YouVersion Logo
Search Icon

1ኛ መጽሐፈ መቃብያን 6

6
የአንጥዮኩስ ኤጲፋንዮስ የመጨረሻ ቀናት
1ንጉሥ አንጥዮኩስ በላይኞቹ ክፍለ ሀገር ይዘዋወር ነበር፤ በፋርስ አገር በሀብትም፥ በብርና በወርቅ የታወቀች ኤሊማይድ የምትባል ከተማ እንዳለች ስማ፤ 2በመጀመሪያ በግሪካውያን ላይ የነገሠው የመቄዶንያው ንጉሥ የፊሊጶስ ልጅ እስክንድር የተዋቸው የወርቅ ጋሻዎችና የብረት ልብሶች፥ የጦር መሣሪያዎችም ያሉበት በጣም ሀብታም የሆነ ቤተ መቅደስ በዚያ እንዳለ ሰማ። 3ወደዚያ ሄደ፥ ከተማዋን ይዞ ለመዝረፍ ፈለገ፤ ነገር ግን የከተማዋ ሰዎች ነገሩን ስለ ሰሙ አልተሳካለትም፤ 4ውጊያ ሊገጥሙት ተነሡ፤ እርሱም ወደ ኋላ አፈገፈገ፤ እጅግ አዝኖ ወደ ባቢሎን ተመልሶ ለመሄድ ቦታውን ለቀቀ። 5ወደ ይሁዳ አገር የሄዱት ወታደሮች መሸነፋቸው ነበር፤ አይሁዳውያን በጦር መሣሪያዎችና በስንቅ ካሸነፉቸው በፋርስ ተነገረው። 6ከባድ ሠራዊት ይዞ የሄደው ሊስያስ በአይሁዳውያን ተሸንፎ ነበር፤ አይሁዳውያን በጦር መሣሪያዎችና በስንቅ ካሸነፉዋቸው ሠራዊቶች በወሰዱዋቸው ብዙ ምርኮዎች ተጠናክረው ነበር። 7እንዲሁም አንጥዮኩስ በኢየሩሳሌም መሠዊያ ላይ ሠርቶ የነበረውን ርኩስ ነገር ገለባብጠውት ነበር፤ ቤተ መቅደሳቸውን እንደ ቀድሞው በረጅም ግንብ ከበውት ነበር፤ እንዲሁም የንጉሡን ከተማ ቤተሱርን ይዘው አጠናክረውት ነበር፤ 8ንጉሡ ይህን ወሬ በሰማ ጊዜ ደንግጦና ታውኮ በአልጋው ላይ ወደቀ፤ ነገሮች እርሱ እንደፈለገው ስላልሆኑለት በትካዜ በሽታ ላይ ወደቀ። 9በኀዘን ተውጦ በሽታው እየጠናበት ብዙ ቀኖች ቆየ፤ የሚሞት መሆኑም ታወቀው፤ 10በዚያን ጊዜ ወዳጆቹን ሁሉ ሰብስቦ እንዲህ አላቸው፥ “እንቅልፍ ከዐይኖቼ ርቋል፤ ሐሳብ ያስጨንቀኛል፤ 11እንዲህ ዓይነት ሁኔታ በዙሪያዬ ሊከበኝ፥ የመከራም ጎርፍ ሊያጥለቀልቀኝ እንደምን እንደቻለ አይገባኝም፤ በጣም ጀግና የተወደድኩም ነበርኩና። 12አሁን ግን በኢየሩሳሌም ላይ የፈጸምኳቸው ክፉ ድርጊቶች ታወሱኝ፤ እዚያ የሚገኘውን የወርቅ ብር ዕቃዎች ሁሉ ወስጃለሁ፤ ያለ ምክንያት የይሁዳን አገር ሰዎች አስጨርሻለሁ። 13ይህ ክፉ ነገር የደረሰብኝ በዚህ ምክንያት መሆኑን አወቅሁ፤ እነሆ በሰው አገር በትካዜ መሞቴ ነው”።
የአምስተኛው የአንጥዮኩስ መተካት
14ከወዳጆቹ አንዱን ፊሊጶስን ጠርቶ በመላው መንግሥቱ ላይ ሾመው፤ 15ልጁን አንጥዮኩስን እንዲያሳድግና አደራ በማለት አክሊሉን፥ ቀሚሱን፥ ማኀተሙን ሰጠው። 16ንጉሥ አንጥዮኩስ በመቶ አርባ ዘጠኝ ዓመት ላይ በዚያን ቦታ ሞተ። 17ሊሲያስ የንጉሡን ሞት በሰማ ጊዜ ከልጅነቱ የሳደገው የንጉሡን ልጅ አነገሠና ሰሙን ኤውጳጦር አለው።
የኢየሩሳሌም ምሽግ በይሁዳ መቃቢስ ተከበበ
18የምሽጉ ሰዎች እስራኤላውያንን በቤተ መቅደሱ ዙሪያ ዘግተውባቸው ሁልጊዜ በእርሱ ላይ ክፉ ሥራ ለመሥራትና አረማውያንን ለማጠናከር ይፈልጉ ነበር። 19ይሁዳ እነርሱ ለመደምሰስ ፈለገ፤ እነርሱን ለመክበብና ለመውጋት ሕዝቡን ሁሉ ሰበሰበ። 20ሕዝቡም ተሰበሰበ፤ ምሽጉ ፊት ለፊት በመቶ ሐምሳ 163 ዓ.ዓ ከበባውና ውጊያው ተደረገ፤ የጦር መወርወሪያ መሣሪያዎችና ሌሎችም የጦር መኪናዎች ተዘጋጁ። 21ግን ከተከበቡት አንዳንዶቹ ከበባውን ጥሰው መውጣት ችለዋል። ከእነርሱ ጋር አንዳንድ ከሐዲዎች እስራኤላውያን አብረው ተቀላቀሉ። 22ወደ ንጉሡ ሄደው እንዲህ አሉት “እውነተኛ ፈርድ ለመስጠትና የወንድሞቻችንን ደም ለመበቀል እስከ መቼ ነው የምትጠብቀው? 23እኛ አባትህን ለማገልገልና ትእዛዙን ለመፈጸም፥ ሕጉንም ለመጠበቅ ደስተኞች ነበርን፤ 24በዚህ የተነሣ ከወገኖቻችን ጋር ተቆራርጠናል፤ በእኛ መካከል የነበሩትን ሰዎች አግኝተው ገድለዋል፤ ቤተሰቦቻችንን፥ ንብረቶቻችንንም ዘርፈዋል። 25እጃቸውን ያነሡት በእኛ ላይ ብቻ አይደለም፤ በግዛቶችህም ሁሉ ላይ ነው። 26ይኸውና መቅደሱንና ቤተሱርን አጠናክረው መሽገዋል። 27አሁን ቶሎ ብለህ ካልያዝሃቸው (ካላቆምሃቸው) እየጨመሩ ይሄዳሉ፤ ልታቆማቸውም የማትችልበት ደረጃ ላይ ትደርሳለህ”።
የአምስተኛው አንጥዮኩስና የሊስያስ ዘመቻ
የቤተ ዘካሪያስ ጦርነት
28ንጉሡ ይህን በሰማ ጊዜ ተቆጣና ወዳጆቹን ሁሉ የእግረኛና የፈረሰኛ ጦር አለቆችን፥ አማካሪዎችን ሰበሰበ። 29ከሌሎች መንግሥታትና ከሜድትራኒያን ደሴቶችም ቅጥረኛ ወታደሮች መለመለ። 30የዳበረ የጦርነት ልምድ ያላቸው የእረኛ ወታደሮቹ ቍጥር እስከ መቶ ሺህ፥ ፈረሰኛ ጦር ሃያ ሺህ፥ ዝሆኖች ደግሞ ሠላሳ ሁለት ነበሩ። 31በኤዱሚያስ በኩል መጥተው ቤተሱርን ከበቡ፤ በጦር ተሽከርካሪዎች እየተረዱ ብዙ ጊዜ ወጓት፤ ግን የተከበቡት መውጫ አበጅተው እሳት ለቀቁባትና በጀግንነት ተዋጉ። 32በዚያን ጊዜ ይሁዳ ከምሽጉ ወጥቶ በንጉሡ ሰፈር ፊት ለፊት በቤተ ዘካርያስ ቦታውን ያዘ። 33ንጉሡ በማለዳ ተነሥቶ ሠራዊቱን ባንድ ጊዜ ወደ ቤተዘካርያስ መንገድ ላይ አስወጣ፤ ወታደሮቹም ለውጊያ ተሰለፉ፤ መለከትንም ነፉ። 34ዝሆኖቹን ለውጊያ ለማነሣሣት የወይንና የእንጆሪ ጭማቂ አቀረቡላቸው። 35እንስሶቹ በእግረኛ ጦር መካከል ተከፋፈሉ፤ በእያንዳንዱ ዝሆን አጠገብ የብረት ልብስ የለበሱና የራስ ቁር ያደረጉ ወታደሮች ተሰልፈው ቆሙ፤ እንዲሁም አምስት መቶ ምርጥ ፈረሰኞች በእያንዳንዱ ዝሆን ጐን ተሰለፉ። 36እነዚህ ወታደሮች የዝሆኑን እንቅስቃሴ አስቀድመው በመመልከት ከቶ ሳይለዩት በሁሉ ቦታ ይከተሉት ነበር።፥ 37በእያንዳንዱ ዝሆን ላይ በጠፍር ጥብቅ ተደርጐ የታሰረ ጠንካራ የእንጨት ቤት እንደ መከላከያ ምሽግ ሆኖ ተሠርቶለት ነበር። በውስጡም ተመድበው የሚያገለግሉ ሶስት ተዋጊ ወታደሮችና አንድ የዝሆን ጠባቂ ይገኛሉ። 38ንጉሡ የቀረውን ፈረሰኛ ሠራዊት ጦሩን እንዲያነቃቃና እንዲጠብቅ በሠራዊቱ ጐንና ጐን አሰለፈው። 39በወርቅና በናስ የተሠሩ ጋሻዎች ላይ ፀሐይ ብልጭ ባለ ጊዜ ተራራዎቹ በሩ፥ እንደነደደ ችቦ ተንቦገቦጉ። 40የንጉሡ አንደኛው ክፍለ ጦር ወደ ተራራው ጫፎች ላይ ተሰማራ፤ የቀረው ክፍል ወደ ዝቅተኛው ቦታ ሄደ፤ በጥንቃቄና በሥነ ሥርዓት ይሄዱ ነበር። 41የእነዚህን የብዙ ወታደሮች ጫጫታና የእግሮቻቸውን ድምፅ፥ የሠራዊታቸውንና የመሣሪያዎቻቸውን ቅጭልጭልታ በሰሙ ጊዜ ሰዎች ሁሉ ደነገጡ፤ ይህ ሠራዊት በእውነቱ እጅግ በጣም ብዙና ብርቱ ነበር። 42ይሁዳና ሠራዊቱ ውጊያውን ለመጀመር ወደ ፊት ሄዱ፤ ከንጉሡ ሠራዊት ስድስት መቶ ሰዎች ሞቱ። 43አዋራን ተብሎ የሚጠራው ኤልዓዛር የንጉሡ የጦር ልብስ የተደረበበትና 44በቁመቱ ከሌሎቹ ዝሆኖች ሁሉ ከፍ ያለ አንድ ዝሆን በማየቱ የማይሞት ስም ለማትረፍ ብሎ ራሱን ሠዋ፤ 45ይህ ሰው በግራና በቀኝ ያሉትን ወታደሮች እየጨፈጨፈ በሠራዊቱ መካከል ወደ ዝሆኑ በድፍረት እየተንደረደረ ሄደ፤ ጠላቶቹም ወዲያና ወዲህ ገለል ብለው አሳለፉት። 46እርሱም ወደ ዝሆኑ ሥር ገብቶ ዝሆኑን በታች በኩል በኃይል ወጋውና ገደለው፤ ዝሆኑ ኤልዓዛር ላይ ወደቀና ኤልዓዛር ወዲያውኑ ሞተ፤ 47አይሁዳውያን የንጉሡን ጦር ኃይል ብርታት በማየት ወደ ኋላ አፈገፈጉ።
የቤተሱር መያዝና የጽዮን ተራራ በሶሪያውያን መከበብ
48የንጉሡ ሠራዊት ከኢየሩሳሌም ውጭ ሊገጥማቸው ተንቀሳቀሰ፤ ንጉሡም የይሁዳን ምድርና የጽዮንን ተራራ ከበበ። 49ከተማዋን ለቀው የሚወጡ የቤተሱር ሰዎች ንጉሡ ሰላምን እንደሚሰጥ ቃል ገባ፤ ከተማዋ ዓመታዊውን የእረፍት ጊዜ የምታሳልፍበት ስለ ነበር ከበባውን ተቋቁማ የምግብ አቅርቦትን ልታሟላ አልቻለችም ነበር። 50ንጉሡ ቤተሱርን ያዘ፤ እዚያም ጠባቂ ወታደሮች አደረገበት። 51ለብዙ ቀኖች ቤተ መቅደሱን ከበበ፤ የድንጋይ መወርወሪያ መሣሪያዎችና መዘውሮች፥ እሳትና ጦር ወርዋሪ መሣሪያዎች፥ ቀስት መወርወሪያዎችና ወንጭፎች ከእዚያ አደረገ። 52የተከበቡት ሰዎች የራሳቸውን ተሽከርካሪዎች በመስራት የመከላከል ችሎታቸውን አጠናከሩ። 53ነገር ግን በመጋዘናቸው የሚበላ አልነበራቸውም፤ ይህም የሆነበት ምክንያት ዘመኑ ሰባተኛው የዕረፍት ዓመት በመሆኑና ከአረመኔዎች መካከል ወደ ይሁዳ አገር በመሄድ የተጠጉት እስራኤላውያን የመጨረሻውን ስንቅ በልተው አጠናቀው ስለ ነበር ነው 54በረሃብ አደጋ ላይ ስነበሩ በቤተ መቅደሱ ጥቂት ሰዎች ብቻ ትተው ሌሎቹ ወደየቦታው ተበታተኑ።
ንጉሡ ለአይሁዳውያን የሃይማኖት ነጻነት ሰጠ
55ልጁን አንጥዮኩስ (5 ኛውን) እንዲያሳድግለትና ለመንገሥ እንዲያበቃው በንጉሥ አንጥዮኩስ (4 ኛው) የተሾመው ፊሊጶስ 56ከንጉሡ ጋር ዘምተው ከነበሩት ወታደሮች ጋር ከፋርስና ከምድያም ተመልሶ መምጣቱንና የሁሉም ነገር የበላይ አስተዳዳሪ መሆን መፈለጉን 57ሊስያስ በሰማ ጊዜ ለመሄድ በፍጥነት ተዘጋጀ፤ ንጉሡንና የሠራዊቱን መሪዎች፥ ሰዎቹንም ምግባችንም እያለቀ ሄደ፤ ይህ የከበብነው ቦታ በጣም የተጠናከረ ነው፤ የመንግሥቱ አስተዳደር ጉዳይ ኃላፊነቱ የወደቀው እኛ ላይ ነው። 58አሁን ቀኝ እጃችንን ወደ እነዚህ ሰዎች ዘርግተን ከእርሱ ጋርና ከሕዝባቸውም ሁሉ ጋር ሰላም እናድርግ፤ 59እንደ ቀድሞው በልማዳቸው መሠረት እንዲያደርጉ እንፍቀድላቸው፤ ምክንያቱም እነርሱ የተቆጡትና ይህን ሁሉ ያደረጉት ባህላቸውን ስለደመሰስንባቸው ነው በማለት ተናገረ። 60ይህ ንግግር ንጉሡንና ሹማምንቱን ደስ አሰኘ፤ ስለዚህ ሊስያስ ሰላም እናድርግ ባለው መሠረት ንጉሡ ወደ አይሁዳውያን የሰላም ቃል ላከ፤ እነርሱም እሺ ብለው ተቀበሉ። 61ንጉሡና ሹማምንቱም ጉዳዩን በመሐላ ካጸደቁት በኋላ የተከበቡት ከምሽጉ እንዲወጡ ተፈቀደላቸው። 62ንጉሡ ወደ ጽዮን ተራራ ሄዶ (ገብቶ) ቦታው ምን ያህል የማይደፈር መሆኑን እንደተመለከተ ምሽጐችን ካየ በኋላ መሐላውን በማፍረስ መካበቢውን ግንብ እንዲያፈርሱ ትእዛዝ ሰጠ። 63ከዚህ በኋላ በፍጥነት ሄደ፤ ወደ አንጾኪያም ተመለሰ፤ እዚያ ፊሊጶስን የከተማዋ ሹም ሆኖ አገኘው፤ ውጊያ ገጠመውና ከተማዋን በኃይል ወሰደበት።

Highlight

Share

Copy

None

Want to have your highlights saved across all your devices? Sign up or sign in