YouVersion Logo
Search Icon

መጽሐፈ መዝሙር 33

33
የምስጋና መዝሙር
1ጻድቃን ሆይ! በእግዚአብሔር ደስ ይበላችሁ፤
ቅኖች ሊያመሰግኑት ይገባል።
2እግዚአብሔርን በመሰንቆ አመስግኑት፤
ዐሥር አውታር ባለውም በገና ዘምሩለት።
3አዲስ መዝሙር ዘምሩለት!
ባማረ ስልት በገና ደርድሩ፤
በደስታም “እልል” በሉ።
4የእግዚአብሔር ቃል እውነት ነው፤
ሥራውም ሁሉ የታመነ ነው።
5እግዚአብሔር ጽድቅንና ፍትሕን ይወዳል፤
ዘለዓለማዊ ፍቅሩም ምድርን ይሞላል።
6እግዚአብሔር ሰማያትን በቃሉ፥
በሰማይ የሚገኙትን ፍጥረቶች
በትእዛዙ ፈጠረ።
7ባሕርን ሁሉ በአንድ ቦታ ሰበሰበ፤
ጥልቅ ለሆኑት ውቅያኖሶችም
መከማቻ ስፍራ አዘጋጀላቸው።
8በምድርም የምትኖሩ ሁሉ እግዚአብሔርን ፍሩ፤
የዓለም ሕዝቦች ሁሉ እግዚአብሔርን አክብሩ።
9እርሱ በተናገረ ጊዜ ዓለም ተፈጠረ፤
በትእዛዙም ሁሉ ነገር ጸንቶ ቆመ።
10እግዚአብሔር የአሕዛብን ዕቅድ እንዳይሳካ ያደርጋል፤
የሕዝቦችንም ዓላማ ዋጋቢስ ያደርጋል።
11የእግዚአብሔር ዕቅድ ለዘለዓለም ጸንቶ ይኖራል፤
ዓላማውም ከትውልድ ወደ ትውልድ ይተላለፋል።
12እግዚአብሔር አምላኩ የሆነለትና
እግዚአብሔር የራሱ አድርጎ የመረጠው ሕዝብ የተባረከ ነው!
13እግዚአብሔር ከሰማይ ሆኖ ይመለከታል፤
የሰውንም ዘር ሁሉ ያያል፤
14በዙፋኑ ላይ ሆኖ
በምድር ላይ ያሉትን ሁሉ ያያል።
15የሁላቸውንም ልብ የሠራ እርሱ ነው
የሚያደርጉትን ሁሉ ይመለከታል።
16ንጉሥ በሠራዊቱ ብዛት አይድንም፤
አርበኛም በከፍተኛ ኀይሉ አያመልጥም።
17ፈረስ ለማዳን ከንቱ ተስፋ ነው፤
ከዚያ ሁሉ ኀይሉ ጋር ሊያድን አይችልም።
18እግዚአብሔር የሚፈሩትንና
ዘለዓለማዊ ፍቅሩ ተስፋቸው የሆነውን ይመለከታል።
19ይህም የሚሆነው ከሞት ሊያድናቸውና
ከራብም ሊጠብቃቸው ነው።
20እግዚአብሔርን በተስፋ እንጠብቀዋለን
ረዳታችንና ጋሻችን እርሱ ነው።
21በቅዱስ ስሙም ስለምንታመን
በእርሱ ደስ ይለናል።
22እግዚአብሔር ሆይ!
ተስፋችንን በአንተ እንዳደረግን
ዘላቂ ፍቅርህ በእኛ ላይ ይሁን።

Highlight

Share

Copy

None

Want to have your highlights saved across all your devices? Sign up or sign in

Videos for መጽሐፈ መዝሙር 33