YouVersion Logo
Search Icon

መጽሐፈ መዝሙር 22

22
የሐዘን ጩኸትና የምስጋና መዝሙር
1አምላኬ! አምላኬ! ለምን ተውከኝ?
እኔን ከማዳን የራቅኸው ለምንድን ነው?
ከመቃተት ድምፄስ የራቅኸው ለምንድን ነው? #ማቴ. 27፥46፤ ማር. 15፥34።
2አምላኬ ሆይ! በቀን ወደ አንተ እጮኻለሁ፤
አንተ ግን አትሰማኝም፤
በሌሊት እጣራለሁ፤ ዕረፍትም የለኝም።
3ሆኖም አንተ በእስራኤል የተመሰገንክ፥
በዙፋንህ ላይ ተቀምጠህ የምትገዛ ቅዱስ አምላክ ነህ።
4የቀድሞ አባቶቻችን በአንተ ተማመኑ፤
በአንተም ስለ ተማመኑ አዳንካቸው።
5ለእርዳታ ወደ አንተ በጮኹ ጊዜ አዳንካቸው፤
አንተን በተማመኑ ጊዜ አላሳፈርካቸውም።
6እኔ ግን ከሰው ሁሉ ያነስኩ ትል ነኝ፤
ሰዎች ያፌዙብኛል በሕዝብም ዘንድ የተናቅሁ ነኝ።
7የሚያዩኝ ሰዎች ሁሉ ይዘባበቱብኛል፤
ፊታቸውን ያኰሳትሩብኛል፤
ራሳቸውንም ይነቀንቁብኛል። #ማቴ. 27፥39፤ ማር. 15፥29፤ ሉቃ. 23፥35።
8“እግዚአብሔር ያድነው ዘንድ
በእርሱ ተማምኖአልና
የሚወደው ከሆነ እስቲ ያድነው” ይላሉ። #ማቴ. 27፥43።
9በደኅና እንድወለድ ያደረግኸኝ አንተ ነህ፤
የእናቴን ጡት በምጠባበት በሕፃንነቴ ወራት እንኳ
የጠበቅኸኝ አንተ ነህ።
10ከተወለድኩበት ቀን ጀምሮ በአንተ ጥበቃ ሥር ነኝ፤
ከልደቴ ጊዜም ጀምሮ አንተ አምላኬ ነህ።
11መከራ ሊደርስብኝ ስለ ተቃረበና የሚረዳኝም ስለሌለ
እባክህ ከእኔ አትራቅ!
12ብዙ ጠላቶች እንደሚዋጉ በሬዎች ከበውኛል፤
እንደ ባሳን ተዋጊ ኰርማዎችም በዙሪያዬ ናቸው፤
13የሚበላውን ነገር አድኖ ለመቦጫጨቅ እንደሚያገሣ አንበሳ
ጠላቶቼ አፋቸውን ከፈቱብኝ።
14ጒልበቴ ደክሞ እንደ ውሃ ፈሰሰ፤
አጥንቶቼ ሁሉ ከመገጣጠሚያቸው ተለያዩ፤
ልቤም እንደ ሰም በውስጤ ቀለጠ።
15ጒሮሮዬ እንደ ሸክላ ደረቀ፤
ምላሴም ከላንቃዬ ጋር ተጣበቀ፤
እንደ ሞተ ሰው በትቢያ ላይ ተውከኝ።
16ክፉ ሰዎች እንደ ውሻ ስብስብ ከበቡኝ፤
እጆቼንና እግሮቼን ቸነከሩ።
17አጥንቶቼ ተቈጠሩ፤
ጠላቶቼም አተኲረው እያዩ በማፌዝ ተመለከቱኝ።
18ልብሶቼን ተከፋፈሉ፤
በቀሚሴም ላይ ዕጣ ተጣጣሉ። #ማቴ. 27፥35፤ ማር. 15፥24፤ ሉቃ. 23፥34፤ ዮሐ. 19፥24።
19እግዚአብሔር ሆይ! ከእኔ አትራቅ፤
ረዳቴ ሆይ! እኔን ለመርዳት ፈጥነህ ድረስ።
20ነፍሴን ከሰይፍና
ከእነዚያ ውሾች ኀይል አድነኝ።
21ከአንበሳ አፍ አድነኝ
ከተዋጊ ጐሽ ቀንድም ጠብቀኝ።
22የስምህን ታላቅነት ለወገኖቼ እናገራለሁ፤
እነርሱ በተሰበሰቡበት ስፍራ አመሰግንሃለሁ፤ #ዕብ. 2፥12።
23እናንተ እግዚአብሔርን የምትፈሩት አመስግኑት!
እናንተ የያዕቆብ ዘሮች ሁሉ አክብሩት!
እናንተ የእስራኤል ዘሮች ሁሉ በፍርሃት ከፍ ከፍ አድርጉት!
24የተጨቈነውን ሰው አልናቀውም፤
በሁናቴውም አልተጸየፈውም፤
ፊቱን ከእርሱ አልሰወረም፤
ነገር ግን ለእርዳታ የሚያደርገውን ጩኸት አዳመጠው።
25ስለ ሠራኸው መልካም ሥራ
ብዙ ሕዝብ በተሰበሰበበት ስፍራ አመሰግንሃለሁ፤
በሚፈሩህ ሰዎች ፊት ሆኜ፥
የተሳልኩትን ስለት እፈጽማለሁ።
26ድኾች እስኪጠግቡ ይበላሉ፤
እግዚአብሔርን የሚሹት ያመሰግኑታል፤
ልባቸው በሕይወት ዘመናቸው ሁሉ ይደሰታል።
27እስከ ምድር ዳርቻ ያሉ ሰዎች ሁሉ አስታውሰው ወደ እግዚአብሔር ይመለሳሉ፤
በዓለም የሚገኙት ሕዝቦች ሁሉ በፊቱ ይሰግዳሉ።
28ሥልጣን ሁሉ የአንተ ነው፤
ሕዝቦችም ሁሉ ይገዙልሃል።
29ጌታ ሆይ! የተትረፈረፈ ሀብት ያላቸው ሁሉ ይሰግዱልሃል።
ለሞትና ለመቃብር የተቃረቡትም መጥተው ይንበረከኩልሃል።
30መጪው ትውልድ ያገለግለዋል፤
የወደፊት ትውልድም ስለ እግዚአብሔር ይነገረዋል።
31እነርሱ የጽድቅ ሥራውን በማወጅ
“እግዚአብሔር ሕዝቡን አዳነ” ብለው ገና ላልተወለዱ ሰዎች ይናገራሉ።

Highlight

Share

Copy

None

Want to have your highlights saved across all your devices? Sign up or sign in

Videos for መጽሐፈ መዝሙር 22