YouVersion Logo
Search Icon

1ኛ መጽሐፈ መቃብያን 5

5
ይሁዳ በኢዱማውያንና በአሞናውያን ላይ ዘመተ
1በአካባቢው የሚኖሩ አረማውያን ሕዝቦች መሠዊያው እንደገና መሠራቱንና ቤተ መቅደሱም ታድሶ እንደ ቀድሞው መሆኑን ሰሙ፤ 2ስለዚህ በጣም ተቆጡና በእነርሱ መካከል የሚኖሩትን የያዕቆብ (የእስራኤል) ልጆች ለመደመሰስ ወሰኑ፤ ሕዝባችንን መግደልና ማስወጣት ጀመሩ። 3ይሁዳ የኤሳውን ልጆች በኢዱምያስና በአቅራባቲና ወጋቸው፤ ምክንያቱም እነርሱ የእስራኤልን ሕዝብ ከበው ነበር፤ ደኀና አድርጐ መታቸውና አሸነፋቸው፤ ዕቃዎቻቸውንም ማርኮ ወሰደ። 4ቀጥሎም የቤያንን ልጆች ክፋት አስታወሰ፤ በየመንገዱ መጥመድ በመዘርጋት ሕዝቡን በአደጋ ላይ መጣላቸውን አሰበ፤ 5ከተማቸውን በመከበብና እንዳይፈናፈኑ በማድረግ ወጋቸው፤ አጠፋቸው፤ ምሽጐቻቸውንም በውስጦቸው ከነበሩት ሰዎች ጋር አጋያቸው። 6ከዚህ በኋላ ወደ አሞን ልጆች አለፈ፤ እዚያም በጢሞቴዎስ ይታዘዝ የነበረ ብርቱ ሠራዊትና ብዙ ሕዝብ አገኘ። 7ብዙ ውጊያ ካደረገ በኋላ ቀጠቀጣቸውና አሸነፋቸው፤ 8ጋዜርንና በአካባቢዋ የነበሩትን መንደሮች ያዘ፤ ከዚህ በኋላ ወደ ይሁዳ አገር ተመለሰ።
ለገለዓድና ለገሊላ ዘመቻዎች የተደረገ ቅድመ ዝግጅት
9የገለዓድ ሕዝቦች በምድራቸው የሚገኙትን እስራኤላውያንን ለማጥፋት ተባብረው ተነሡባቸው፤ እስራኤላውያን መጠጊያ ለማግኘት ወደ ድያቴማ ምሽግ ሸሹ። 10እንዲህ የሚል መልእክት ወደ ይሁዳና ወደ ወንድሞቹ ላኩ፥ “አረማውያን ሕዝቦች ሊያጠፉን ከበውናል፤ 11እነርሱ የተጠጋንበትን ምሽግ ለመውረር በዝግጅት ላይ ናቸው፤ የሠራዊታቸው መሪ ጢሞቴዎስ ነው፤ 12እስካሁን ድረስ ብዙ ጥፋት የደረሰብን ስለሆነ በፋጣኝ ደርሰህ ከእጃቸው አውጣን። 13ጦቢያ አገር የነበሩ ወንድሞቻችን ሁሉ ተገድለዋል፤ ሚስቶቻቸው ተማርከው፤ ንብረቶቻቸው ተወሰዋል፤ በእነዚህ አገሮች ወደ ሺህ የሚጠጉ ሰዎች አልቀዋል።” 14ይህ መልእክት ገና በመነበብ ላይ ሳለ ሌሎች መልእክተኞች ልብሳቸውን በኀዘን ቀደው ይህንኑ የመሰለ ወሬ ይዘው ከገሊላ መጡ፤ 15“የጰጦሌማይዳ፥ የጢሮስ የሲዶና ሰዎች በገሊላ ከሚኖሩት ከባዕድ አገር ሰዎች ጋር ሆነው እኛን ለማጥፋት ተባብረውናል”። 16ይሁዳና ሕዝቡ ይህን ነገር በሰሙ ጊዜ ስለተጨቆኑትና በውጊያ ስላሉት ወንድሞቻቸው ምን ማድረግ እንደሚገባ ለመመካከር ብዙ ሰዎችን ሰበሰቡ። 17ይሁዳ ወንድሙን ስምዖንን፥ “ሰዎች ምረጥና በገሊላ ያሉትን ወንድሞችህን ለማውጣት ሂድ፥ እኔና ወንድሜ ዮናታን ወደ ገለዓድ እንሄዳለን” አለው። 18የዘካሪያስን ልጅ ዮሴፍንና የሕዝቡን መሪ ዓዛርያስን ከቀረው ሠራዊት ጋር በይሁዳ አገር ተዋቸው። 19“ሕዝቡንም አስተዳድሩ (ጠብቁ) እኛ እስክንመለስ ድረስ ከአረማውያን ውጊያ አትግጠሙ” ብሎ አዘዛቸው። 20ለስምዖን ወደ ገሊላ የሚሄዱ ሦስት ሺህ ሰዎች ተሰጡ፤ ከይሁዳ ጋር ወደ ገሊላ የሚሄዱ ስምንት ሺህ ሰዎችም ተመረጡ።
የገሊላና የገለዓድ ዘመቻ
21ስምዖን ወደ ገሊላ ሂዶ ብዙ ውጊያ ካደረገ በኋላ አረማውያንን ጠራርጐ አጠፋቸው። 22እስከ ጰጦሎማይዳ በር ድረስ ተከታትሎ አባረራቸው። ሦስት ሺህ ያህል አረማውያን ሞቱ፤ ዕቃዎቻችን ሁል ማረከ። 23በገሊላና በአራባቲስ የሚኖሩትን አይሁዳውያን ከነሚስቶቻቸውና ከነልጆቻቸው፤ ከንብረታቸው ጋር በደስታ ወደ ይሁዳ አገር ወሰዳቸው። 24ይሁዳ መቃቢስና ወንድሙ ዮናታን ዮርዳኖስን ተሻግረው ሦስት ቀን በበረሃ ተጓዙ፤ 25በሰላም ወደ እነርሱ የመጡትን ናቦታውያንን አገኙዋቸው፤ 26እንዲሁም ለእነርሱ ብዙዎቹ በቦዝራ፥ በአሊሜስ፥ በቃስፎር፥ በማቄድ፥ በቃርኔን በእነዚህ ታላላቅ ከተሞችና ምሽጐች ውስጥ መከባባቸውን ነገሩዋቸው፤ 27በገለዓድ፥ በሌሎች ከተሞችም ውስጥ ተዘግተው የሚገኙ እንዳሉ፥ ጠላቶቻቸውም በሚቀጥለው ቀን ምሽጐቹን ወግተው ለመያዝና እዚያ የሚገኙትን ሁሉ ባንድ ቀን ለማጥፋት እንደወሰኑ አወሩላቸው። 28ይሁዳና ሠራዊቱ ቶሎ ብለው ወደ ቦዝራ በረሃ አመሩ፤ ከተማዋን ያዙ፤ ወንዶቹን ሁሉ በሰይፍ ገደሉ፤ ምርኮውን ሁሉ ወሰዱ፤ ከተማዋንም አቃጠሉ። 29በሌሊት ሄዱ፥ እስከ ምሽጉ አጠገብ ድረስ ተጓዙ። 30በነጋ ጊዜ ቀና ብለው ሲመለከቱ ከተማዋን ለመያዝ መሰላሎችንና የጦር ተሽከርካሪያዎች የሚያዘጋጁ ቍጥር ስፍር የሌላቸው ብዙ ወታደሮችን አዩ፤ ውጊያውም ተጀምሮ ነበር። 31ይሁዳ ውጊያው መጀመሩንና መለከቱንና የጦርነት ዋይታ ከመለከቱ ድምፅ ጋር እና ከብጥብጡ ጋር ወደ ሰማይ መድረሱን አይቶ 32ለሠራዊቱ እንዲህ አለ፤ “ዛሬ ስለ ወንድሞቻችን ተዋጉ”። 33ሠራዊቱን በሦስት ክፍል ከፋፍሎ ከጠላት በስተ ኋላ በኩል እንዲሄድ አደረገ፤ ያንጊዜ መለከት ተነፋ ከፍ ባለም ድምፅ ጸሎቱ ቀጠለ። 34የጢሞቴዎስ ሠራዊት ይሁዳ መቃቢስ መሆኑን አውቆ ካጠገቡ ሸሸ፤ ይሁዳም ሙሉ ለሙሉ ደመሰሳቸው፤ በዚያን ቀን በውጊያ ላይ የሞቱት ሰዎች ስምንት ሺህ ያህል ናቸው። 35ከዚህ በኋላ ፊቱን ወደ አሌማ መለሰና ወጋት፥ ያዛት፥ ወንዶቹን በሙሉ ገደለ፥ ምርኮውን ሰበሰበ፥ ከተማዋን አቃጠለ። 36ከዚያም ቃስፎን፥ በቄድን፥ በሶርነና ሌሎችንም የገለዓድ ከተሞች ለመያዝ ሄደ። 37ይህ ነገር ከሆነ በኋላ ጢሞቴዎስ ሌላ ጦር ሠራዊት ሰብስቦ ከወንዝ ወዲያ ማዶ በራፎን ፊት ለፊት ተሰለፈ። 38ዓረቦችም ጦሩን ለማሟላት ከባድ ሠራዊት ሆነው በጢሞቴዎስ ዙሪያ ተሰብስበዋል፤ 39ዓረቦችም ጦሩን ለማሟላት ተቀጥረዋል፤ ውጊያ ሊገጥሙህ ተዘጋጅተው ከወንዙ ወዲያ ማዶ ሰፍረዋል። ይሁዳ ውጊያ ሊገጥማቸው ወደ እነርሱ ሄደ፤ 40ከሠራዊቱ ጋር ሆኖ ወደ ውሃው (ወንዙ) ተጠጋ፤ ጢሞቴዎስም፤ “እርሱ ቀድሞን ወዲህ የተሻገረብን እንደሆነ ልንቋቋመው አንችልም፤ ምክንያቱም ከተሻገረ ከእኛ ይበልጥ እርሱ ጥቅም ያገኝበታል። 41ነገር ግን ከፈራና ከወንዙ ወዲያ ማዶ ከሰፈረ እኛ እንሻገረና እናሸንፈዋለን” አለ። 42ይሁዳ በወንዙ ውሃ አጠገብ በደረሰ ጊዜ በወንዙ ዳር የሕዝቡ ጸሐፊዎችን አቁሞ፥ “ሁሉም ወደ ውጊያ ይሂድ እንጂ ማንም እዚህ እንዲሰፍር አታድርጉ” ብሎ ትእዛዝ ሰጣቸው። 43እርሱ ቀድሞ ተሻገረና ወደ ጠላት ሄደ፤ ሕዝቡም ሁሉ ተከተሉት። አረማውያንን ቀጠቀጣቸው፤ እነርሱ የጦር መሣሪያዎቻቸውን ጥለው ወደ ቃርኔን ቤተ መቅደስ ሸሽተው ሄዱ። 44የይሁዳ አገር ሰዎች አስቀድመው ከተማዋን ያዙ፤ በኋላም ቤተ መቅደሳቸውንና እዚያ ያሉትን በእሳት አጋዩ። ቃርኔን ወደመች፤ ከዚያ በኋላ ይሁዳን መቋቋም አልተቻለም። 45ይሁዳ በገለዓድ የተገኙትን እስራኤላውያንን ትልቁንም ትንሹንም በሙሉ ከነሚስቶቻቸው፤ ከነልጆቻቸው፤ ከነንብረቶቻቸው በአንድነት ሰበሰባቸው፤ በጣም ብዙ ሕዝብ ነበረ፤ ሁሉም ወደ ይሁዳ አገር እንዲሄዱ ተደረገ። 46በመንገዳቸው ላይ ወደምትገኘው ታላቅና ብርቱ ከተማ ወደ ሆነችው ወደ ኤፌሮን ደረሱ፤ ይህችን ከተማ በመካከሏ ማለፍ ካልሆነ በቀር ወደ ቀኝ ወይ ወደ ግራ ዞሮ ማለፍ አይቻልም ነበር። 47የከተማይቱ ሰዎች ማለፍ ከለከሏቸው፤ በሮቹንም በቋጥኝ ድንጋዮች ጥርቅም አድርገው ዘጉ። 48ይሁዳም፤ “በሀገራችሁ በኩል አልፈን ወደ ሀገራችን የምንሄድ ነን፤ ማንም ክፉ አያደርግባችሁም፤ የምንፈልገው በእግራችን ብቻ ማለፍ ነው።” ሲል የሰላም ቃል ወደ እነርሱ ላከ፤ እነርሱ ግን አንከፈትልህም አሉት። 49በዚያን ጊዜ ይሁዳ ለሠራዊቱ፤ “በያለህበት እርጋ” የሚል ትእዛዝ አስተላለፈ። 50ወታደሮቹ ቦታ ቦታቸውን ያዙ፤ ይሁዳ ያን ቀን በሙሉና ሌሊቱንም በሙሉ ከተማዋን ወጋት፤ ከተማዋ በእጃቸው ወደቀች፤ 51ወንዶቹን በሙሉ በሰይፍ ገደላቸው፤ ከተማዋን ባድማ አደረጋት፤ ዕቃዎችን ማርኮ በተገደሉት ሰዎች ሬሳ ላይ አልፎ ሄደ። 52ከዚያም ዮርዳኖስን በመሻገር በቤትሳን ፊት ለፊት ወዳለው ታላቁ ሜዳ ተሻገሩ፤ 53ዮርዳኖስን የቀሩትን እያሰባሰበ፤ በመንገድ ያሉትን ሕዝብ እያበረታታ ወደ ይሁዳ ምድር እስኪደርስ ድረስ ወዲያ ወዲህ ይል ነበር። 54በደስታ ተሞልተው የጽዮንን ተራራ ወጡ፤ አንድም ሰው ሳይሞትባቸው በሰላም ስለ ተመለሱ የሚቃጠሉ ምሥዋዕቶችን አቀረቡ።
ውድቀት በያምንያ
55ይሁዳና ዮናታን በገልዓድ አገር ወንድሙ ስምዖን በጰጦሎማይዳ ፊት ለፊት በገሊላ በሚገኙበት ጊዜ 56የጦር ሹማምንቱ የዘካርያስ ልጅ ዮሴፍና አዛርያ የእነርሱን ጀግንነትና ያደረጓቸውንም ውጊያዎች ሰሙና 57“እኛም ዝናን እናትርፍ፤ እንሂድና በአካባቢያችን ያሉትን አረማውያን ሕዝቦች እንውጋ” ተባባሉ። 58ከነርሱም ጋራ ለነበረው ሠራዊት ሁሉ ትእዛዝ በመስጠት በጃኔያ ከተማዎች ላይ ሰፈሩ።#5፥58 ጃኔያ-አዛጦስ (አሽዶድ) አውራጃ ዋና ከተማ ናት። 59ጐርጊያስ ውጊያ ሊገጥማቸው ከወታደሮቹ ጋር ሆኖ ከከተማ ወጣ። 60ዮሴፍና ዓዛርያስ ተሸነፉና እስከ ይሁዳ ምድር ዳርቻ ድረስ ተባረሩ። በዚያን ቀን ከእስራኤል ሕዝብ ሁለት ሺህ ያህል ሰዎች ሞቱ። 61የጀግንነት ሥራ የሚሠሩ መስሏቸው ይሁዳንና ወንድሞቹን ስላልሰሙ የእስራኤል ሕዝብ ሽንፈት ደረሰበት። 62ነገር ግን እነርሱ እስራኤልን ለማዳን ኃላፊነት የተጣለባቸው ሰዎች ዓይነት አልነበሩም።
በኤዶሚያንና በፍልስጥኤም የተገኙ ድሎች
63ጀግናው ይሁዳና ወንድሞቹ በእስራኤል ዘንድና ስማቸው ሲነገር በተሰማበት በአረማውያን ሕዝቦችም ዘንድ ታላቅ ክብር አግኝተዋል። 64ሰው ሁሉ እነርሱን ለማመስገን በዙሪያቸው ይረባረብ ነበር። 65ይሁዳ ከወንድሞቹ ጋር ሆኖ በደቡብ አውራጃ ከዔሳው ልጆች (ኤዱማውያን) ጋር ለመዋጋት ሄደ፤ ሔብሮንና መንደሮችዋን ያዘ፤ ምሽጐቿን አፈረሰ፥ የመካበቢያውን ረጃጅም ግንቦች በእሳት አጋየ። 66ከዚህ በኋላ ወደ ፍልስጥኤማውያን አገር መጓዝ ጀመረ፤ በማሪባ በኩል አልፎ ሄደ። 67በዚያን ቀን ወደ ውጊያ በመሄድ ጉብዝናቸውን ለማሳየት የፈለጉ ካህናት በውጊያው ላይ ሞቱ፤ 68ቀጥሎም ይሁዳ የፍልስጥኤማውያን አገር ወደ ሆነችው ወደ አዞጦን ተመለሰ፤ መሠዊያዎቻቸውን ገለባበጠ፤ የጣዖቶቻቸውን የተቀረጹ ምስሎች አቃጠለ፤ የከተማዎቹን የምርኮ ዕቃዎች ወሰደ፤ ወደ ይሁዳ ምድር ተመለሰ።

Highlight

Share

Copy

None

Want to have your highlights saved across all your devices? Sign up or sign in