YouVersion Logo
Search Icon

1ኛ መጽሐፈ መቃብያን መግቢያ

መግቢያ
መቃቢስ የሚለው ቃል ምናልባት ትርጉሙ “መዶሻ” ማለት ነው። ይህ ስም በመጽሐፍ መቃቢያን ውስጥ ለካህኑ ማታቲያስ ሦስተኛ ልጅ ተሰጥቶ ነበር። በዚያን ዘመን በሶርያ የነበሩ ግሪኮች በአይሁድ እምነት ተከታዮች ላይ ከፍተኛ ስደት አድርሰውባቸው ነበር። ይህንን ስደት ለመቃወም አይሁዶች ሲያምጹ መሪያቸው ይሄው ሦስተኛው ልጅ ይሁዳ ነበር። ይህ ስያሜ ለይሁዳ መቃቢስ ወንድሞችም አገልግሎ ነበር። ከዚህም አልፎ ለደጋፊዎቹና በጊዜው ለነበሩም ሌሎች የአይሁድ ጀግኖች፥ ለሰባቱ ወንድማማቾች ተሰጥቶ ነበር።
ሁለቱ የመቃቢያን መጽሐፎች (በከፊል አንድ ዓይነት ቢሆኑም) በሁለተኛው ክፍለ ዘመን ከክርስቶስ ልደት በፊት በእስራኤል አገር ውስጥ የአይሁድ እምነትን በመቃወም የተከናወኑ ክስተቶችን የሚተርኩ ዘገባዎች ናቸው። ለዚህ ጭቆና የተሰጠው ጥብቅ ምላሽ ለጥቂት ጊዜም ቢሆን ለአይሁዳውያን ሃይማኖታዊና ፖለቲካዊ ነጻነት አስገኝቶላቸዋል።
አንደኛ መቃብያን የተጻፈው በ 100 ቅድመ ልደተ ክርስቶስ ሲሆን፥ የመጀመሪያው ቅጂ ወደ እኛ ባይደርስም የተጻፈው በዕብራይስጥ ቋንቋ ነው። ጸሐፊው የሕዝቡን ወግ እና የተቀደሱ መጻሕፍት ጠንቅቆ የሚያውቅና ለቅርብ ጊዜ ታሪኮችም (ከ 175 እስከ 134 ከክርስቶስ ልደት በፊት) አስተማማኝ መረጃን የሚሰጥ መሆኑን ያሳያል። ጸሐፊው ምናልባትም የዚህ የታሪክ ክፍል አባል ሊሆን እንደሚችል ይገመታል። የመጽሐፉ ዓላማ እግዚአብሔር በማታቲያስ ቤተሰብ አማካኝነት፥ በተለይም በሦስቱ ልጆቹ ማለትም በይሁዳ፥ በዮናታንና በስምዖን፤ እንዲሁም በልጅ ልጁ ዮሐንስ በሒርቃኑስ የሚከናወነውን የእስራኤልን ነፃነት መመዝገብ ነው። የእነርሱንም ቀናይነት ከጥንቶቹ የእስራኤል ጀግኖች፥ ከመሳፍንት፥ ከሳሙኤልና ከዳዊት ጋር ያነጻጽራል።
በመጽሐፉ ውስጥ የብሉይን የዕብራይስጥ ቅኔ የሚመስሉ ሰባት ዓይነት ቅኔያዊ ክፍሎች አሉ። አራቱ የሰቆቃና፥ ሦስቱ “የአባቶቻችንን” የውዳሴ ዝማሬዎች፥ የይሁዳ፥ እና የስምዖን ናቸው። በመጽሐፉ ውስጥ የተገለፀው አስተምህሮ በሁለተኛ መቃቢያን እና በትንቢተ ዳንኤል ውስጥ ከታዩት የእሥራኤል ባሕላዊ እምነቶች ጋር ይመሳሰላል። የእስራኤል ሕዝብ በእግዚአብሔር ቃል ኪዳን ተመርጠዋል። ለእነርሱም ዘላለማዊ ደጋፊያቸውና የማያቋርጥ የእርዳታ ምንጫቸው እግዚአብሔርን ብቻ ነው። እነርሱም እርሱን ብቻ ማወቅና ማምለክ አለባቸው። ለእነርሱ የተሰጣቸውን ሕጎችና መመሪያ በትክክል ማክበር ይጠበቅባቸዋል። በመጽሐፈ መቃቢያን የኢየሩሳሌም ቤተ መቅደስ ከረከሰ በኋላ በመቃቢያን ተጋድሎ ይታደሳል፤ ይህም የሃኑካ ለተባለው የአይሁድ በዓል ምንጭ ነው።
መጽሐፈ መቃቢያን ለእግዚአብሔር ሕግ በመታመን እስራኤል ለእግዚአብሔር ያለውን ፍቅርና ታማኝነት የሚገልጽበት እንደሆነ አበክሮ ያሳያል። መጽሐፉ የሚያብራራው ፍልሚያ በአይሁዶችና በአሕዛብ መካከል ብቻ እንደሆነ ሳይሆን ሕጉን አጥብቀው በያዙትና ያንን ሕግ ለማጥፋት በሚሠሩት አይሁድና ለሕጉ በሚቆሙ አይሁድም መካከል ነው። ትልቁም ወቀሳ የሚሰነዘረው በሙሴ ሕግ ላይ ታማኝነትን በሚያጎድሉት፥ ቃል ኪዳኑን ረስተው የግሪክን ባሕል መከተል በወደዱት አይሁዳን ላይ ነው።
አጠቃላይ የመጽሐፉ ይዘት
ፈታኝ ወቅትና የተሰጠው ምላሽ (1፥1—2፥70)
የይሁዳ መቃቢስ አመራር (3፥1—9፥22)
የዮናታን አመራር (9፥23—12፥53)
የስምኦን አመራር (13፥1—16፥24)
ምዕራፍ

Highlight

Share

Copy

None

Want to have your highlights saved across all your devices? Sign up or sign in