መጽሐፈ መዝሙር 18
18
የዳዊት የድል መዝሙር
(2ሳሙ. 22፥1-51)
1እግዚአብሔር ሆይ!
ኀይል የምትሰጠኝ አንተ ስለ ሆንክ፥ እወድሃለሁ።
2እግዚአብሔር አለቴ፥ አምባዬና አዳኜ ነው፤
አምላኬ የምጠጋበት አለቴ ነው፤
እርሱ ጋሻዬና የመዳኔ ቀን፥ ጠንካራ መመኪያም ነው።
3ምስጋና የሚገባውን እግዚአብሔርን እጠራለሁ፤
እርሱም ከጠላቶቼ ያድነኛል።
4የሞት ጣር ከበበኝ፤
የጥፋት ጐርፍም አጥለቀለቀኝ።
5የሲኦል ገመድ ተበተበኝ፤
የሞት ወጥመድም ተጠመደብኝ።
6መከራ በደረሰብኝ ጊዜ እግዚአብሔርን ጠራሁት፤
እንዲረዳኝም አምላኬን ለመንኩት፤
በመቅደሱ ሆኖ ድምፄን ሰማ፤
ጩኸቴንም አደመጠ።
7እግዚአብሔር ስለ ተቈጣ
ምድር ተናወጠች፤ ተንቀጠቀጠችም፤
የተራሮች መሠረቶች ተናጉ፤ ተነቃነቁም።
8ከአፍንጫው የቊጣ ጢስ ወጣ፤
ከአፉም የሚባላ የእሳት ነበልባልና
የሚያቃጥል ፍም ወጣ።
9ሰማይን ሰንጥቆ ወደ ታች ወረደ፤
ከእግሩም በታች ጥቅጥቅ ያለ ደመና ነበረ።
10በኪሩቤል ላይ ሆኖ በረረ፤
በነፋስ ክንፎች ላይ ሆኖ ወደ ላይ መጠቀ።
11ሁለንተናውን በጨለማ ሸፈነ፤
በውሃ የተሞላ ጥቅጥቅ ያለ ደመና ከቦታል።
12በፊቱ ካለው ነጸብራቅ በረዶና የእሳት ብልጭታ
ጥቅጥቅ ያለውን ደመና ሰንጥቆ ወጣ።
13እግዚአብሔር ከሰማይ አንጐደጐደ፤
ልዑል እግዚአብሔር ድምፁን አሰማ።
14ፍላጻውን ከቀስቱ አስፈነጠረ፤
ጠላቶቹንም በተናቸው፤
በመብረቁም ብልጭታ አሳደዳቸው።
15እግዚአብሔር ሆይ!
ጠላቶችህን በገሠጽህ ጊዜ፥
የቊጣ ድምፅህንም ባሰማህ ጊዜ
የውቅያኖስ ወለል ታየ፤
የምድርም መሠረት ተጋለጠ።
16እግዚአብሔር ከላይ ሆኖ እጁን በመዘርጋት ያዘኝ፤
ከጥልቅ ውሃም ስቦ አወጣኝ።
17በጣም በርትተውብኝ ከነበሩት
ከኀይለኞች ጠላቶቼና ከሚጠሉኝ ሰዎች ሁሉ እጅ
እግዚአብሔር አዳነኝ።
18እኔ በተቸገርኩበት ጊዜ በጠላትነት ተነሡብኝ፤
እግዚአብሔር ግን ጠበቀኝ።
19ወደ ሰፊ ቦታ አወጣኝ፤
በእኔ ደስ ስለ ተሰኘም አዳነኝ።
20እግዚአብሔር እንደ ጽድቄ ይከፍለኛል፤
እንደ እጄም ንጽሕና ይመልስልኛል።
21እኔ የእግዚአብሔርን መንገድ ተከትዬአለሁ፤
ፊቴን ከአምላኬ በመመለስ ክፉ ነገር አላደረግሁም።
22የእግዚአብሔርን ሕጎች ሁሉ እፈጽማለሁ
ሥርዓቱንም ከማክበር ወደ ኋላ አላልኩም።
23በእርሱ ዘንድ ንጹሕ ነበርኩ፤
ከኃጢአትም ራሴን ጠብቄአለሁ።
24እግዚአብሔር እንደ ጽድቄ፥
እንደ እጄም ንጽሕና፥ ዋጋዬን ከፈለኝ።
25አምላክ ሆይ! ለአንተ ታማኞች ለሆኑት ታማኝ ነህ፤
እውነተኞች ለሆኑትም እውነተኛ ነህ።
26ለንጹሖች ንጹሕ ነህ፤
ለጠማሞች ግን ተገቢ ዋጋቸውን ትሰጣለህ።
27ትሑቶችን ታድናለህ፤
ትዕቢተኞችን ግን ታዋርዳለህ።
28እግዚአብሔር ሆይ! ለእኔ ብርሃኔ ነህ፤
አንተ አምላኬ ጨለማዬን ታበራለህ።
29በአንተ ርዳታ አንድ የጦር ጓድ አጠቃለሁ፤
አንተ አምላኬም ቅጥሩን ለመዝለል ትረዳኛለህ።
30የአምላክ መንገድ ፍጹም ነው!
ቃሉም ተጠራ ነው!
እርሱን መጠጊያ ለሚያደርጉት ሁሉ ጋሻቸው ነው።
31ከእግዚአብሔር በቀር ማነው አምላክ?
ከእርሱስ በቀር መጠጊያ የሚሆን ማነው?
32ብርታትን የሚሰጠኝና መንገዴን የሚያቀናልኝ
እግዚአብሔር ነው።
33እርሱ እግሮቼን እንደ ብሖር እግሮች ያጠነክራል፤
በከፍታ ቦታዎችም ያለ ስጋት ለመቆም ያስችለኛል። #ዕን. 3፥19።
34እጆቼን ለጦርነት ያሠለጥናል፤
የነሐስን ቀስት መሳብ እንዲችሉ ክንዶቼን ያበረታል።
35የማዳን ጋሻህን ሰጠኸኝ፤
ቀኝ እጅህም ይጠብቀኛል፤
እኔን ለመርዳት መጥተህ ታላቅ አደረግኸኝ።
36መረማመጃዬን አሰፋህ፤
እግሮቼም አልተንሸራተቱም።
37ጠላቶቼን አሳድጄ እደርስባቸዋለሁ፤
ሳላጠፋቸውም ወደ ኋላ አልመለስም።
38ዳግመኛ እንዳይነሡ አድርጌ እመታቸዋለሁ፤
በእግሬም ሥር ይወድቃሉ።
39ለጦርነት ኀይልን ትሰጠኛለህ፤
በጠላቶቼም ላይ ድልን ታጐናጽፈኛለህ።
40ጠላቶቼ ከፊቴ ወደ ኋላ እንዲሸሹ አደረግህ
የሚጠሉኝንም ሁሉ አጠፋቸዋለሁ።
41የሚረዳቸውን በመፈለግ ይጮኻሉ፤
ነገር ግን ማንም አያድናቸውም፤
እግዚአብሔርንም ይጠሩታል፤
እርሱ ግን አይመልስላቸውም።
42ነፋስ ጠርጎ እንደሚወስደው ትቢያ እስኪሆኑ ድረስ አደቃቸዋለሁ፤
በመንገድ ላይ እንዳለ ጭቃም እረግጣቸዋለሁ።
43ከዐመፀኛ ሕዝብ አዳንከኝ፤
በአሕዛብም ላይ ሾምከኝ፤
የማላውቀውም ሕዝብ ይገዛልኛል።
44ባዕዳን ያጐነብሱልኛል፤
ዝናዬን እንደ ሰሙም ይገዙልኛል።
45በፍርሃት ይጨነቃሉ፤
በመንቀጥቀጥም ከምሽጋቸው ወጥተው
ወደ እኔ ይመጣሉ።
46እግዚአብሔር ሕያው ነው!
አምላኬ መጠጊያዬ ይመስገን!
ያዳነኝም ኀያል አምላክ ከፍ ከፍ ይበል።
47እርሱ ጠላቶቼን ይበቀልልኛል፤
ሕዝቦችንም ከበታቼ አድርጎ ያስገዛልኛል።
48ከጠላቶቼም ታድነኛለህ።
ከጠላቶቼ በላይ ከፍ ከፍ ታደርገኛለህ፤
ከግፈኞችም ታድነኛለህ።
49እግዚአብሔር ሆይ! ስለዚህ በሕዝቦች መካከል አመሰግንሃለሁ፤
ለስምህም እዘምራለሁ። #ሮም 15፥9።
50እርሱ ላነገሠው ንጉሥ ታላቅ ድልን ያጐናጽፈዋል፤
ራሱ ለቀባው ዘለዓለማዊ ፍቅሩን ያሳየዋል፤
ለዳዊትና ለዘሩ ለዘለዓለም ይህን ያደርጋል።
Currently Selected:
መጽሐፈ መዝሙር 18: አማ05
Highlight
Share
Copy
Want to have your highlights saved across all your devices? Sign up or sign in
© The Bible Society of Ethiopia, 2005
© የኢትዮጵያ መጽሐፍ ቅዱስ ማኅበር፥ 1997