መጽሐፈ ምሳሌ 21
21
1የንጉሥ ልብ በእግዚአብሔር እጅ ነው፤
እርሱንም እንደ ወራጅ ውሃ ወደ ፈቀደው ይመራዋል።
የንጉሥንም አእምሮ ይቈጣጠራል።
2ሰው የሚያደርገው ነገር ሁሉ ትክክል ይመስለዋል፤
እግዚአብሔር ግን የልብን ሐሳብ ይመዝናል።
3መሥዋዕት ከማቅረብ እውነተኛ ይልቅ ትክክልና
የሆነውን ነገር ማድረግ እግዚአብሔርን ደስ ያሰኘዋል።
4ትዕቢትና ዕብሪት የክፉ ሰዎች መታወቂያ ናቸው፤
ይህም ኃጢአት ነው።
5በጥንቃቄ በወጣ ዕቅድ የሚሠራ ሥራ ትርፍ ያስገኛል፤
ያለ ዕቅድ በችኰላ የሚሠራ ሥራ ግን ያደኸያል።
6በመዋሸት የሚገኝ ሀብት ተኖ እንደሚጠፋ እንፋሎትና
እንደሚገድል ወጥመድ ነው።
7ዐመፀኞች መልካም የሆነውን ነገር ማድረግ
ስለማይወዱ በግፍ ሥራቸው ይጠፋሉ።
8ኃጢአተኞች በጠማማ መንገድ መሄድ ይወዳሉ፤
ልበ ንጹሖች ግን መልካም የሆነውን ነገር ያደርጋሉ።
9ከጨቅጫቃ ሚስት ጋር በአንድ ቤት ከመኖር ይልቅ
በጣራ ማእዘን ላይ መኖር ይሻላል።
10ዐመፀኞች ዘወትር ክፋትን ማድረግ ይወዳሉ፤
ለማንም ሰው ርኅራኄ የላቸውም።
11ፌዘኛ በሚቀጣበት ጊዜ አላዋቂ ሰው ጥበብን ያገኛል፤
ለብልኅም ሰው ትምህርት በሚሰጥበት ጊዜ የበለጠ ዐዋቂ ይሆናል።
12ጻድቁ አምላክ በክፉዎች ቤት የሚደረገውን ሁሉ ይመለከታል።
ክፉዎችንም አሸቀንጥሮ በመጣል ያጠፋቸዋል።
13የድኾችን ጩኸት ለመስማት ፈቃደኛ ያልሆነ ሰው
እርሱም ተቸግሮ በሚጮኽበት ጊዜ የሚረዳው አያገኝም።
14የተቈጣ ሰው ስጦታ በድብቅ ሲቀርብለት
ንዴቱ ይበርድለታል፤
በምሥጢር የሚሰጥ እጅ መንሻ ቊጣን ያበርዳል።
15ትክክለኛ ፍርድ በሚሰጥበት ጊዜ
ደጋግ ሰዎች ደስ ይላቸዋል፤
ክፉዎችን ግን ያስደነግጣል።
16ከማስተዋል መንገድ የሚርቀውን ሰው
ሞት ይጠብቀዋል።
17ቅንጦትን የሚወድ ሰው ይደኸያል፤
የወይን ጠጅንና ቅባትን የሚወድድ ሰው ምንጊዜም አይበለጽግም።
18በደጋግ ሰዎች ላይ ሊደርስ የነበረው ችግር
በክፉ ሰዎች ላይ ይደርሳል፤ በቀጥተኛ ሰዎች ላይ
ሊደርስ የነበረው ችግር በእምነተ ቢሶች ላይ ይመጣል።
19ከጨቅጫቃና ከነዝናዛ ሚስት ጋር አብሮ ከመኖር
በምድረ በዳ መኖር ይሻላል።
20ብልኅ ሰው ብዙ ሀብትና ውድ ነገሮችን በቤቱ ያከማቻል፤
ማስተዋል የጐደለው ሰው ግን ያለውን ሁሉ ያባክናል።
21ጽድቅንና ቸርነትን የሚከተል ሰው
ሕይወትን፥ ብልጽግናንና ክብርን ያገኛል።
22ብልኅ የጦር መሪ በብርቱ ሠራዊት
የተጠበቀውን ከተማ ድል አድርጎ ይይዛል፤
የተማመኑባቸውንም ምሽጎች ያፈራርሳል።
23ከመከራ ለማምለጥ የሚፈልግ፥
ክፉ ከመናገር ይቈጠባል።
24ትዕቢተኛና ትምክሕተኛ ሰው ፌዘኛ ነው፤
ድርጊቱም በትዕቢት የተሞላ ነው።
25መሥራት የማይፈልግ ሰነፍ ሰው
ራሱን የገደለ ያኽል ይቈጠራል።
26ሰነፍ ሰው ዘወትር የሚመኘው ብዙ ነገር ለማግኘት ነው፤
ደግ ሰው ግን በልግሥና ይሰጣል።
27ዐመፀኞች የሚያቀርቡት መሥዋዕት በእግዚአብሔር ዘንድ አጸያፊ ነው፤
በተለይም በክፉ አሳብ ተነሣሥተው የሚያቀርቡለት መሥዋዕት የበለጠ አጸያፊ ነው።
28የሐሰተኛ ሰው ምስክርነት ውድቅ ይሆናል፤
በጥንቃቄ አስቦ የሚናገር ሰው ቃል ግን ይጸናል።
29ክፉ ሰው “አልተሳሳትኩም” በማለት በግትርነት ይጸናል፤
እውነተኛ ሰው ግን ስለ ራሱ ጠባይ በጥንቃቄ ያስባል።
30ሰው በጥበቡ፥ በአስተዋይነቱና በዕቅዱ
በእግዚአብሔር ላይ መነሣት አይችልም።
31ፈረስን ለጦርነት ማዘጋጀት ይቻላል፤
ድልን የሚያጐናጽፍ ግን እግዚአብሔር ነው።
Currently Selected:
መጽሐፈ ምሳሌ 21: አማ05
Highlight
Share
Copy
Want to have your highlights saved across all your devices? Sign up or sign in
© The Bible Society of Ethiopia, 2005
© የኢትዮጵያ መጽሐፍ ቅዱስ ማኅበር፥ 1997