የዮሐንስ ራእይ 21
21
አዲሱ ሰማይና አዲሲቱ ምድር
1ከዚህ በኋላ አዲስ ሰማይና አዲስ ምድር አየሁ፤ የመጀመሪያው ሰማይና የመጀመሪያይቱ ምድር አልፈው ነበር፤ ባሕርም ከእንግዲህ ወዲህ አይኖርም። #ኢሳ. 65፥17፤ 66፥22፤ 2ጴጥ. 3፥13። 2ቅድስቲቱ ከተማ፥ አዲሲቱ ኢየሩሳሌም፥ ለባልዋ እንዳጌጠች ሙሽራ ተዘጋጅታ ከሰማይ ከእግዚአብሔር ዘንድ ስትወርድ አየሁ፤ #ኢሳ. 52፥1፤ 61፥10፤ ራዕ. 3፥12። 3እንዲህም የሚል ከፍተኛ ድምፅ ከዙፋኑ ሲወጣ ሰማሁ፤ “እነሆ! የእግዚአብሔር ማደሪያ ከሰዎች ጋር ነው፤ ከእነርሱም ጋር ይኖራል፤ እነርሱም የእርሱ ሕዝብ ይሆናሉ። እግዚአብሔር ራሱ ከእነርሱ ጋር ይሆናል፤ አምላካቸውም ይሆናል፤ #ሕዝ. 37፥27፤ ዘሌ. 26፥11-12። 4እንባን ሁሉ ከዐይናቸው ላይ ይጠርጋል፤ የቀድሞው ሥርዓት ስላለፈ ሞት ወይም ሐዘን ወይም ለቅሶ ወይም ሥቃይ ከእንግዲህ ወዲህ አይኖርም።” #ኢሳ. 25፥8፤ 35፥10፤ 65፥19።
5በዙፋኑ ላይ የተቀመጠውም “እነሆ! እኔ ሁሉን ነገር አዲስ አደርጋለሁ!” አለ፤ ቀጥሎም “ይህ ቃል የታመነና እውነት ስለ ሆነ ጻፍ” አለኝ። 6ከዚህም በኋላ እንዲህ አለኝ፤ “ተፈጸመ! አልፋና ዖሜጋ፥ የመጀመሪያውና የመጨረሻው እኔ ነኝ፤ ለተጠማ ከሕይወት ውሃ ምንጭ ያለ ምንም ዋጋ በነጻ እሰጠዋለሁ፤ #ኢሳ. 55፥1። 7ድል የሚነሣ ይህን ይወርሳል፤ እኔ አምላክ እሆነዋለሁ፤ እርሱም ልጄ ይሆናል፤ #2ሳሙ. 7፥14፤ መዝ. 89፥26-27። 8ነገር ግን ፈሪዎች፥ እምነተ ቢሶች፥ ርኩሶች፥ ነፍሰ ገዳዮች፥ አመንዝሮች፥ አስማተኞች፥ ጣዖት አምላኪዎች፥ ውሸታሞች ሁሉ ዕጣ ክፍላቸው በዲን በሚቃጠለው በእሳት ባሕር ውስጥ ይሆናል፤ ይህም ሁለተኛው ሞት ነው።”
አዲሲቱ ኢየሩሳሌም
9የመጨረሻዎቹ ሰባት መቅሠፍቶች የሞሉባቸውን ሰባቱን ጽዋዎች ከያዙት ከሰባቱ መላእክት አንዱ መጥቶ “ና! የበጉ ሚስት የሆነችውን ሙሽራይቱን አሳይሃለሁ” አለኝ። 10በመንፈስም ወደ አንድ ትልቅ ረጅም ተራራ ወሰደኝና ቅድስቲቱ ከተማ ኢየሩሳሌም ከእግዚአብሔር ዘንድ ከሰማይ ስትወርድ አሳየኝ፤ #ሕዝ. 40፥2። 11በእግዚአብሔር ክብር ታበራ ነበር፤ የብርሃንዋም ድምቀት እጅግ እንደ ከበረ ድንጋይ፥ እንደ ብርሌ የጠራ የእያሰጲድ ዕንቊ ነበረ፤ 12ዐሥራ ሁለት ደጃፎች ያሉት ታላቅና ረጅም የግንብ አጥር ነበራት፤ በዐሥራ ሁለቱም ደጃፎች ዐሥራ ሁለት መላእክት ቆመው ይጠብቁ ነበር፤ በደጃፎቹም ላይ የዐሥራ ሁለቱ የእስራኤል ነገዶች ስሞች ተጽፈውባቸው ነበር። 13በምሥራቅ ሦስት ደጃፎች በሰሜን ሦስት ደጃፎች፥ በደቡብ ሦስት ደጃፎች፥ በምዕራብ ሦስት ደጃፎች ነበሩ። #ሕዝ. 48፥30-35። 14የከተማይቱ የግንብ አጥር ዐሥራ ሁለት መሠረቶች ነበሩት፤ በመሠረቶቹም ላይ የዐሥራ ሁለቱ የበጉ ሐዋርያት ስሞች ተጽፈው ነበር፤ 15የተናገረኝም መልአክ ከተማይቱንና ደጃፎችዋን፥ የግንቡንም አጥር የሚለካበት የወርቅ ዘንግ ነበረው፤ #ሕዝ. 40፥3። 16ከተማይቱም ርዝመትዋና ስፋትዋ እኩል የሆነ የአራት ማእዘን ቅርጽ ነበራት፤ መልአኩ ከተማይቱን በመለኪያው ዘንግ ለካትና ርዝመትዋ ሁለት ሺህ አራት መቶ ኪሎ ሜትር ያኽል ሆነ፤ ስፋትዋና ከፍታዋም ያንኑ ያኽል ሆነ፤ 17መልአኩ የግንቡን አጥር ለካ፤ መልአኩ በሚለካበት በታወቀው መለኪያ ልክ ሰባ ሁለት ሜትር ያኽል ሆነ፤ 18ግንቡም የተሠራው ከኢያሰጲድ ነበረ፤ ከተማይቱም እንደ መስተዋት በጠራ በንጹሕ ወርቅ የተሠራች ነበረች፤ #ኢሳ. 54፥11-12። 19የከተማይቱ ግንብ መሠረቶች በልዩ ልዩ የከበረ ድንጋይ ያጌጡ ነበሩ፤ የመጀመሪያው መሠረት ኢያሰጲድ ነበረ፤ ሁለተኛው ሰንፔር፥ ሦስተኛው ኬልቄዶን፥ አራተኛው መረግድ፥ 20አምስተኛው ሰርዶንክስ፥ ስድስተኛው ሰርድዮን፥ ሰባተኛው ክርስቲሎቤ፥ ስምንተኛው ቢረሌ፥ ዘጠነኛው ወራውሬ፤ ዐሥረኛው ክርስጵራስስ፥ ዐሥራ አንደኛው ያክንት፥ ዐሥራ ሁለተኛው አሜቴስጢኖስ ነበረ። 21ዐሥራ ሁለቱም ደጃፎች ዐሥራ ሁለት ዕንቆች ነበሩ፤ እያንዳንዱ ደጃፍ ከአንድ ዕንቊ የተሠራ ነበረ፤ የከተማይቱም መንገድ እንደ መስተዋት ብርሃን ከሚያስተላልፍ ከንጹሕ ወርቅ የተሠራ ነበረ።
22ሁሉን የሚችል ጌታ አምላክና በጉ የእርስዋ መቅደስ ስለ ሆኑ በከተማይቱ ውስጥ መቅደስ አላየሁም፤ 23የእግዚአብሔር ክብር ስለሚያበራላትና በጉ መብራትዋ ስለ ሆነ ከተማይቱ ፀሐይ ወይም ጨረቃ እንዲያበሩላት አያስፈልጋትም። #ኢሳ. 60፥19-20። 24ሕዝቦች በብርሃንዋ ይመላለሳሉ፤ የምድር ነገሥታትም ክብራቸውን ወደ እርስዋ ያመጣሉ፤ #ኢሳ. 60፥3። 25በዚያች ከተማ ሌሊት ስለሌለ ደጃፎችዋ በማንኛውም ቀን አይዘጉም። 26የመንግሥታት ገናናነትና ክብር ወደ እርስዋ ይገባሉ፤ #ኢሳ. 60፥11። 27ጸያፍ የሆነ ነገር ከቶ ወደ እርስዋ አይገባም፤ ርኲሰትን የሚያደርግና ውሸት የሚናገር ከቶ ወደ እርስዋ አይገባም፤ ወደ እርስዋ የሚገቡ ስሞቻቸው በበጉ የሕይወት መጽሐፍ የተጻፉ ብቻ ናቸው። #ኢሳ. 52፥1፤ ሕዝ. 44፥9።
Currently Selected:
የዮሐንስ ራእይ 21: አማ05
Highlight
Share
Copy
Want to have your highlights saved across all your devices? Sign up or sign in
© The Bible Society of Ethiopia, 2005
© የኢትዮጵያ መጽሐፍ ቅዱስ ማኅበር፥ 1997