YouVersion Logo
Search Icon

1ኛ መጽሐፈ መቃብያን 10

10
ስክንድር ባላስ የዮናታንን ድጋፍ ለማግኘት ጣረ፤ ሊቀ ካህናትም አድርጐ መረጠው
1በመቶ ስልሳ ዓመተ ዓለም የአንጥዮኩስ ልጅ እስክንድር ኤጲፋኔስ መጥቶ ጰጠሎማይዳን ያዘ፤ ሰዎቹ ተቀበሉት፤ ከዚያም ነገሠ። 2ይህን በሰማ ጊዜ ንጉሥ ዲመትሪዮስ እጅግ ብዙ ሠራዊት ሰብስቦ እርሱን ለመውጋት ወደ እርሱ ሄደ። 3ከዚህም ሌላ በእርቅ የተሞላና ዮናታንንም ለከፍተኛ ማዕረግ እንደሚያበቃው የሚያረጋግጥ ቃል የያዘ ደብዳቤ ላከ፤ 4“በእኛ ላይ ከእስክንድር ጋር የሰላም ንግግር ከማድረጉ በፊት እኛ በፍጥነት ከሱ ጋር የሰላም ንግግር እናድርግ፤ 5ምክንያቱም በዚያን ጊዜ በእርሱ ላይና በወንድሞቹ ላይ እንዲሁም በሕዝቡ ላይ ያደረግነውን ክፉ ነገር ሊያስብ ይችላል” በማለትም አሳሰበ። 6እንዲያውም ሠራዊት እንዲያሰባስብ፤ የጦር መሣሪያ እንዲሠራ፥ የጦር ጓደኛው ነኝ እንዲል ሥልጣን ሰጠው፤ በኢየሩሳሌም ምሽግ ውስጥ በዋስትና የተያዙበት ሰዎች እንዲመለሱለትም አዘዘ። 7ዮናታን ወደ ኢየሩሳሌም መጥቶ በሕዝቡ ሁሉና በምሽጉ ውስጥ በነበሩት ሰዎች ሁሉ ፊት መልእክቱን አነበበ። 8ንጉሡ ለዮናታን ሠራዊት እንዲሰበሰብ ሥልጣን መስጠቱን በሰሙ ጊዜ ሰዎቹ በጣም ፈሩ። 9የኢየሩሳሌም ምሽግ ሰዎች በዋስትና የተያዙትን ሰዎች ለዮናታን አስረከቡ፤ እሱም እነርሱን ለቤተሰቦቻቸው አስረከባቸው። 10ዮናታን በኢየሩሳሌም የተቀመጠ፤ ከተማዋን እንደገና መገንባት ጀመረ። 11ሥራውን ለሚሠሩት ሰዎች ግንቡን እንዲገነቡና የጽዮንን ተራራ በጥርብ ድንጋይ ዙሪያዋን እንደከቧት ትእዛዝ ሰጣቸው፤ እነርሱም እንደ ትእዛዙ አደረጉ። 12ባቂደስ ባሠራቸው ምሽጐች ውስጥ ይኖሩ የነበሩ የሌላ አገር ሰዎች ሸሽተው ሄዱ። 13እያንዳንዱ ሰው ወደየአገሩ ለመመለስ ቦታውን ተወ። 14ሕግንና ትእዛዝን ጥሰው የነበሩ አንዳንድ ሰዎች በቤተሱር ብቻ እንዲቀሩ ተውአቸው፤ ምክንያቱም እርሱ የመጠጊያ ቦታ ነበረ። 15ዲመትሪዮስ ለዮናታን የላከለትን የተስፋ ቃል ንጉሥ እስክንድር አወቀ። እንዲሁም ዮናታንና ወንድሞቹ ያደረሱባቸወም መከራዎች ተነገረው። 16“ከቶ እንዲህ ያለ ሰው እናገኛለን? ከዛሬ ጀምሮ እርሱን ወዳጅና የጦር ጓደኛ ማድረግ ያስፈልገናል” አለ። 17ስለዚህ እንዲህ የሚል ደብዳቤ ጻፈለት፤ 18“ንጉሥ እስክንድር ለወንድሙ ለዮናታን ሰላምታ ያቀርባል። 19አንተ ጀግናና የኛ ወዳጅ ለመሆን ብቁ መሆንህን ሰምተናል፤ 20ስለዚህ ከዛሬ ቀን ጀምሮ የሕዝብህ ሊቀ ካህናት እንድትሆን ሾመንሃል፤ የእኛ ወገን እንድትሆንና ከእኛ ጋር ያለህን ወዳጅነት እንድትጠብቅ ‘የንጉሥ ወዳጅ’ የሚል ስም ሰጥተንሃል።” ለዮናታን የከፋይ ልብስና የወርቅ አክሊል በመላክ አከበረው። “በዚህም መሠረት ፍላጎታችንና ወንድማዊ ግንኙነታችንን እንድታውቅና እንድታጠናክርም እንፈልጋለን”። 21ዮናታን በሰባተኛው ወር በመቶ ስልሳ ዓመት (ጥቅምት) 15 2 ዓ.ዓ. (በዳስ) በዓል ጊዜ ቅዱሱን ልብስ ለበሰ፤ ወዲያውኑ ሠራዊቱን ለማሰባሰብና መሣሪያ ለመሥራት ተነሣ።
ለዮናታን የተላከ የንጉሥ ዲሜጥሮስ ደብዳቤ
22ዲሜጥሮስ ይህን በሰማ ጊዜ አዘነ፤ 23“እስክንድር የአይሁዳውያኑን ወዳጅነት ቀድሞ በማግኘት አቋሙን ያጠናከረውና እቅዳችንንም ያሰናከለው ምን ብናደርገው ይሆን? 24እኔም ብሆን እድገትና ሀብትን አስገኝላችኋለሁ በሚል የእነርሱን ድጋፍ ማግኘት አለብኝ” በማለት ተናገረ። በመቀጠልም 25እንዲህ ሲል ጻፈላቸው፥ “ንጉሥ ዲሜጥሮስ ለአይሁድ ሕዝብ ሰላምታ ያቀርባል፤ 26በእኛ መካከል የተደረገውን ውል እናንተ ሁልጊዜ አጽንታችሁ ይዛችኋል፤ የእኛ ወዳጆች ሆናችሁ ቀርታችኋል፤ ወደ ጠላቶቻችን አልሄዳችሁም፤ ይህን ሁሉ አውቀናል፤ ስለዚህም ደስ ብሎናል። 27ለእኛ ታማኞች መሆናችሁን ቀጥሉ፤ ስለታማኝነታችሁ መልካም ነገሮች እናደርግላችኋለን። 28ከቀረጥ ነጽ እናውጣችኋለን፤ ልዩ መብቶችን እንሰጣችኋለን። 29ከዛሬ ጀምሮ እንግዲህ ነጻ አውጥቻችኋለሁ፤ አይሁዳውያንን በሙሉ በቀረጥ ከጨው ግብር፥ ከዘውድ ግብር ነጻ አውጥቻለሁ። 30በሌላ በኩል ከዛሬ ጀምሮ ከመሬት ፍሬ የሚሰጠውን ሲሶ ለሁልጊዜ ትቻለሁ፤ ከዛፎች ፍሬ የሚደርሰኝንም እኩሌታ ትቻለሁ፤ ይህን ያደረግሁት ለይሁዳ አገርና ከሰማርያና ከገሊላ ለተጨመሩለት ለሦስቱም አገሮች ነው። 31ኢየሩሳሌም ቅድስትና ነጻ ትሆናለች፤ እንዲሁም የእርሷ ምድር ከአሥራትና ከግብር ነጻ ይሆናል። 32የኢየሩሳሌምንም ምሽግ እለቃለሁ፤ ኢየሩሳሌምን ለሊቀ ካህናቱ ትቼለታለሁ፤ እርሱ የሚጠብቋን ሰው መርጦ እዚያ ማድረግ ይችላል። 33በመንግሥቴ ውስጥ የትም ቦታ ይሁን ከእሁዳ አገር ተማርኮ የመጣ አይሁዳዊ ሁሉ ምንም ሳይከፍል ነፃ እንዲሆን አድርጌዋለሁ፤ ሁሉም ከግብር ነፃ ይሁኑ፤ የተያዘባቸውም እንስሳ ነፃ ይውጣ፤ 34የበዓል ቀኖች ሁሉ፤ የሰንበት ቀኖች፤ የመጀመሪያ ጨረቃ ቀኖች፤ የትእዛዝ በዓላት ቀኖች፤ እንዲሁም ከበዓል በፊት ያሉት ሦስት ቀኖችና ከበዓል በኋላ ያሉት ሦስት ቀኖች በመንግሥቴ ለሚገኙ አይሁዳውያን ሁሉ ግብር የማይከፈልባቸው ነጻ ቀኖች ይሆናሉ። 35ማንም እነርሱን ለማስከፈል ወይም በምንም ዓይነት እነርሱን ለማስቸገር ሥልጣን አይኖረውም። 36አይሁዳውያን በንጉሡ ሠራዊት ውስጥ እስከ ሠላሳ ሺህ ወታደሮች ተመልምለው ሊገቡ ይችላሉ፤ ለመንግሥት ሠራዊት ሁሉ የሚከፈለው ደሞዝ ይከፈላቸዋል። 37አንዳንዶቹ በታላላቅ መንግሥት ምሽጐች ውስጥ ይሆናሉ። አይሁዳውያን በመንግሥት ታማኝነት ቦታ ላይ ይሰማሉ፤ መሪዎቻቸውና አለቆቻቸው ከነእርሱ ውስጥ ይመረጣሉ፤ ንጉሡ በይሁዳ አገር ውስጥ እንዳዘዘው በሕጋቸው መሠረት ይተዳደራሉ። 38ከሰማርያ ተወስደው ለይሁዳ አገር የተጨመሩት ሦስቱ አገሮች ከይሁዳ አገር ጋር ይሁኑ፤ በአንድ አለቃ ሥር ብቻ ይሁኑ፤ ለሊቀ ካህናት ብቻ እንጂ ለሌላ ባሥልጣን አይታዘዙ። 39አምልኮ የማያስፈልገውን ገንዘብ ለመሸፈን እንዲቻል ለኢየሩሳሌም ቤተ መቅደስ ጰጦሌማይዳንና አካባቢዋን ሰጥቻለሁ። 40እኔም ከግብር ከማገኘው ድርሻዬ በየዓመቱ ዐሥራ አምስት ሺህ ብር እሰጣለሁ። 41መጋቢወች እንዳለፉት ዓመታት ሳይከፍሉ ያስቀሩትን ሁሉ ከዛሬ ጀምሮ ለቤተ መቅደሱ ሥራዎች እንዲውል ይሰጣሉ። 42ከዚህም በላይ በየዓመቱ ከቤተ መቅደስ ይወሰድ የነበረው አምስት ሺህ ብር በአገልግሎት ላይ ላሉት ካህናት ይሆናል። 43ለንጉሥ መክፈል በሚገባቸው ነገር ወይም በሌላ ጉዳይ ምክንያት በኢየሩሳሌም ቤተ መቅደስና በአካባቢዎቹ የሙጥኝ ያሉ ሁሉ በመንግሥቴ ውስጥ ካላቸው ንብረት ሁሉ ጋር ነጻ ይሆናሉ። 44ለቤተ መቅደሱ ማሠሪያና ማደሻ የሚወጣው ገንዘብ ከንጉሡ ግምጃ ቤት ወጪ ይሆናል። 45ግንቦቹን እንደገና ለማሠራትና የኢየሩሳሌምንም መካበቢያ ዳግም ለመገንባት በይሁዳ አገር ያሉትንም ግንቦች ለማሠራት የሚያስፈልገው ወጪ ከንጉሡ ሒሳብ ወጪ ያደረጋል”።
ዮናታን የንጉሥ ዲሜጥሮስን ስጦታ ሳይቀበል ቀረ፤
የንጉሥ ዲሜጥሮስ ዜና እረፍት
46ዮናታንና ሕዝቡ እነዚህን ቃሎች በሰሙ ጊዜ አናምንም ቃሎቹንም አንቀበልም አሉ፤ ምክንያቱም ዲሜጥሮስ በእስራኤል ላይ ያደረገው ክፉ ነገር ሁሉና በነእርሱ ላይ የፈጸመው ከባድ ጭቆና ገና ከአሳባቸው አልጠፋም ነበር። 47ከሁለቱ ምርጫዎች መካከል የተሻለ ሆኖ ያገኙትን የንጉስ እስክንድርን ቃል ለመቀበል ወሰኑ፤ ከጐኑም ተሰለፉ። 48ንጉሥ እስክንድር ብዙ ሠራዊት ሰብስቦ በዲሜጥሮስ ላይ ለመዝመት ተነሣ። 49ሁለቱ ነገሥታት ሲዋጉ የዲሜጥሮስ ሠራዊት ሸሸ፤ እስክንድር ተከታተለውና አሸነፈው፤ 50ጦርነቱን በወኔ ፀሐይ እስክትጠልቅ ድረስ ቀጠለ፤ በዚያኑ ቀን ዲሜጥሮስ ሞተ፤
የዮናታን ገዥነትና የጦር እልቅና፤
የንጉሥ እስክንድር እና ኪሊዮጳጥራ ጋብቻ
51እስክንድር ወደ ግብጽ ንጉሥ ጰጠሎሜዮስ እንዲህ ሲል መልእክተኛ ላከ፤ 52“እነሆ ወደ መንግሥቴ ተመልሼ በአባቶቼ ዙፋን ላይ ከተቀመጥኩ በኋላ ዲሜጥሮስን ከወታደሮች ጋር አሸፌ ዙፋኑን ይዣለሁ። 53ከእርሱ ጋር ውጊያ አድርገን እርሱንና ሠራዊቱን በፍጹም ደምስሰናል፤ የእርሱን ንጉሣዊ ዙፋን ይዘናል። 54አሁን እንግዲህ ወዳጆች እንሁን፤ ከዛሬ ጀምሮ ሴት ልጅህን በሚስትነት ስጠኝ፤ አማችህ እሆናለሁ፤ ለአንተም ሆነ ለእርሷ የተገባውን እጅ መንሻ አቀርባለሁ”። 55ንጉሥ ጰጠሎሜዮስ እንዲህ ሲል መለሰለት፦ “ወደ አባትህ አገር የገባህበትና በንጉሣዊ ዙፋን ላይ የተቀመጥህበት ቀን የተባረከ ነው፤ 56አሁንም በጽሑፉ የገለጽህልኝን አደርግልሃለሁ፤ ግን እንድነነጋገር ወደ ጰጠሎማይዳ ወጥተህ እንድንገናኝ ይሁን፤ እንዳልኸው አማችህ እሆናለሁ።” 57ጰጠሎሜዮስ ከሴት ልጁ ከኪሊዮጳጥራ ጋር ከግብጽ ተነሥቶ በመቶ ስልሳ ሁለት ዓመተ ዓለም ወደ ጰጠሎማይዳ መጣ፤ 58ንጉሥ እስክንድርም ጰጠሎሜዮስን ለመቀበል መጣ፤ ለነገሥታት መደረግ እንደሚገባው ጰጠሎሜዮስ ልጁን ኪሊዮጳጥራን ሰጠውና በጰጠሎማይዳ ታላቅ በዓል አደረገ። 59ንጉሥ እስክንድር ለዮናታን መጥቶ እንደገናኘው ጻፈለት። 60ዮናታን በታላቅ ክብር ወደ ጰጠሎማይዳ ሄደ፤ ከሁለቱ ነገሥታት ጋር ተገናኘ፤ ለእነርሱና ለወዳጆቻቸውም ብርና ወርቅ፤ ብዙ እጅ መንሻም አቀረበ። 61ሃይማኖት የሌላቸውና ሕግን የማያከብሩ የእስራኤል በሽታ የሆኑ ሰዎች በእርሱ ላይ ተነሡበትና በንጉሡ ፊት ቀርበው ከሰሱት፤ ንጉሡ ግን ክሳቸውን አልተቀበላቸውም። 62እንዲያውም የዮናታንን ልብስ አውልቀው ከፋይ እንዲያለብሱት አዘዘ፤ እንዲሁም ተደረገ። 63ንጉሡ በአጠገቡ አስቀመጠውና ሹማምንቱን እንዲህ አላቸው፤ “ከእርሱ ጋር አብራችሁ ወደ ከተማ መሀል ሂዱ፤ በምንም ዓይነት ምክንያት ማንም እንዳያስቸግረው አሳውጁለት”። 64በንጉሡ አዋጅ መሠረት የተሰጠውን ክብርና የለበሰውን ከፋይ ባዩ ጊዜ ሐሜተኞቹ ሁሉ ሸሽተው ሄዱ። 65ንጉሡ ክሱ ከመጀመሪያዎቹ ወዳጆቹ መካከል እንዲጻፍ አደረገው፤ የጦር መሪና የክፍለ ሀገር አስተዳዳሪ አደረገው፤ 66ዮናታን በሰላም፤ በደስታ ወደ ኢየሩሳሌም ተመለሰ።
ዳግማዊ ዲሜጥሮስ፥ የቀለሶርያ ገዥ አጶሎንዮስ በዮናታን ድል መመታት
67በመቶ ሰላሳ አምስት ዓመተ ዓለም ዲሜጥሮስ (2ኛው) የዲሜጥሮስ (1ኛው) ልጅ ከቀርጤስ ወደ አባቶቹ አገር መጣ። 68ንጉሥ እስክንድር ይህን በሰማ ጊዜ በጣም አዝኖ ወደ አንጾኪያ ተመልሶ መጣ፤ 69አጶሎንዮስ የቀለሶርያ አስተዳዳሪ እንዲሆን ዲሜጥሮስ አጸናለት፤ አጶሎንዮስም ብዙ ሠራዊት ሰብስቦ በያምንያ አጠገብ መጣና ሠፈረ፤ ወደ ሊቀ ካህናቱ ወደ ዮናታንም እንዲህ ሲል ላከ፤ 70“በእኛ ላይ የተነሣህ በእውነት አንተ ብቻ ነህ፤ በአንተ ምክንያት እነሆ እኔ መሳቂያና ማላገጫ ሆኛለሁ፤ አንተ በተራራ ላይ ሆነህ ሥልጣንህን በእኛ ላይ ደረረግኸው ስለምንድነው? 71በሠራዊትህ የምትተማመን ከሆንህና ከእንግዲህ አሁን ወደ ሜዳው ውረድ፤ እዚያ እኔና አንተ እንፈታተናለን፤ ምክንያቱም የከተማዎቹ ኃይል ከእኔ ጋር ነው። 72እኔ ማን መሆኔንና የሚረዱኝም ሰዎች ማን መሆናቸውን ጠይቀህ ተረዳ፤ ከዚህ ቀደም አባቶችህ በገዛ አገራቸው ላይ ሁለት ጊዜ ተሸንፈዋልና፤ እናንተም በፊታችን መቆም እንደማትችሉ ትሰማለህ። 73ግን ድንጋይ ወይም ዓለት እንዲሁም ማምልጫም በሌለበት ሜዳ ላይ ፈረሰኛውንና እጅግ ብዙ የሆነውን ሠራዊቴን መቋቋም አትችልም”።
74ዮናታን የአጶሎንዮስን ቃል በሰማ ጊዜ መንፈሱ ተቆጣ፤ ተነሣሳም፤ ዐሥር ሺህ ሰዎች መረጠና ከኢየሩሳሌም ወጥቶ ሄደ፤ ወንድሙ ስምንም እርሱን ለማገዝ ተከትሎት ሄደ። 75ከኢዮጴ ወጣ ብሎ ሠረፈ፤ የአጶሎንዮስ ወታደሮች በከተማዋ ስለ ነበሩ ነዋሪዎቹ በሮቹን ዘጉባቸው፤ እነዮናታን ውጊያ ጀመሩ። 76የከተማይቱ ነዋሪዎችም በፍርሃት ተይዘው በሮቹን ከፈቱላቸው፤ ዮናታንም ኢዮጴን ያዘ። 77አጶሎንዮስ ይህን በሰማ ጊዜ ሦስት ሺህ ፈረሰኞችና ብዙ ሠራዊት አሰለፈና አገሩን ሰንጥቆ የሚያልፍ መስሎ ወደ አዛጦን አመራ፤ ግን ብዛት ባለው በፈረሰኛው ጦር ተማምኖ በዚያኑ ጊዜ ወደ ሜዳው ዘልቆ ሄደ። 78ዮናታን እስከ አዛጦን ስለተከተለው ወታደሮቻቸው በዚያው ውጊያ ጀመሩ። 79አጰሎንዮስ ከነዮናታን በስተ ኋላ አንድ ሺህ ፈረሰኞች በድብቅ ትቶ ነበር። 80ዮናታን እንዲህ ያለ ወጥመድ በስተ ኋላው መኖሩን አወቀ፤ ፈረሰኞቹ የእርሱን ሠራዊት ከበው ከጠዋት ጀምሮ እስከ ማታ ድረስ ቀስቶቻቸውን ወረወሩባቸው። 81ዮናታን ወታደሮች እርሱ በሚያስተላልፍላቸው ትእዛዝ መሠረት ጦሩን በደንብ ተቋቋሙ፤ ፈረሰኞቹም ደከሙ። 82በዚያን ጊዜ ስምዖን ወታደሮቹን ይዞ እግረኛውን ክፍለ ጦር ወጋ፤ ፈረሰኛው ጦር ደከመና ጠላቶች በስምዖን ተሸነፉና ሸሹ። 83ፈረሰኛው ጦር በሜዳው ተበታተነ፤ ሸሽተው ወደ አዛጦን ደረሱና ራሳቸውን ለማዳን ወደ ጣዖታቸው ወደ ዳጐን ቤት ገቡ። 84ዮናታን አዛጦንንና በአካባቢዋ ያሉትን ከተሞች በእሳት አጋየ፤ ዘረፋቸው የዳጐንን ቤትና በዚያ ውስጥ ተጠግተው የሚገኙትን በእሳት አቃጠለ። 85በጠቅላላው ስምንት ሺህ ሰዎች በሰይፍ ወይም በእሳት ሞተዋል። 86ዮናታንም ከእዚያ በመሄድ በአስቃሉን አጠገብ ሠፈረ፤ ነዋሪዎቹ በታላቅ ክብር ሊቀበሉት ወጡ፤ 87ከእዚህ በኋላ ዮናታንና የእርሱ ሰዎች ብዙ ምርኮ ይዘው ወደ ኢየሩሳሌም ተመለሱ። 88ንጉሥ እስክንድር ይህን ሁሉ በሰማ ጊዜ ለዮናታን በክብር ላይ ክብር ጨመረለት፤ 89ለንጉሥ ዘመዶች መስጠት የተለመደውን የወርቅ መቆለፊያ ላከለት፤ አቃሮንንና አካባቢዋንም ጭምር በባለቤትነት ሰጠው።

Highlight

Share

Copy

None

Want to have your highlights saved across all your devices? Sign up or sign in