YouVersion Logo
Search Icon

ወደ ፊልጵስዩስ ሰዎች 1

1
1የኢየሱስ ክርስቶስ አገልጋዮች ከሆኑት ከጳውሎስና ከጢሞቴዎስ፥ #ሐ.ሥ. 16፥12።
በፊልጵስዩስ ከተማ ለሚኖሩ፥ በኢየሱስ ክርስቶስ ቅዱሳን ለሆኑ ሁሉ፥ እንዲሁም ለኤጲስ ቆጶሳትና ዲያቆናት፦
2ከአባታችን ከእግዚአብሔርና ከጌታ ከኢየሱስ ክርስቶስ ጸጋና ሰላም ለእናንተ ይሁን።
የጳውሎስ የምስጋና ጸሎት
3እናንተን በማስታውስበት ጊዜ ሁሉ አምላኬን አመሰግናለሁ፤ 4ስለ ሁላችሁም በምጸልይበት ጊዜ ሁሉ ጸሎቴ በደስታ የተሞላ ነው። 5ከመጀመሪያው ቀን አንሥቶ እስከ አሁን ወንጌልን በመስበክ የሥራዬ ተባባሪዎች ስለ ሆናችሁ እግዚአብሔርን አመሰግናለሁ፤ 6ይህን መልካም ሥራ በእናንተ ሕይወት ውስጥ የጀመረ አምላክ፥ ኢየሱስ ክርስቶስ ለፍርድ በሚመለስበት ቀን ወደ ፍጻሜ እንደሚያደርሰው እርግጠኛ ነኝ። 7አሁን በእስር ቤት ባለሁበት ጊዜና ከመታሰሬም በፊት ለወንጌል እውነት ለመከላከልና እርሱንም ለማጽናት እግዚአብሔር በጸጋው በሰጠኝ ዕድል ሁላችሁም ተካፋዮች ስለ ሆናችሁ እናንተ ሁልጊዜ በልቤ ናችሁ። ስለዚህም ስለ እናንተ የሚሰማኝ ስሜት ትክክል ነው። 8በኢየሱስ ክርስቶስ ፍቅር ሁላችሁንም ምን ያኽል እንደምናፍቃችሁ እግዚአብሔር ምስክሬ ነው።
9ፍቅራችሁ ዕውቀትና ማስተዋል የሞላበት ሆኖ እያደገ እንዲሄድ እጸልያለሁ። 10ይኸውም የተሻለውን ነገር መርምራችሁ እንድታውቁና ክርስቶስ ተመልሶ በሚመጣበት ቀን ንጹሖችና ነውር የሌለባችሁ ሆናችሁ እንድትገኙ ነው። 11በዚህም ዐይነት ሕይወታችሁ ከኢየሱስ ክርስቶስ በሚገኘው የጽድቅ ፍሬ የተሞላ ሆኖ ለእግዚአብሔር ክብርና ምስጋና የምታስገኙ ትሆናላችሁ።
የጳውሎስ መታሰር ለወንጌል መስፋፋት እንደ ረዳ
12ወንድሞቼ ሆይ! በእኔ ላይ የደረሰው ነገር ሁሉ ወንጌል በይበልጥ እንዲስፋፋ ማድረጉን እንድታውቁ እወዳለሁ። 13እኔም የታሰርኩት በክርስቶስ ምክንያት መሆኑን የቤተ መንግሥት ዘበኞችና ሌሎችም እዚያ ያሉት ሰዎች ሁሉ ያውቃሉ። #ሐ.ሥ. 28፥30። 14በእኔ መታሰር ምክንያት ከአማኞች ወንድሞች ብዙዎቹ በይበልጥ በጌታ የሚተማመኑ ሆነዋል፤ ስለዚህ የእግዚአብሔርን ቃል ያለ ፍርሀት ለማብሠር ከቀድሞ የበለጠ ድፍረት አግኝተዋል።
15ይሁን እንጂ አንዳንዶቹ የክርስቶስን የምሥራች ቃል የሚያበሥሩት በቅናት፥ ሌሎቹም በፉክክር መንፈስ ነው፤ ሌሎቹ ግን ክርስቶስን የሚሰብኩት በቅን ልቡና ነው። 16እነዚህ የእግዚአብሔርን ቃል በቅን ልቡና የሚያበሥሩት ከፍቅር የተነሣ ነው፤ እነርሱም እኔ ለወንጌል ለመከላከል እዚህ የተጣልኩ መሆኔን ስለሚያውቁ ነው። 17እነዚያ ግን ስለ ክርስቶስ አጣምመው የሚሰብኩት በቅንነት ሳይሆን በራስ ወዳድነትና በእስራቴ ላይ ተጨማሪ ችግር ሊያመጡብኝ አስበው ነው።
18ያም ሆነ ይህ በዚህ ደስ ይለኛል፤ በማስመሰልም ሆነ በእውነት በሁሉም መንገድ ክርስቶስ ይሰበካል። 19ሌላው የምደሰትበት ምክንያት በእናንተ ጸሎትና በኢየሱስ ክርስቶስ መንፈስ ርዳታ ነጻ እንደምወጣ ስለማውቅ ነው። 20በፍጹም እንደማላፍር በተስፋ እጠባበቃለሁ፤ ነገር ግን ዘወትር እንደማደርገውና ዛሬ በሕይወት ብኖር ወይም ብሞት ክርስቶስ በሰውነቴ ይከብራል ብዬ በድፍረት እናገራለሁ። 21ስለዚህ ለእኔ ሕይወት ማለት በክርስቶስ መኖር ነው፤ ሞትም ማለት ጥቅም የሚገኝበት ነገር ነው። 22ይሁን እንጂ በዚሁ ሥጋዊ አካሌ ቀጥዬ የምኖር ብሆን ፍሬ የሚሰጥ ሥራ መሥራት ማለት ነው፤ ሆኖም ግን ቀጥዬ ከመኖርና ከመሞት የትኛውን እንደምመርጥ አላውቅም። 23በእነዚህ በሁለቱ ሐሳቦች መካከል ተይዤአለሁ፤ በአንድ በኩል ከክርስቶስ ጋር መሆን ከሁሉ የሚበልጥ ነገር ስለ ሆነ ከዚህ ሕይወት ተለይቼ ከክርስቶስ ጋር መሆንን እፈልጋለሁ ይኸውም ከክርስቶስ ጋር መኖር እጅግ የተሻለ ስለ ሆነ ነው። 24በሌላ በኩል በሕይወት መኖሬ ለእናንተ የበለጠ አስፈላጊ ነው። 25በዚህ በመተማመን እኔ ከሞት ተርፌ እምነታችሁ እንዲያድግና ደስታን እንድታገኙ ከሁላችሁም ጋር እንድቈይ ዐውቃለሁ። 26እኔም እንደገና ወደ እናንተ ስመጣ በእኔ ምክንያት ያላችሁ ትምክሕት በኢየሱስ ክርስቶስ ይበዛል።
27እንግዲህ ከሁሉም በላይ ሕይወታችሁ የክርስቶስን ወንጌል የሚያስመሰግን ይሁን፤ ይህም እኔ መጥቼ ባያችሁም ወይም ከእናንተ ብርቅ በአንድ ዓላማ ጸንታችሁ መቆማችሁንና ወንጌልን በኅብረት ለማዳረስ መጋደላችሁን እሰማለሁ። 28ተቃዋሚዎቻችሁንም በምንም ነገር አትፍሩአቸው፤ ይህም ድፍረታችሁ ለእነርሱ የመጥፋታቸው ምልክት ሲሆን ለእናንተ ግን ከእግዚአብሔር ዘንድ የሆነ የመዳኛችሁ ምልክት ነው። 29ክርስቶስን የማገልገል ዕድል የተሰጣችሁ በእርሱ እንድታምኑ ብቻ ሳይሆን በእርሱ ምክንያት መከራ እንድትቀበሉም ጭምር ነው። 30ስለዚህ አሁን ከእኔ ጋር የመከራ ተካፋዮች ሆናችኋል፤ ይህም መከራ ከዚህ በፊት ደርሶብኝ ያያችሁትና አሁንም እየደረሰብኝ መሆኑን የምትሰሙት ነው። #ሐ.ሥ. 16፥19-40።

Highlight

Share

Copy

None

Want to have your highlights saved across all your devices? Sign up or sign in