YouVersion Logo
Search Icon

1ኛ መጽሐፈ መቃብያን 2

2
የማታትያስ ቅዱስ ጦርነት መጀመር
ማታትያስና ልጆቹ
1በእነዚያ ዘመን ከዮሃሪብ ልጆች መካከል ካህን የሆነ፥ የዮሐንስ ልጅ የሆነ፥ የስምዖን የልጅ ልጅ ማታያስ ተነሣ፤ ኢየሩሳሌምን ትቶ በመዲን ተቀመጠ። 2አምስት ልጆችም ነበሩት፤ እነሱም ጋዲ የተባለ ዮሐንስ፤ 3ባሕሲ የተባለ ስምዖን፥ 4መቃቢስ የተባለ ይሁዳ፤ 5አዋራን የተባለ ኤልዓዛር፥ አጶሁስ የተባለ ዮናታን ናቸው። 6በይሁዳ አገርና በኢየሩሳሌም የተደረገውን ርኩሰት አየ፤ 7እንዲህም አለ፥ “ወዮልኝ፥ እኔ የተወለድሁት የሕዝቤን መጥፋትና የቅድስቲቱን ከተማ መደምሰስ ለማየት ነውን? ከተማይቱ በጠላት እጅ ስትወድቅና ቤተ መቅደሷም ለባዕድ ሰዎች ተላልፎ ሲሰጥ ቁጭ ብሎ ልቀር ነውን? 8ቤተ መቅደሱ ክብር እንደሌለው ሰው ሆኗል፤ 9ክብሩን የሚያንጸባርቁ ዕቃዎች ተማርከው ሄደዋል፤ ሕፃናቱ በየመንገዱ ታርደዋል፤ ወጣቶቹም በጠላት ሰይፍ ወድቀዋል። 10(የከተማችንን) የመንግሥትነት መብቷን ያልወረሰባት ምን አገር አለ? ምርኮዎችዋን ያልወሰደ ማን አለ? 11ጌጧ ተወስዶባታል፤ የቀድሞ ነጻነትዋ በባርነት ተቀይሯል። 12እነሆ የተቀደሰው ቦታ፥ ተቀይሯል። ውበታችን መና ሆኗል፤ አሕዛብ አርክሰውታል። 13ለመሆኑ የምንኖረው ለምኑ ነው?” 14ማታትያስና ልጆቹ በኀዘን ልብሳቸውን ቀደዱ፤ የተለተለ ልብሳቸውን የተለተለ ለብሰው ታላቅ ኀዘን አደረጉ። 15ለማስካድ የታዘዙ የንጉሡ መልእክተኞች መሥዋዕት ፍለጋ ወደ ሞደን መጡ። 16ብዙ እስራኤላውያን ወደ እነርሱ ሄዱ፤ ማታትያስና ልጆቹ ግን ብቻቸውን ተለይተው ቀሩ። 17የንጉሡ መልእክተኞች ማታትያስን እንዲህ አሉት፥ “አንተ በዚች ከተማ ክቡርና ታላቅ ሹም ነህ፤ በልጆችህና በወንድሞችህ የተደገፍህ ነህ። 18በል እንግዲህ ሕዝቦች ሁሉና በኢየሩሳሌም የቀሩ ሰዎች እንዳደረጉት አንተ በመጀመሪያ ቅደምና በንጉሡ የተወሰነውን ነገር ፈጽም፤ አንተና ልጆችህ ቁጥራችሁ ከንጉሡ ወዳጆች ጋር ይሆናል፤ ብርና ወርቅ ይሰጣችሁና ብዙ ስጦታዎችም ይደረግላችሁና ትከብራላችሁ”። 19ማታትያስ በብርቱ ቃል እንዲህ ሲል መልስ ሰጠ፤ “በንጉሡ መንግሥት ውስጥ ያሉት ሕዝቦች ሁሉ ከየአባቶቻቸው አምልኮ ርቀውና ትእዛዙንም እሺ ብለው ቢቀበሉትም 20እኔና ልጆቼ፥ ወንድሞቼም የምንከተለው የአባቶቻችንን ቃል ኪዳን ነው። 21ሕጉንና ትእዛዞቹን እንዳንተው ጸጋውን ይስጠን። 22ወደ ቀኝ ወይም ወደ ግራ በማለት ከአምልኮአችን ርቀን የንጉሡን ትእዛዞች አንቀበልም”። 23ማታትያስ ንግግሩን ባቆመ ጊዜ አንድ አየሁዳዊ ሰው በንጉሡ ትእዛዝ መሠረት በሞዲን መሠዊያ ላይ በሰዎች ሁሉ ፊት ለመሠዋት ወደ ፊት ሄደ። 24ማታትያስ ይህን ባየ ጊዜ በእግዚአብሔር ፍቅር ተቃጠለ፤ ሰውነቱም በቁጣ ተንቀጠቀጠ፥ በጣም ተቆጣ፥ ሮጦም ሰውዬውን በመሠዊያው ላይ አረደው፤ 25ሰዎቹ እንዲሰዉ ያስገድድ የነበረውን የንጉሡን ባለሟል ወዲያው ገደለውና መሠዊያውንም ገልብጦ ጣለው። 26በሳሉ ልጅ በዚምሪ ላይ ፊንሃስ እንዳደረገው ሁሉ ማታትያስ በሙሴ ሕግ ፍቅር በመቃጠል እንዲሁ አደረገ። 27ከዚህ በኋላ ማታትያስ በከተማው መካከል ሲያልፍ ድምፁን ከፍ አድርጐ፥ “የሙሴን ሕግ የሚያፈቅሩ ሰዎች ሁሉ፥ ቃል ኪዳኑንም የሚደግፉ ሁሉ ይከተሉኝ” እያለ ጮኸ። 28እርሱና ልጆቹ በከተማ ያላቸውን ሁሉ ትተው ወደ ተራራ ሸሹ።
የሰንበት ቀን መከራ በበረሃ
29ፍትሕንና ትክክለኛነትን ይፈልጉ የነበሩ ብዙ ሰዎች በበረሃ ለመኖር ወደ በረሃማው አገር ወረዱ፤ 30እነርሱ፥ ልጆቻቸውና ሚስቶቻቸው መከራ ስለ በዛባቸው ሁሉም ወደ በረሃ ሄዱ። 31በዳዊት ከተማም፥ ኢየሩሳሌም ለነበሩ ለንጉሡ ባለሥልጣኖችና ወታደሮች የንጉሡን ትእዛዝ አንቀበልም ያሉ በበረሃ ወደሚገኝ ያልታወቀ ስፍራ እንደ ሸሹ ተነገራቸው። 32ብዙ ወታደሮች ተከታተሏቸውና ደረሱባቸው፤ የጦር ሰፈራቸውንም በእነርሱ ፊት ለፊት አደረጉ፤ በሰንበት ቀን ከእነርሱ ጋር ውጊያ ለመግጠምም ተዘጋጁ፤ 33“አሁን እንግዲህ በቃ፤ ውጡና የንጉሡን ትእዛዝ ፈጽሙ፤ ሕይወታችሁም ይድናል” አሏቸው። 34እነርሱ ግን፥ “አንወጣም፥ ሰንበትን አፍርሰን ንጉሡ ያዘዘውን አንቀበልም” ብለው መለሱ። 35ወታደሮቹ ወዲያውኑ ውጊያ ገጠሙዋቸው፤ 36እነዚያ ምንም አልመለሱለቸውም፤ ድንጋይም አልወረወሩባቸውም፤ መደበቂያቸውንም አልዘጉባቸውም። 37“ሕሊናችን ንጹሕ ሆኖ እንሙት፤ ያለ አግባብ እንደምትገድሉን ሰማይና ምድር ይታዘባሉ” ይሉ ነበር። 38እነዚህ ሰዎች በሰንበት ቀን ጦርነት ገጠሙዋቸው፤ ከነሚስቶቻቸው፥ ከነልጆቻቸው፥ ከነአባቶቻቸው አንድ ሺህ የሚያህሉቱ በዚህ ቀን አለቁ። 39ማታትያስና ጓደኞቹም ይህን በሰሙ ጊዜ እጅግ አዘኑ። 40እርስ በርሳቸውም እንዲህ ተባባሉ፦ “ሁላችንም እንደ ወንድሞቻችን አይሁዶች ብንሆን ኖሮ ሕይወታችንንና ሃይማኖታችንን ለመጠበቅ ከአሕዛብ ወገን የሆኑትን ስንዋጋ እንኑር ብንል፥ ከምድር ገጽ ፈጽመው ያጠፉናል።” 41በዚያም ቀን በሰንበት ቀን አንድ ሰው ቢገድልባቸው፥ እነርሱም ራሳቸውን መከላከል እንዳለባቸውና ከዋሻቸው ውስጥ እንዳሉ ዐይኖቻቸው እያየ እንደሞቱ ወገኖቻቸው እንዳይጠፉ ወሰኑ። 42በዚያን ጊዜ የእስራኤል ጀግኖች እና ተዋጊዎች ከሕጉ ጎን ለመቆም ፈቃደኛ የሆኑ ሰዎች በአሲዳውያን እየተመሩ ተቀላቀሉዋቸው። 43ከእነዚህ ከሚደርስባቸው ክትትል ለመሸሽ የመረጡት ሁሉ ከጐናቸው በመሰለፋቸው ኃይላቸው እየተጠናከረ ሄደ። 44ራሳቸውን በሠራዊት መልክ አደራጅተው ኃጢአተኞችንና ክፉዎቹን (ከሐዲዎቹን) በቁጣቸው መቷቸው፤ የቀሩት ወደ አረማውያን ሕዝብ ሸሽተው አመለጡ። 45ማታትያስና ጓደኞቹ እየዞሩ የአረማውያንን መሠዊዎች አፈራረሱ። 46በእስራኤል አገር የሚገኙትን ያልተገረዙ ልጆችንም በግድ ገረዙዋቸው፤ 47ትዕቢተኞቹንም በታተኑዋቸው፥ ሥራቸውም ተቃናላቸው። 48ከአረማውያንና ከነገሥታት እጅ የሙሴን ሕግ ነጥቀው ወሰዱ፤ የኃጢአተኛቹንም ወኔ ሰለቡ።
የማታትያስ ምስክርነት እና ሞት
49የማታትያስ ቀኖች ወደ ፍጻሜአቸው እየተቃረቡ ሄዱ፤ ለልጆቹ እንዲህ አላቸው፥ “እነሆ አሁን ትዕቢትና በደል ወደ ላይ ከፍ ከፍ እያሉ ነው፤ ዘመኑም የብጥብጥና ጥላቻ ዘመን ነው፤ 50ልጆቼ ሆይ የሙሴ ሕግ ፍቅር ይኑራችሁ፤ የአባቶቻችሁን ቃል ኪዳን ለመፈጸም ሕይወታችሁን አሳልፋችሁ የምትሰጡበት ወቅት አሁን ነው። 51አባቶቻችን በጊዜአቸው የፈጸሟቸውን ሥራዎች አስታውሰ፤ ታላቅ ክብርና ዘላለማዊ ዝና ታገኛላችሁ፤ 52አብርሃም በፈተናው ጊዜ ታማኝ ሆኖ ስለ ተገኘ እንደ ጽድቅ ሆኖ አልተቆጠረለትምን? 53ዮሴፍ በመከራው ጊዜ ሕግን ጠብቆ የግብጽ አገር ጌታ ሆነ። 54አባታችን ፊንሃስ በተቃጠለ ፍቅሩ የዘላለማዊ ክህነት ቃል ኪዳንን ተቀበለ። 55ኢያሱ ግዳጁን በመፈጸሙ በእስራኤል ዳኛ ሆነ። 56ካሌብ ለእስራኤል ሕዝብ በሰጠው እውነተኛ ምስክርነቱ እርስት አገኘ። 57ዳዊት በመንፈሳዊነቱ ለዘለዓለም ንጉሣዊ ዜማን ወረሰ። 58ኤልያስ ስለ ሙሴ ሕግ በፍቅር በመቃጠሉ፤ ወደ ሰማይ ተወሰደ። 59አናንያ፥ አዛርያ፥ ሚሳኤል በእግዚአብሔር ስለተማመኑ፤ ከእሳት ነበልባል አመለጡ። 60ዳንኤል በቅንነቱ ከአንበሶች አፍ ዳነ። 61በእርሱ በእግዚአብሔር ተስፋ የሚያደርጉ ሁሉ ከትውልድ እስከ ትውልድ ድክመት እንደማያገኛቸው ዕወቁ። 62የኃጢአተኛን ሰው ዛቻ አትፍሩ፤ ምክንያቱ የእርሱ ክብር የሚሄደው ወደ መበስበስና ወደ ትል ነው። 63ዛሬ ክብርን ያገኛል፥ ነገ ግን አይገኝም፤ ምክንያቱም ወደ መጣበት ትቢያ ይመለሳል፤ ዕቅዱም እንዳልነበር ይሆናል። 64ልጆቼ ሆይ፥ የሙሴን ሕግ ጠንክራችሁ ያዙ፤ ምክንያቱም ትልቅ ክብር የሚያስገኝላችሁ እርሱ ነው። 65ወንድማችሁ ስምዖን መልካም ምክር ሊለግሳችሁ እንደሚችል አውቃለሁ፤ ሁልጊዜ ስሙት፥ አባት ይሆናችኋል። 66ገና በወጣትነቱ ጀግና የሆነው ይሁዳ መቃቢስ የጦር ሠራዊታችሁ መሪ ይሆናል፤ በአሕዛቦች ላይ በምታደርጉት ጦርነት ይመራችኋል። 67እናንተ ግን የሙሴን ሕግ የሚጠብቁትን ሁሉ ወደ እናንተ ሰብስቧቸው፤ የሕዝባችሁን በደል ተበቀሉ። 68አረማውያን ያደረጉባችሁን ክፉ ነገር መልሳችሁ አድርጉባቸው፤ የሙሴ ሕግ የሚያዘውን በጥብቅ ፈጽሙ”። 69ከዚህ በኋላ ባረካቸውና ሞተ። 70በመቶ አርባ ስድስት ዓመተ ዓለም ሞተ፤ በሞዲን በቤተሰብ መቃብ ተቀበረ፤ መላው እስራኤል በጥልቅ አዘነለት።

Highlight

Share

Copy

None

Want to have your highlights saved across all your devices? Sign up or sign in