1ኛ የጴጥሮስ መልእክት 1
1
ሰላምታ
1የኢየሱስ ክርስቶስ ሐዋርያ ጴጥሮስ፥ በጳንጦስ፥ በገላትያ፥ በቀጰዶቅያ፥ በእስያ፥ በቢታንያ፥ ለተበተኑ መጻተኞች፤ 2እግዚአብሔር አብ አስቀድሞ ያወቃችሁ፥ በመንፈስ የተቀደሳቹ፥ ለኢየሱስ ክርስቶስ ትታዘዙና በደሙም ትረጩ ዘንድ ለተመረጣችሁት፥ ጸጋና ሰላም ይብዛላችሁ።
ስለ ሕያው ተስፋ
3ኢየሱስ ክርስቶስ ከሙታን በመነሣቱ ሕያው የሆነውን ተስፋ የሰጠን፥ ከምሕረቱ ብዛት በአዲስ ልደት ልጆቹ ያደረገን፥ የጌታችን የኢየሱስ ክርስቶስ አምላክ እና አባት ይመስገን፤ 4#ማቴ. 6፥19-20።እንዲሁም የማያልፍም፥ እድፈትም የሌለበት፥ የማይጠፋ ርስት በሰማይ ቀርቶላችኋል። 5ይህም ርስት በመጨረሻው ዘመን ይገለጥ ዘንድ ለተዘጋጀ መዳን በእምነት በእግዚአብሔር ኃይል ለተጠበቃችሁ ለእናንተ በሰማይ ተዘጋጅቶላችኋል። 6አሁን ለጥቂት ጊዜ ቢያስፈልግ በልዩ ልዩ ፈተና ብታዝኑም እንኳን፥ እጅግም ደስ ይላችኋል። 7#1ቆሮ. 3፥13።በዚህም በእሳት ምንም ቢፈተን ከሚጠፋው ወርቅ ይልቅ አብልጦ የሚከብር የተፈተነ እምነታችሁ፥ ኢየሱስ ክርስቶስ ሲገለጥ፥ ለምስጋናና ለክብር ለውዳሴም ይገኝ ዘንድ ነው። 8እርሱንም ሳታዩት ትወዱታላችሁ፤ አሁንም ምንም ባታዩትም በእርሱ በማመናችሁ መግለጽ በማይቻልና ክብር በሞላበት ሐሤት ደስ ብሎአችኋል። 9የእምነታችሁን ፍፃሜ እርሱም የነፍሳችሁን መዳን እየተቀበላችሁ ነውና።
10ለእናንተም ስለሚሰጠው ጸጋ ትንቢት የተናገሩት ነቢያት ስለዚህ መዳን ተግተው ፈለጉም መረመሩም፤ 11በእነርሱ ውስጥ የነበረው የክርስቶስ መንፈስ፥ ስለ ክርስቶስ መከራ እና ከእርሱም በኋላ ስለሚመጣው ክብር አስቀድሞ ሲመሰክር፥ ምን ወይም እንዴት ባለ ዘመን እንዳመለከተ ይመረምሩ ነበር። 12ከሰማይ በተላከ በመንፈስ ቅዱስ ወንጌልን የሰበኩላችሁ ሰዎች አሁን በነገሯችሁ ነገር፥ እናንተን እንጂ ራሳቸውን እንዳላገለገሉ ተገለጠላቸው፥ ይህንም ነገር መላእክቱ ሊመለከቱ ይመኛሉ።
በቅድስና ለመኖር የቀረበ ጥሪ
13ስለዚህ የልቡናችሁን ወገብ ታጥቃችሁና በመጠን ኖራችሁ፥ ኢየሱስ ክርስቶስ ሲገለጥ የምታገኙትን ጸጋ ፈጽማችሁ ተስፋ አድርጉ። 14እንደሚታዘዙ ልጆች፥ ባለማወቃችሁ አስቀድሞ የኖራችሁበትን ምኞት አትከተሉ። 15ነገር ግን የጠራችሁ እርሱ ቅዱስ እንደሆነ እናንተ ደግሞ በኑሮአችሁ ሁሉ ቅዱሳን ሁኑ። 16#ዘሌ. 11፥44፤45፤ 19፥2።ምክንያቱም “እኔ ቅዱስ ነኝና ቅዱሳን ሁኑ፤” ተብሎ ተጽፎአልና፤ 17ለሰው ፊትም ሳያደላ በእያንዳንዱ ላይ እንደ ሥራው የሚፈርደውን አባት ብላችሁ የምትጠሩት ከሆነ፥ በእንግድነታችሁ ዘመን በፍርሃት ኑሩ። 18ከአባቶቻችሁ ከወረሳችሁት ከከንቱ ኑሮአችሁ እንደተዋጃችሁ ታውቃላችሁ፥ በሚያልፍ ነገር በብር ወይም በወርቅ አይደለም፤ 19ነገር ግን ነውርና እድፍ እንደሌለው በግ ደም፥ በክርስቶስ ክቡር ደም ነው፥ 20ዓለም ሳይፈጠር እንኳ አስቀድሞ ታወቀ፤ ነገር ግን ስለ እናንተ በዘመኑ መጨረሻ ተገለጠ። 21እምነታችሁና ተስፋችሁ በእግዚአብሔር ይሆን ዘንድ፥ ከሞት ባስነሣው ክብርንም በሰጠው፥ በእግዚአብሔር በእርሱ ትተማመናላችሁ።
22ለእውነት በመታዘዝ ነፍሳችሁን አንጽታችሁ ለወንድማማች እውነተኛ ፍቅር፥ እርስ በርሳችሁ ከልባችሁ አጥብቃችሁ ተዋደዱ። 23ዳግመኛ የተወለዳችሁት በሕያውና ጸንቶ በሚኖር በእግዚአብሔር ቃል አማካይነት ከማይጠፋ ዘር እንጂ፤ ከሚጠፋ ዘር አይደለም።
24 #
ኢሳ. 40፥6-8። ምክንያቱም፥
“ሥጋ ሁሉ እንደ ሣር፥
ክብሩም ሁሉ እንደ ሜዳ አበባ ነውና፤
ሣሩ ይጠወልጋል አበባውም ይረግፋል፤
25የጌታ ቃል ግን ለዘለዓለም ጸንቶ ይኖራል።”
የተሰበከላችሁም የምሥራች ቃል ይህ ነው።
Currently Selected:
1ኛ የጴጥሮስ መልእክት 1: መቅካእኤ
Highlight
Share
Copy
Want to have your highlights saved across all your devices? Sign up or sign in