1ኛ መጽሐፈ ዜና መዋዕል 21
21
ቈጠራና መቅሰፍት
1ሰይጣንም በእስራኤል ላይ ተነሣ፥ እስራኤልንም እንዲቈጥር ዳዊትን አነሣሣው። 2ዳዊትም ኢዮአብንና የሕዝቡን አለቆች፦ “ሂዱ፥ ከቤር-ሳቤህ ጀምሮ እስከ ዳን ድረስ እስራኤልን ቁጠሩ፥ ድምራቸውንም እንዳውቅ ተመልሳችሁ አስታውቁኝ” አላቸው። 3ኢዮአብም አለ፦ “ጌታ ሕዝቡን በአሁኑ ላይ መቶ እጥፍ ይጨምር፤ ጌታዬ ንጉሥ ሆይ! ሁሉ የጌታዬ ባርያዎች አይደሉምን? ይህን ነገር ጌታዬ ለምን ይሻል? በእስራኤል ላይ በደል ስለምን ያመጣል?” 4ነገር ግን የንጉሡ ቃል በኢዮአብ ላይ አሸነፈ፤ ኢዮአብም ወጥቶ በእስራኤል ሁሉ ላይ ተዘዋወረ፥ ወደ ኢየሩሳሌምም ተመለሰ። 5ኢዮአብም የቈጠራቸውን የሕዝቡን ድምር ለዳዊት ሰጠ፤ ከእስራኤልም ሁሉ አንድ ሚሊዮን አንድ መቶ ሺህ ሰይፍ የሚመዝዙ ሰዎችን አገኘ፤ ከይሁዳም አራት መቶ ሰባ ሺህ ሰይፍ የሚመዝዙ ሰዎችን አገኘ። 6የንጉሡ ትእዛዝ ግን በኢዮአብ ዘንድ የተጠላ ነበረና ሌዊና ብንያም ከእነርሱ ጋር አልተቈጠሩም።
7ከዚህም ነገር የተነሣ እግዚአብሔር ተቈጣ፥ እስራኤልንም ቀሠፈ። 8ዳዊትም እግዚአብሔርን፦ “ይህን በማድረግ እጅግ በድያለሁ፤ አሁን ግን ይህን ባለማወቅ አድርጌአለሁና የባርያህን ኃጢአት እንድታስወግድ እለምንሃለሁ” አለው። 9ጌታም ለዳዊት ባለ ራእይ ለጋድ፦ 10“ሂድ፥ ለዳዊት፦ ‘ጌታ እንዲህ ይላል፦ ሦስቱን ነገሮች በፊትህ አኖራለሁ፤ በአንተ ላይ እንዳደርግብህ ከእነርሱ አንዱን ምረጥ’ ብለህ ንገረው” ብሎ ተናገረው። 11ጋድም ወደ ዳዊት መጥቶ እንዲህ አለው፦ “ጌታ እንዲህ ይላል፦ ‘የምትወድደውን ምረጥ፤ 12የሦስት ዓመት ራብ፥ ወይም ሦስት ወር የጠላቶችህ ሰይፍ እንዲያገኝህ ከጠላቶችህም ፊት እንድትሰደድ፥ ወይም ሦስት ቀን የጌታ ሰይፍ ቸነፈርም በምድር ላይ እንዲሆን፥ የጌታም መልአክ በእስራኤል ምድር ሁሉ ጥፋትን እንዲያመጣ ምረጥ፤’ ለላከኝ ምን መልስ እንደምሰጥ አሁን ወስን።” 13ዳዊትም ጋድን፦ “እጅግ ተጨንቄአለሁ፤ ምሕረቱ ብዙ ነውና በጌታ እጅ ልውደቅ፤ በሰው እጅ ግን አልውደቅ” አለው።
14ጌታም በእስራኤል ላይ ቸነፈርን ሰደደ፤ ከእስራኤልም ሰባ ሺህ ሰዎች አለቁ። 15እግዚአብሔርም ለማጥፋት ወደ ኢየሩሳሌም መልአክን ላከ፤ ሊያጠፋትም በቀረበ ጊዜ ጌታ አይቶ ስለ ክፉው ነገር ተፀፀተ፥#21፥15 ክፉ ከማድረግ ተመለሰ፤ የሚያጠፋውንም መልአክ፦ “በቃህ፤ አሁን እጅህን መልስ” አለው። የጌታም መልአክ በኢያቡሳዊው በኦርና አውድማ አጠገብ ቆሞ ነበር። 16ዳዊትም ዐይኖቹን አነሣ፤ የጌታ መልአክ በምድርና በሰማይ መካከል ቆሞ፥ የተመዘዘም ሰይፍ በእጁ ሆኖ ወደ ኢየሩሳሌም ተዘርግቶ አየ። ዳዊትም ሽማግሌዎችም ማቅ ለብሰው በግምባራቸው ተደፍተው ሰገዱ። 17ዳዊትም እግዚአብሔርን እንዲህ አለው፦ “ሕዝቡ እንዲቈጠር ያዘዝሁ እኔ አይደለሁምን? የበደልሁና ክፉ የሠራሁ እኔ ነኝ፤ እነዚህ በጎች ግን ምን አድርገዋል? አቤቱ አምላኬ ሆይ! እጅህ በእኔና በአባቴ ቤት ላይ ይሁን፥ ነገር ግን መቅሰፍት በሕዝብህ ላይ አይሁን።”
የንጉሥ ዳዊት መሠውያና መሥዋዕት
18የጌታም መልአክ ዳዊት ወጥቶ በኢያቡሳዊው በኦርና አውድማ ላይ ለጌታ መሠዊያ እንዲሠራ ለዳዊት እንዲነግረው ጋድን አዘዘው። 19ዳዊትም በጌታ ስም እንደ ተናገረው እንደ ጋድ ቃል ወጣ። 20ኦርናም ዘወር ብሎ መልአኩን አየ፥ ከእርሱም ጋር የነበሩ አራቱ ልጆች ተሸሸጉ፤ ኦርናም ስንዴ ያበራይ ነበር። 21ዳዊትም ወደ ኦርና በመጣ ጊዜ ኦርና ቀና ብሎ ተመለከተ ዳዊትንም አየ፤ ከአውድማውም ወጥቶ ዳዊትን እጅ ሊነሣ በምድር ላይ ተደፍቶ ሰገደ። 22ዳዊትም ኦርናን፦ “በላዩ ለጌታ መሠዊያ እንድሠራ ይህን የአውድማ ስፍራ ስጠኝ፤ ሙሉ ዋጋ ልክፈልና ስጠኝ፤ መቅሰፍቱም ከሕዝቡ ይከለከላል” አለው። 23ኦርናም ዳዊትን እንዲህ አለው፦ “ለአንተ ውሰደው፥ ጌታዬ ንጉሡም ደስ የሚያሰኘውን ያድርግ፤ እነሆ፥ ለሚቃጠለው መሥዋዕት በሬዎቹን፥ ለማገዶም የአውድማውን መውቅያ፥ ለእህልም ቁርባን ስንዴውን እሰጥሃለሁ፤ ሁሉን እሰጣለሁ።” 24ንጉሡም ዳዊት ኦርናን፦ “አይደለም፥ ነገር ግን የአንተ የሆነውን ለጌታ አምጥቼ የሚቃጠል መሥዋዕት አድርጌ በከንቱ አላቀርብምና በሙሉ ዋጋ እገዛዋለሁ” አለው። 25ዳዊትም ስለ ስፍራው ስድስት መቶ ሰቅል ወርቅ በሚዛን ለኦርና ሰጠው። 26ዳዊትም በዚያ ለጌታ መሠዊያ ሠራ፥ የሚቃጠለውን መሥዋዕትና የአንድነቱን መሥዋዕት አቀረበ፥ ጌታንም ጠራ፤ ጌታም ከሰማይ የሚቃጠለው መሥዋዕት በሚቀርብበት መሠዊያ ላይ በእሳት መለሰለት። 27ጌታም መልአኩን አዘዘው፥ ሰይፉንም በአፎቱ ከተተው።
ለቤተ መቅደሱ የተመረጠ ቦታ
28በዚያን ጊዜ ጌታ በኢያቡሳዊው በኦርና አውድማ እንደ መለሰለት ዳዊት ባየ ጊዜ፥ በዚያ መሥዋዕት ሠዋ። 29ሙሴም በምድረ በዳ የሠራት የጌታ ማደሪያና ለሚቃጠል መሥዋዕት የሚሆነው መሠዊያ በዚያን ጊዜ በገባዖን ባለው በኮረብታው መስገጃ ነበሩ። 30ዳዊት ግን የጌታን መልአክ ሰይፍ ስለ ፈራ እግዚአብሔርን ለመጠየቅ ወደዚያ መሄድ አልቻለም።
Currently Selected:
1ኛ መጽሐፈ ዜና መዋዕል 21: መቅካእኤ
Highlight
Share
Copy
Want to have your highlights saved across all your devices? Sign up or sign in