋላ የሰላውቂስ ልጅ ዲሜጥሮስ ከብዙ ወታደሮችና መርከቦች ጋር ወደ ትሪፖሊ ጠረፍ መድረሱንና 2አገሩንም ይዞ አንጥዮኩስንና መምህሩን ሊስያስን መግደሉን ይሁዳና የእርሱ ሰዎች ሰሙ። 3አንድ አልኒቀውስ የተባለ ሰው በፊት ሊቀ ካህናት ሆኖ የነበረ፥ በግርግሩ ጊዜ በፈቃዱ የረከሰ፥ በምንም ዓይነት ደኀንነት እንደማይኖረው አውቆ፥ ከእንግዲህ ወዲህ ወደተቀደሰው መሠዊያው መቅረብ እንደማይችል ተረድቶ 4ወደ 151 ዓመተ ዓለም ገደማ ወደ ንጉሥ ዲሜጥሮስ ሄደና የወርቅ አክሊል ከዘንባባ ጋር አቀረበለት፤ ከዚህም በላይ በቤተ መቅደስ እንደተለመደው የወይራ ዝንጣፊ አቀረበለትና በዚያን ቀን ምንም ሳይናገር ዝም ብሎ ዋለ።
5ዲሜጥሮስ ወደ ምክር ቤቱ ጠርቶት የአይሁዳውያንን ሁናቴና ሐሳብ በጠየቀው ጊዜ የማይጨበጠውን እቅዱን ለመግለጽ ጊዜ አገኘ፤ እንዲህም ሲል መለሰ፥ 6“ይሁዳ መቃቢስ የሚመራቸው አሲዳውያን የሚባሉ አይሁዳውያን ጦርነትና ሁከትን ያነሣሣሉ፤ መንግሥት በጸጥታ እንዲኖር አይተውም። 7ስለዚህ ከአባቶች የወረስኩትን የሊቀ ካህናትነት ክብሬን ተገፍፌ ወደዚህ መጣሁ፤ 8ወደዚህ የመጣሁበትም በመጀመሪያ በእውነት ለንጉሥ የሚያስፈልጉትን ገነሮች በማሰብ ቀጥሎም እነዚያ ክፉ ሰዎች ሕዝባችን በታላቅ ችግር ውስጥ ስለ ጨመሩት ሰለ ሕዘቤ በማሰብ ነው። 9ስለዚህ አንተ ንጉሥ ሆይ እያንዳንዱን ነገር ባወቅህ ጊዜ እባክህ ስለ ሀገራችን ስለ ተቸገረው ሕዝባችን ለሁሉም በምታደርገው በተወደደው ደግነትህ አስብ፤ 10ምክንያቱም ይሁዳ በሕይወት እስካለ ድረስ መንግሥትህ ሰላምን ማግኘት አይችልም።”
11ንግግሩን ባቆመ ጊዜ ወዲያውኑ ሌሎቹ የንጉሡ ወዳጆች የይሁዳን ሥራ በማጥላላት ንጉሡን ዲሜጥሮስን ለማነሣሣት ተጣደፉ። 12ወዲያውኑ የዝሆኖች አለቃ የነበረው ኒቃኖርን ጠርቶ የይሁዳ ምድር ገዥ አደረገውና ላከው፤ 13ይሁዳን እንዲያጠፋና ከእርሱ ጋር ያሉትን እንዲበታትን አለቂሞስንም የታላቁ ቤተ መቅደስ ሊቀ ካህናት አድርጐ እንዲሾመው አዘዘ። 14ከይሁዳ ሸሽተው የነበሩ የይሁዳ ምድር አረማውያንም ከኒቃኖር ወታደሮች ጋር ተደባለቁ (አብረው ሆኑ)፤ የአይሁዳውያን ጭንቅና መከራ ለእነርሱ የሚበጅ ነው ብለውም አስበው ነው።
ኒቃኖር የይሁዳ ወዳጅ ሆነ
15አይሁዳውያን የኒቃኖርን መቃረብና የአረማውያንን አብረው መምጣት በሰሙ ጊዜ በራሳቸው ላይ አመድ ነስንሰው ሕዘቡን ለዘወትር ያኖረና በሚታዩ ተአምራተ ርስቱን ለመርዳት የማያቋርጠውን አምላክ ይለምኑ ጀመር። 16በአለቃቸው ትእዛዝ መሠረት ከነበሩበት ቦታ በቶሎ ሄዱና በዴሳው መንደር አጠገብ ከጠላት ጋር ጦርነት ገጠሙ። 17የይሁዳ ወንድም ስምዖን ከኒቃኖር ጋር ጦርነት ገጥሞ ነበር፤ ግን ጠላቶች በድንገት በመምጣታቸው ጥቂት እንደ መረበሽ አለ። 18ሆኖም ኒቃኖር የይሁዳ ወታደሮች ብርታት ምን መሆኑን፥ ስለ ሀገራቸው ሊዋጉ ያላቸውን ድፍረት ስላወቀ ነገሩ በደም መፋሰስ ይፈታል የሚል ግምት አልነበረውም። 19ስለዚህ የሰላም እጁን ለአይሁዳውያን ለመዘርጋትና እነርሱም እንዲጨብጡ ብሎ ጶሊየንን፥ ቴዎዱትንና ማታትያስን ላከባቸው።
20ስለዚህ በቀረቡት ሐሳቦች ላይ ብዙ ውይይት ከተደረገ በኋላ የጦር መሪው ለወታደሮቹ አስታወቀ፤ በጉዳዩ ስለተስማሙ ውሉን ለመቀበል እሺ ማለታቸውን ገለጹ። 21የጦር አለለቆች በተለይ የሚገናኙበት አንድ ቀን ወሰኑ፤ ከዚህም ከዚያም መቀመጫ ተሰጠ፤ የክብር ወንበሮችም ተዘጋጁ። 22ይሁዳ ምናልባት በድንገት ከጠላት በኩል ክፉ ነገር ቢመጣ የሚደርሱ የጦር መሣሪያ የታጠቁ ሰዎች በምቹ ቦታዎች አዘጋጅቶ ነበር፤ ግን ንግግሩ በመልካም ተፈጸመ። 23ኒቃኖር ምንም ክፉ ነገር ሳያደርግ በኢየሩሳሌም ሰነበተ፤ በእርሱ ዙሪያ ተሰብስበው የነበሩትንም አረማውያን አሰናበተ። 24ለይሁዳ ልቡን ሰጥቶ ከእርሱ ምንም አልተለየም። 25ሚስት እንዲያገባና ልጆች እንዲወልድ ይሁዳን ለመነው፤ ሚስት አገባ፤ ተገቢውን ሕይወት ለመምራት ተደላድሎ ተቀመጠ።
ኒቃኖር በቤተመቀደሱ ላይ የሰነዘረው ዛቻ
26ነገር ግን አልቂሞስ መስማማታቸውን አይቶ፥ የውላቸውን ጽሑፍ ይዞ ወደ ዲመትሪዮስ መጣና ኒቃኖር ይሁዳን ወራሹ አድርጐ በመንግሥት ላይ ተቃውሞ አድርጓል ሲል ነገረው።
27ንጉሡ ተቆጣ፤ በዚህ በክፉ ሰው ምክንያት ተቆጥቶ፥ በስምምነቱነ ያልተደሰተ መሆኑን ገልጾ ይሁዳ መቃቢስን አስሮ በቶሎ ወደ አንጾኪያ እንዲልከው ትእዛዙን ለኒቃኖር ጻፈለት።
28ይህን በሰማ ጊዜ ኒቃኖር ደገነጠ፤ ምንም በደል በሌለበት ሰው ላይ እንዴት ውል ማፍረስ ይቻላል ሲል ተበሳጨ። 29ነገር ግን ንጉሡን መቃወም ሰለማይቻል ይህን ትእዛዝ ለመፈጸም ምቹ አጋጣሚ ጊዜ በጥበብ ይፈልግ ነበር። 30ይሁዳ መቃቢስም በበኩሉ ከኒቃኖር ጋር ያለው ግንኙነት እየቀዘቀዘ መሄድንና ሲገናኘውም ቁጣ ቁጣ የሚለውም መሆኑን በመገንዘብ ይህ ነገር መልካም አለመሆኑን አሰበ። ስለዚህ ከሰዎቹ ብዙዎቹን ሰበሰበና ይዞ ከኒቃኖር ተሠወረ። 31ኒቃኖር ይህ ሰው በብልጠት እንደረታው አውቆ ካህናት የተለመደውን መሥዋዕት በሚያቀርቡበት ጊዜ ወደ ታላቁና ቅዱስ ቤተ መቅደስ ሄዶ ሰውዬውን አሳልፈው እንዲሰጡት አዘዘ። 32የምትፈልገው ሰው የት መሆኑን አናውቅም ብለው በመሐላ በነገሩ ጊዜ 33ኒቃኖር ቀኝ እጁን ወደ ቤተ መቅደሱ ዘርግቶ እንዲህ ሲል በመሐለ ተናገረ፥ “ይሁዳን አስራችሁ ካልሰጣችሁኝ ይህን የእግዚአብሔር ቤተ መቅደስ ደምስሸ ሜዳ አደርገዋለሁ፤ መሠዊያውንም አፈርሰዋለሁ፤ በዚህ ቦታ ላይ ለዲዩናስዩስ ያማረ መቅደስ አቆማለሁ”፤ 34ይህን ተናግሮ ሄደ፤ ካህናት ግን እጆቻቸውን ወደ ሰማይ ዘርግተው ዘወትር ስለ ሕዝባቸው የተዋጋውን አምላክ እንዲህ ሲሉ ለመኑት፥ 35“አንተ ምንም የማይቸግርህ አምላክ ሆይ በእኛ መካከል የምትኖርበት ቤተ መቅደስ እንዲኖርህ ፈለግህ፤ 36አሁን እንግዲህ የቅዱሳን ሁሉ ቅዱስ አምላክ ሆይ ይህን ከጥቂት ጊዜ በፊት የነጻውን ቤት ከመርከስ ዘወትር ጠብቀው”።
የራዝያስ ሞት
37ከኢየሩሳሌም ሽማግሌዎች አንዱ ራዝያስ የተባለ ሰው በኒቃኖር ፊት ተከሰሰ፤ ይህ ሰው የሀገሩን ሕዝብ የሚወድ እጅግ ጥሩ ስም ያለው፥ ሰለ ፍቅሩ የአይሁዳውያን አባት ይባል የነበረ ጐምቱ ነው። 38ሕዝቡ ለጦርነት ከመነሣቱ በፊት ባሉት ጊዜዎች አይሁዳዊነቱን በማራመድ ተከሶ ነበረ፤ በታላቅ ወኔ ስለእምነቱ አካሉንና ሕይወቱን ሰጥቶ ነበር፤ 39ኒቃኖር በአይሁዳውያን ላይ ያለውን ጥላቻ ለመግለጽ ፈልጐ እንዲይዙት ከአምስት መቶ የሚበልጡ ወታደሮች ላከ፤ 40ምክንያቱም ይህን ሰው ከገደለ አይሁዳውያን ላይ ከባድ ምት እንዳሳረፈ ያምን ነበር። 41የእርሱ ወታደሮች የምሽጉን ግንብ ለመያዝና የውጪውን በር ለማፈረስ በመታገል ላይ ነበሩ፤ መዝጊያዎችንም ለማቃጠል ታዘው ነበረ። ራዝያስ በሁሉም ቦታ ስለተከበበ የገዛ ራሱን በሰይፍ ወጋ፤ 42በጨካኞች እጅ ከመውደቅና ክብሩን ከማዋረድ ይልቅ በክብር መሞትን መረጠ። 43ነገር ግን በወቅቱ ጦርነቱ በጣም ተፋፍሞ ስለ ነበር ሰይፈ በደንብ አልወጋውም ነበር፤ ወታደሮቹም በበሩ እየተጋፉ ወደ ውስጥ ገቡ፤ እርሱ በድፍረት ወደ ትልቁ ግንብ እየሮጠ ሄደና ምንም ሳይፈራ ወደ ሰዎቹ ተወርውሮ ወደቀ፤ 44ሁሉም በፍጥነት ወደ ኋላ ስላሉና ከቦታው ገለል ስላሉ በሆድ በምድር ላይ ወደቀ፤ 45ገና ስላልሞተ በመንፈሱ ተነሣሥቶ ብድግ አለ፤ ደሙን እየዘራና በቁስሎቹ በጣም እየተሠቃየ በሰዎቹ መካከል ሮጠ፤ በትልቅ ዓለት ድንጋይ ላይ ወጣ፤ 46ደሙ ሁሉ ፈስሶ አለቀ፤ አንጀቱን ከሆድ አወጣና በሁለት እጁ ይዞ በሰዎች መካከል ወረወረው፤ የሕይወትና የመንፈስ ጌታ አንድ ቀን መልሶ አንጀቱን እንዲሰጠው ጸልዮ፥ በዚህ ዓይነት ሞት ሞተ።
Currently Selected:
2ኛ መጽሐፈ መቃብያን 14: መቅካእኤ
Highlight
Share
Copy
Want to have your highlights saved across all your devices? Sign up or sign in