YouVersion Logo
Search Icon

1ኛ መጽሐፈ ዜና መዋዕል 15

15
ታቦቱ ወደ ኢየሩሳሌም መመለሱ
1ዳዊትም በራሱ ከተማ ላይ ለራሱ ቤቶችን ሠራ፤ ለእግዚአብሔርም ታቦት ስፍራ አዘጋጀ፥ ድንኳንም ተከለለት። 2#ዘዳ. 10፥8።በዚያን ጊዜም ዳዊት እንዲህ አለ፦ “የእግዚአብሔርን ታቦት እንዲሸከሙ፥ ለዘለዓለሙም እንዲያገለግሉት ጌታ ከመረጣቸው ከሌዋውያን በቀር ማንም የጌታን ታቦት ሊሸከም አይገባውም።” 3ዳዊትም ወዳዘጋጀለት ስፍራ የጌታን ታቦት ለማምጣት እስራኤልን ሁሉ ወደ ኢየሩሳሌም ሰበሰበ። 4ዳዊትም የአሮንን ልጆችና ሌዋውያን ሰበሰበ። 5ከቀዓት ልጆች፤ ከመቶ ሀያ ወንድሞቹ ጋር አለቃው ኡርኤል ነበር፤ 6ከሜራሪ ልጆች፤ ከሁለት መቶ ሀያ ወንድሞቹ ጋር አለቃው ዓሣያ ነበር፤ 7ከጌድሶን ልጆች፤ ከመቶ ሠላሳ ወንድሞቹ ጋር አለቃው ኢዮኤል ነበር፤ 8ከኤሊጻፋን ልጆች፤ ከሁለት መቶ ወንድሞቹ ጋር አለቃው ሸማያ ነበር፤ 9ከኬብሮን ልጆች፤ ከሰማንያ ወንድሞቹ ጋር አለቃው ኤሊኤል ነበር፤ 10ከዑዝኤል ልጆች፤ ከመቶ ዐሥራ ሁለት ወንድሞቹ ጋር አለቃው አሚናዳብ ነበር። 11ዳዊትም ካህናቱን ሳዶቅንና አብያታርን፥ ሌዋውያንንም ኡርኤልን፥ ዓሣያን፥ ኢዮኤልን፥ ሸማያን፥ ኤሊኤልን፥ አሚናዳብንም ጠራቸው፤ 12እነርሱንም እንዲህ አላቸው፦ “እናንተ የሌዋውያን አባቶች ቤቶች አለቆች ናችሁ፤ ወዳዘጋጀሁለት ስፍራ የእስራኤልን አምላክ የጌታን ታቦት እንድታመጡ እናንተና ወንድሞቻችሁ ተቀደሱ። 13ቀድሞም አልተሸከማችሁትምና፥ እንደ ሥርዓቱም አልፈለግነውምና ጌታ አምላካችን በመካከላችን ቊጣውን አወረደ።” 14የእስራኤልንም አምላክ የጌታን ታቦት ለማምጣት ካህናቱና ሌዋውያኑ ተቀደሱ። 15#ዘፀ. 25፥14።ሙሴም እንዳዘዘው እንደ ጌታ ቃል የሌዋውያን ልጆች የእግዚአብሔርን ታቦት በትከሻቸው ላይ በመሎጊያዎቹ ተሸከሙ።
16ዳዊትም በዜማ ዕቃ በመሰንቆና በበገና በጸናጽልም እንዲያዜሙ፥ ድምፃቸውንም በደስታ ከፍ እንዲያደርጉ መዘምራኑን ወንድሞቻቸውን እንዲሾሙ ለሌዋውያን አለቆች ተናገረ። 17ሌዋውያኑም የኢዮኤልን ልጅ ኤማንን፥ ከወንድሞቹም የበራክያን ልጅ አሳፍን፥ ከወንድሞቻቸውም ከሜራሪ ልጆች የቂሳን ልጅ ኤታንን ሾሙ፤ 18ከእነርሱም ጋር በሁለተኛው ደረጃ ያሉትን ወንድሞቻቸውን ዘካርያስን፥ ቤንን፥ ያዝኤልን፥ ሰሚራሞትን፥ ይሒኤልን፥ ዑኒን፥ ኤልያብን፥ በናያስን፥ መዕሤያን፥ መቲትያን፥ ኤሊፍሌሁን፥ ሚቅኔያን፥ ደጁንም የሚጠብቁትን ዖቤድ-ኤዶምንና ይዒኤልን ሾሙ። 19መዘምራንም የነበሩት ኤማንና አሳፍ ኤታምንም የናሱን ጸናጽል ድምፅ ከፍ አድርገው ያሰሙ ነበር። 20ዘካርያስ፥ ዓዝዔል፥ ሰሚራሞት፥ ይሒኤል፥ ዑኒ፥ ኤልያብ፥ መዕሤያ፥ በናያስ በመሰንቆ ምሥጢር ነገር ያዜሙ ነበር። 21መቲትያ፥ ኤልፍሌሁ፥ ሚቅኔያ፥ ዖቤድ-ኤዶም፥ ይዒኤል፥ ዓዛዝያ ስምንት አውታር ባለው በገና ይዘምሩ ነበር። 22የሌዋውያኑም አለቃ ክናንያ ዜማን አዋቂ ስለ ነበር ዜማውን እንዲመራ ተሾሞ ነበር። 23በራክያና ሕልቃናም የታቦቱን እልፍኝ ጠባቂዎች ነበሩ። 24ካህናቱም ሰበኒያ፥ ኢዮሣፍጥ፥ ናትናኤል፥ ዓማሣይ፥ ዘካርያስ፥ በናያስ፥ አልዓዛር በእግዚአብሔር ታቦት ፊት መለከት ይነፉ ነበር። ዖቤድ-ኤዶምና ይሒያም የታቦቱን እልፍኝ ጠባቂዎች ነበሩ።
25ዳዊትም፥ የእስራኤልም ሽማግሌዎች፥ የሻለቆችም የጌታን የቃል ኪዳኑን ታቦት ከዖቤድ-ኤዶም ቤት በደስታ ለማምጣት ሄዱ። 26የጌታንም ቃል ኪዳን ታቦት የተሸከሙትን ሌዋውያንን እግዚአብሔር ስለረዳቸው ሰባት በሬዎችና ሰባት አውራ በጎች ሰዉ። 27ዳዊትም፥ ታቦቱንም የተሸከሙ ሌዋውያን ሁሉ፥ መዘምራኑም፥ የመዘምራኑም አለቃ ከናንያ የጥሩ በፍታ ቀሚስ ለብሰው ነበር፤ ዳዊትም ኤፉድ ያለበት በፍታ ለብሶ ነበር። 28እንዲሁ እስራኤል ሁሉ ሆ እያሉ፥ ቀንደ መለከትና እምቢልታ እየነፉ፥ ጸናጽልና መሰንቆም በገናም እየመቱ፥ የጌታን የቃል ኪዳን ታቦት አመጡ።
29የጌታም ቃል ኪዳን ታቦት ወደ ዳዊት ከተማ በደረሰ ጊዜ የሳኦል ልጅ ሜልኮል በመስኮት ሆና ተመለከተች፤ ንጉሡም ዳዊት ሲያሸበሽብና ሲዘል አይታ በልብዋ ናቀችው።

Highlight

Share

Copy

None

Want to have your highlights saved across all your devices? Sign up or sign in