1ኛ ወደ ተሰሎንቄ ሰዎች 2
2
የጳውሎስ አገልግሎት በተሰሎንቄ
1ወንድሞች ሆይ! እናንተን መጎብኘታችን በከንቱ አልነበረም፥ እናንተም ራሳችሁ ታውቁታላችሁ። 2#የሐዋ. 16፥19-24፤ የሐዋ. 17፥1-9።ነገር ግን እንደምታውቁት በፊልጵስዩስ አስቀድመን መከራንና እንግልትን ብንቀበልም እንኳ፥ በታላቅም ተቃውሞ ፊት የእግዚአብሔርን የምሥራች ቃል ለእናንተ ለመናገር በአምላካችን ድፍረትን አገኘን። 3ምክራችን ከስሕተት ወይም ከርኩሰት ከተንኰልም የመነጨ አልነበረምና፤ 4ነገር ግን ወንጌል በአደራ እንዲሰጠን እግዚአብሔር የታመንን እንዳደረገን፥ እንዲሁ ሰውን ደስ ለማሰኘት ሳይሆን ልባችንን የሚመረምረውን እግዚአብሔርን ደስ ለማሰኘት ብለን እንናገራለን። 5እንደምታውቁት፥ የቁልምጫን ቃል ለስግብግብነትም ማመካኛ የሚሆን ነገር ከቶ አልተገኘብንም፥ እግዚአብሔርም ምስክር ነው። 6እንዲሁም ከእናንተም ሆነ ከሌሎች ክብርን አልፈለግንም፥ 7ዳሩ ግን የክርስቶስ ሐዋርያት እንደ መሆናችን መጠን ልንጫናችሁ በቻልን ነበር፤ ነገር ግን ሞግዚት የራስዋን ልጆች እንደምትንከባከብ፥ በመካከላችሁ የዋሆች ሆንን፤ 8ስለዚህም እናንተን በፍቅር በመሻት የእግዚአብሔርን ወንጌል ብቻ ሳይሆን የገዛ ነፍሳችንን ደግሞ ለማካፈል በጎ ፈቃዳችን ነበረ፤ ምክንያቱም ለእኛ እጅግ የተወደዳችሁ ሆናችሁ ስለ ነበር ነው።
9ወንድሞች ሆይ! ድካማችንንና ጥረታችንን ታስታውሱታላችሁ፤ የእግዚአብሔርን ወንጌል ለእናንተ እየሰበክን በአንዳችሁም ላይ እንኳ ሸክም ላለመሆን ስንል ሌሊትና ቀን እንሠራ ነበር። 10በእናንተ በአማኞች መካከል እንዴት ባለ ቅድስናና ጽድቅ ነቀፋም በሌለበት ኑሮ እንደ ነበርን እናንተና እግዚአብሔር ምስክሮች ናችሁ፤ 11አባት ለልጁ እንደሚሆነው እኛም እንዴት ለእያንዳንዳችሁ እንደ ሆንን እናንተው ታውቁታላችሁ፥ 12በመሆኑም ወደ መንግሥቱ ወደ ክብሩም ለጠራችሁ ለእግዚአብሔር እንደሚገባ እንድትመላለሱ እየመከርናችሁ፥ እያጸናናችሁና እየመሰከርንላችሁ ነበር።
13ስለዚህም የመልእክትን ቃል፥ እርሱም የእግዚአብሔርን ቃል ከእኛ በተቀበላችሁ ጊዜ፥ በእውነት እንዳለ በእናንተ በአማኞች ደግሞ እንደሚሠራ እንደ እግዚአብሔር ቃል እንጂ እንደ ሰው ቃል አድርጋችሁ ስላልተቀበላችሁት፥ እኛ ደግሞ እግዚአብሔርን ሳናቋርጥ እናመሰግናለን። 14#የሐዋ. 17፥5።እናንተ ወንድሞች ሆይ! በይሁዳ የሚኖሩትን በክርስቶስ ኢየሱስ ያሉትን የእግዚአብሔርን ማኅበሮች የምትመስሉ ሆናችኋልና፤ እነርሱ ከአይሁድ መከራ እንደ ተቀበሉ፥ እናንተ ደግሞ ያንን መከራ ከወገኖቻችሁ ተቀብላችኋልና። 15#የሐዋ. 9፥23፤29፤ 13፥45፤50፤ 14፥2፤5፤19፤ 17፥5፤13፤ 18፥12።እነዚያም ጌታን ኢየሱስንና ነቢያትን ገደሉ፤ እኛንም ደግሞ አሳደዱ፤ እግዚአብሔርንም ደስ አያሰኙም፤ ሰዎችንም ሁሉ ይቃወማሉ፤ 16ለአሕዛብ እንዳንናገር በመከልከል እነርሱ እንዳይድኑ ያደርጋሉ፤ በዚህም ያለማቋረጥ የኃጢአታቸውን መስፈርያ ይሞላሉ፤ ነገር ግን በመጨረሻ የእግዚአብሔር ቁጣው ይመጣባቸዋል።
ጳውሎስ የተሰሎንቄን ቤተ ክርስቲያን እንደገና ለመጎብኘት የነበረው ምኞት
17እኛ ግን ወንድሞች ሆይ! በልብ ሳይሆን በአካል ለጥቂት ጊዜ ብናጣችሁም፥ በብዙ ናፍቆት ግን ፊታችሁን ለማየት እጅግ ጓጓን፤ 18ወደ እናንተ ልንመጣ ፈልገን ነበርና፤ በእርግጥም እኔ ጳውሎስ አንድና ሁለት ጊዜ ሞክሬ ነበር፥ ሰይጣን ግን መሰናክል ሆነብን። 19ጌታችን ኢየሱስ በሚመጣበት ጊዜ በፊቱ የተስፋችን ወይም የደስታችን ወይም የመመክያችን አክሊል ምንድነው? እናንተ አይደላችሁምን? 20እናንተ ክብራችን ደስታችንም ናችሁና።
Currently Selected:
1ኛ ወደ ተሰሎንቄ ሰዎች 2: መቅካእኤ
Highlight
Share
Copy
Want to have your highlights saved across all your devices? Sign up or sign in