መጽሐፈ መዝሙር 7
7
ስለ ትክክለኛ ፍትሕ የቀረበ ጸሎት
1እግዚአብሔር አምላኬ ሆይ!
የምተማመንብህ መማጸኛዬ አንተ ነህ፤
ከሚያሳድዱኝ ሁሉ ታደገኝ፤ አድነኝም።
2ካላዳንከኝ ግን እንደ አንበሳ ነጥቀው
ማንም ሊታደገኝ ወደማይችል ስፍራ ይወስዱኛል፤
ሰባብረውም ያደቁኛል።
3-4እግዚአብሔር አምላኬ ሆይ!
አንድን ሰው እንኳ በድዬ ከሆነ፥
ለወዳጄ በመልካም ፈንታ ክፉ መልሼ ከሆነ፥
ጠላቴን ያለ ምክንያት እንዲሁ ጐድቼው ከሆነ፥
ከነዚህ ሁሉ ነገሮች አንዱን እንኳ አድርጌ ከሆነ፥
5ጠላቴ አሳዶ ይያዘኝ!
እስከ ሞት ድረስ ይርገጠኝ
በአቧራም ላይ ጥሎ ክብር ያሳጣኝ!
6እግዚአብሔር ሆይ! በቊጣህ ተነሥ፤
የጠላቶቼንም ቊጣ አስወግድ፤
ፍርድ እንዲስተካከል ባዘዝከው መሠረት
እኔን ለመርዳት ተነሥ፤
7ሕዝቦችን ሁሉ በዙሪያህ ሰብስብ፤
ከላይም ሆነህ ንገሥ።
8እግዚአብሔር በሕዝቦች ላይ ይፈርዳል፤
ጌታ ሆይ! እንደ እውነተኛነቴና እንደ ታማኝነቴ ፍረድልኝ።
9ኅሊናንና ልብን የምትመረምር ጻድቅ አምላክ ሆይ!
የክፉዎችን ዐመፅ አጥፋ፤
የጻድቃንንም ደኅንነት ጠብቅ። #ራዕ. 2፥23።
10ልባቸው ቅን የሆኑትን የሚያድን፥
ልዑል እግዚአብሔር፥ እርሱ ጋሻዬ ነው።
11እግዚአብሔር ሁልጊዜ በክፉዎች ላይ የሚፈርድ
ትክክለኛ ዳኛ ነው።
12ክፉዎች ከክፋታቸው የማይመለሱ ከሆነም፥
እግዚአብሔር ሰይፉን ይስላል፤
ቀስቱንም ያመቻቻል።
13የሚገድሉ የጦር መሣሪያዎችን ያበጃል፤
እንደ እሳት የሚንበለበሉ ፍላጻዎችንም ያዘጋጃል።
14ኃጢአተኞች በደልን ይፀንሳሉ፤
ተንኰልን ያረግዛሉ፤
ውሸትን ይወልዳሉ።
15ለሌሎች ወጥመድ የሚሆን
ጥልቅ ጒድጓድ ይቈፍራሉ፤
ነገር ግን በቈፈሩት ጒድጓድ ውስጥ
እነርሱ ራሳቸው ይገቡበታል።
16የሚያመጡት ችግር በራሳቸው ላይ ይደርሳል፤
በክፉ ድርጊታቸውም ዐናታቸው ይፈጠፈጣል።
17ስለ እውነተኛነቱ እግዚአብሔርን አመሰግናለሁ፤
ለልዑል አምላክ ስም የምስጋና መዝሙር አቀርባለሁ።
Currently Selected:
መጽሐፈ መዝሙር 7: አማ05
Highlight
Share
Copy
Want to have your highlights saved across all your devices? Sign up or sign in
© The Bible Society of Ethiopia, 2005
© የኢትዮጵያ መጽሐፍ ቅዱስ ማኅበር፥ 1997