1ኛ መጽሐፈ ዜና መዋዕል 14
14
የዳዊት መንግሥት በኢየሩሳሌም መጽናቱ
1የጢሮስም ንጉሥ ኪራም ለዳዊት ቤት እንዲሠሩለት መልእክተኞችን የዝግባ እንጨትንም ጠራቢዎችንም አናጢዎችንም ወደ ዳዊት ላከ። 2ስለ ሕዝቡም ስለ እስራኤል መንግሥቱ እጅግ ከፍ ብሏልና ጌታ በእስራኤል ላይ ንጉሥ አድርጎ እንዳጸናው ዳዊት አወቀ።
3ዳዊትም በኢየሩሳሌም ሚስቶችን ጨምሮ አገባ ሌሎችንም ወንዶችና ሴቶችን ልጆች ወለደ። 4በኢየሩሳሌምም የወለዳቸው የልጆቹ ስም፤ ሳሙስ፥ ሶባብ፥ ናታን፥ ሰሎሞን፥ 5ኢያቤሐር፥ ኤሊሱዔ፥ ኤሊፋላት፥ 6ኖጋ፥ ናፌቅ፥ ያፍያ፥ 7ኤሊሳማ፥ ኤሊዳሄ፥ ኤሊፋላት ተብለው ይጠሩ ነበር።
ፍልስጥኤማውያን መሸነፋቸው
8ፍልስጥኤማውያንም ዳዊት በእስራኤል ሁሉ ላይ ንጉሥ ሆኖ እንደተቀባ ሰሙ፥ ፍልስጥኤማውያንም ሁሉ ዳዊትን ሊፈልጉ ወጡ፤ ዳዊትም በሰማ ጊዜ እነርሱን ሊወጋቸው ወጣ። 9ፍልስጥኤማውያንም መጥተው በራፋይም ሸለቆ አደጋ ጣሉ። 10ዳዊትም፦ “ወደ ፍልስጥኤማውያን ልውጣን? በእጄስ አሳልፈህ ትሰጣቸዋለህን?” ብሎ እግዚአብሔርን ጠየቀ። ጌታም፦ “በእጅህ አሳልፌ እሰጣቸዋለሁና ውጣ” አለው። 11ወደ በኣል-ፐራሲምም ወጡ፥ በዚያም ዳዊት ድል ነሣቸው። ዳዊትም፦ “ግድቡን አፍርሶ እንደሚወጣ ጎርፍ እግዚአብሔር ጠላቶቼን በእጄ አፈረሳቸው” አለ። ስለዚህም የዚያን ስፍራ ስም በኣል-ፐራሲም ብለው ጠሩት። 12አማልክቶቻቸውንም በዚያ ተዉ፤ ዳዊትም አዘዘ፥ በእሳትም አቃጠሉአቸው።
13ዳግመኛም ፍልስጥኤማውያን በሸለቆው አደጋ ጣሉ። 14ዳዊትም እንደገና እግዚአብሔርን ጠየቀ፤ እግዚአብሔርም እንዲህ አለው፦ “ከእነርሱ ዞረህ በሾላው ዛፍ ፊት ለፊት ግጠማቸው እንጂ ወደ እነርሱ አትውጣ። 15በሾላውም ዛፍ አናት የሽውሽውታ ድምፅ ስትሰማ የፍልስጥኤማውያንን ጭፍራ ሊመታ እግዚአብሔር በፊትህ ይወጣልና በዚያን ጊዜ ወደ ውግያ ውጣ።” 16ዳዊትም እግዚአብሔር እንዳዘዘው አደረገ፤ ከገባዖንም ጀምሮ እስከ ጌዝር ድረስ የፍልስጥኤማውያንን ጭፍራ መቱት። 17የዳዊትም ዝና በየአገሩ ሁሉ ተሰማ፤ መፈራቱንም ጌታ በአሕዛብ ሁሉ ዘንድ አደረገው።
Currently Selected:
1ኛ መጽሐፈ ዜና መዋዕል 14: መቅካእኤ
Highlight
Share
Copy
Want to have your highlights saved across all your devices? Sign up or sign in