YouVersion Logo
Search Icon

መጽሐፈ መዝሙር 69

69
ርዳታ ለማግኘት የቀረበ ጸሎት
1የውሃ ሙላት እስከ አንገቴ ስለ ደረሰ፤
አምላክ ሆይ! አድነኝ!
2መቆሚያ ስፍራ ስለ አጣሁ በጥልቅ ረግረግ ውስጥ
ለመስረግ ተቃርቤአለሁ፤
በጥልቅ ውሃ ውስጥ እገኛለሁ፤
ውሃ ሙላት ሊያሰጥመኝ ተቃርቦአል።
3ከመጮኼ ብዛት የተነሣ ደከምኩ፤
ጒሮሮዬም ቈሰለ፤
አምላኬን በመጠባበቅ ዐይኖቼ ፈዘዙ።
4ያለ ምክንያት የሚጠሉኝ ከራሴ ጠጒር ይልቅ በዝተዋል፤
ብዙዎች ጠላቶቼ ሊያጠፉኝ ይፈልጋሉ
ያልሰረቅኹትን ነገር መመለስ አለብኝን? #መዝ. 35፥19፤ ዮሐ. 15፥25።
5አምላክ ሆይ! ሞኝነቴን አንተ ታውቃለህ፤
ኃጢአቴ ከአንተ የተሰወረ አይደለም።
6የእስራኤል አምላክ ሆይ!
አንተን ተስፋ የሚያደርጉ በእኔ ምክንያት አይፈሩ፤
የሠራዊት አምላክ እግዚአብሔር ሆይ!
አንተን የሚፈልጉ በእኔ ምክንያት አይዋረዱ።
7ስለ አንተ ስድብን ታግሼአለሁ፤
ኀፍረትም ፊቴን ሸፍኖታል።
8በወንድሞቼ መካከል እንግዳ፥
በእናቴም ልጆች መካከል ባይተዋር ሆንኩ።
9ለቤትህ ያለኝ ቅናት በውስጤ እንደ እሳት ይነዳል፤
በአንተ ላይ የተሰነዘረው ስድብ በእኔ ላይ ዐረፈ። #ዮሐ. 2፥7፤ ሮም 15፥3።
10በምጾምበት ጊዜ በጣም አለቀስኩ፤
በዚህም ተሰደብኩ።
11የሐዘን ልብስ ስለብስ
እየተዘባበቱ ይስቁብኛል።
12በአደባባይ የሚቀመጡት ያሙኛል።
ሰካራሞች በዘፈን ይሰድቡኛል።
13እግዚአብሔር ሆይ! እኔ ግን ወደ አንተ እጸልያለሁ፤
አንተ በመረጥከው ጊዜ ጸሎቴን መልሰህ፥
በዘለዓለማዊው ፍቅርህ ማዳንህን አረጋግጥልኝ።
14በረግረግ ውስጥ ከመስረግ አድነኝ፤
ከጠላቶቼም ጠብቀኝ፤
በጥልቅ ውሃም ከመስጠም አድነኝ።
15ጐርፍ እንዳይወስደኝ፥
ጥልቅ ባሕር እንዳያሰጥመኝ፥
መቃብር እንዳይውጠኝ ጠብቀኝ።
16እግዚአብሔር ሆይ! ቸርነት በተሞላበት ፍቅርህ ጸሎቴን ስማ፤
በታላቁ ምሕረትህ ወደ እኔ ተመለስ።
17ከእኔ ከአገልጋይህ ፊትህን አትሰወር፤
በከባድ ጭንቀት ላይ ስለ ሆንኩ ፈጥነህ ስማኝ።
18ወደ እኔ ቀርበህ ተቤዠኝ፤
ከጠላቶቼም አድነኝ።
19ምን ያኽል እንደምሰደብ አንተ ታውቃለህ፤
ምን ያኽል እንደ ተዋረድኩና ክብሬም
እንደ ተቀነሰ ታስተውላለህ፤
እነሆ፥ ጠላቶቼ ሁሉ በፊትህ ናቸው።
20ስድብ ልቤን ስለ ሰበረው ተስፋ ቈረጥኩ፤
የሚያስተዛዝነኝ ሰው ፈለግኹ፤
ነገር ግን ማንም አልነበረም፤
የሚያጽናናኝ ሰው ፈለግኹ፤
ነገር ግን ማንም አልተገኘም።
21በምግቤ ውስጥ ሐሞት ቀላቀሉ፤
በጠማኝም ጊዜ ሆምጣጤ ሰጡኝ። #ማቴ. 27፥48፤ ማር. 15፥36፤ ሉቃ. 23፥36፤ ዮሐ. 19፥28-29።
22በፊታቸው የተዘረጋው ማእድ ወጥመድና
የሚመገቡትም ምግብ የመውደቂያቸውና የመጥፊያቸው ምክንያት ይሁን።
23ዐይናቸው እንዳያይ ይጨልም፤
ወገባቸው ሁልጊዜ ይንቀጥቀጥ። #ሮም 11፥9-10።
24ኀይለኛ ቊጣህን በላያቸው አፍስስ፤
የቊጣህ መቅሠፍትም ይድረስባቸው።
25መኖሪያቸው ወና ይሁን፤
በቤታቸው ውስጥ አንድም ሰው አይኑር። #ሐ.ሥ. 1፥20።
26አንተ የቀጣሃቸውን ሰዎች ያሳድዳሉ፤
አንተ ባቈሰልካቸው ሰዎች ላይ ሥቃይ ይጨምራሉ።
27በበደላቸው ላይ በደልን ጨምርባቸው፤
ይቅርታም አታድርግላቸው።
28ስሞቻቸው ከሕያዋን መዝገብ ይደምሰሱ፤
ከደጋግ ሰዎችም ጋር አይቈጠሩ። #ዘፀ. 32፥32፤ ራዕ. 3፥5፤ 13፥8፤ 17፥8።
29እኔ ግን በሥቃይና ተስፋ በመቊረጥ ላይ ስለምገኝ
አምላክ ሆይ! ጠብቀኝ፤ አድነኝም።
30እግዚአብሔርን በመዝሙር አመሰግነዋለሁ፤
በምስጋናም መዝሙር ታላቅነቱን እገልጣለሁ።
31ይህም የተሟላ ዕድገት ያለው ኰርማ ወይም ወይፈን ከመሠዋት ይልቅ
እግዚአብሔርን የበለጠ ያስደስተዋል።
32ትሑታን ይህን ባዩ ጊዜ ደስ ይላቸዋል፤
በጸሎት እግዚአብሔርን የምትሹ በርቱ።
33እግዚአብሔር የችግረኞችን ጩኸት ይሰማል፤
በእስር ቤት ያሉትን ወገኖቹንም ችላ አይላቸውም።
34ሰማይና ምድር፥ ባሕሮችና በውስጣቸው የሚኖሩ ተንቀሳቃሽ ፍጥረቶች ሁሉ
እግዚአብሔርን ያመስግኑት።
35እርሱ ጽዮንን ያድናል፤
የይሁዳንም ከተሞች ያድሳል፤
ሕዝቡም በዚያ ይኖራሉ፤
ምድሪቱንም የራሳቸው ያደርጋሉ።
36የአገልጋዮቹም ዘሮች ይወርሱአታል፤
እርሱን የሚወዱ ሁሉ እዚያ ይኖራሉ።

Highlight

Share

Copy

None

Want to have your highlights saved across all your devices? Sign up or sign in