YouVersion Logo
Search Icon

ኦሪት ዘኊልቊ 3

3
የአሮን ወንዶች ልጆች
1እግዚአብሔር ሙሴን በሲና ተራራ ላይ ባነጋገረው ጊዜ የአሮንና የሙሴ ትውልድ ይህ ነበር። 2አሮን አራት ወንዶች ልጆች ነበሩት፤ እነርሱም በኲሩ ናዳብ ሲሆን የቀሩት አቢሁ፥ አልዓዛርና ኢታማር ነበሩ። #ዘኍ. 26፥60። 3እነዚህም በክህነት እንዲያገለግሉ ተቀብተው ነበር። 4ነገር ግን ከእነርሱ ውስጥ ናዳብና አቢሁ በሲና በረሓ በእግዚአብሔር ፊት ያልተቀደሰ እሳት ጭረው በማቅረባቸው ተቀሥፈው ሞቱ፤ እነርሱም ልጆች አልነበሩአቸውም፤ ስለዚህም አልዓዛርና ኢታማር ብቻ አባታቸው አሮን በሕይወት በነበረበት ዘመን ሁሉ በክህነት ያገለግሉ ነበር። #ዘሌ. 10፥1-2፤ ዘኍ. 26፥61።
የሌዋውያን ተግባር
5እግዚአብሔር ሙሴን እንዲህ አለው፤ 6“የሌዊን ነገድ አቅርበህ ለካህኑ አሮን አገልጋዮች እንዲሆኑ መድባቸው፤ 7እነርሱም አሮንንና መላውን ማኅበር በመገናኛው ድንኳን በማገልገል ተግባራቸውን ይፈጽማሉ። 8በመገናኛው ድንኳን ውስጥ ለሚገኙ መገልገያ ዕቃዎች ኀላፊዎች ይሆናሉ። እስራኤላውያንንም በድንኳኑ ውስጥ በማገልገል ተግባራቸውን ይፈጽማሉ። 9ከእስራኤላውያን ሁሉ ተለይተው ለአሮንና ለልጆቹ ያገለግሉ ዘንድ ሌዋውያንን መድባቸው። 10የክህነቱንም ሥራ ያከናውኑ ዘንድ አሮንንና ልጆቹን ሹማቸው፤ ከእነርሱ በቀር ሌላ ሰው ይህን ሥራ ለማከናወን ቢሞክር በሞት ይቀጣ።”
11እግዚአብሔር ሙሴን እንዲህ አለው፤ 12-13“እነሆ ሌዋውያን የእኔ አገልጋዮች ናቸው፤ የግብጻውያንን በኲር ሁሉ በገደልኩ ጊዜ ከያንዳንዱ እስራኤላዊ የሚወለደውን በኲርና ከእንስሶቹም በኲር የሆነውን ሁሉ ለእኔ የተለየ እንዲሆን አድርጌ ነበር፤ አሁን ግን በኲር ሆነው የሚወለዱትን ወንዶች ልጆች የራሴ በማድረግ ፈንታ ሌዋውያንን መርጬአለሁ፤ እነርሱ የእኔ አገልጋዮች ይሆናሉ፤ እኔ እግዚአብሔር ነኝ።” #ዘፀ. 13፥2።
የሌዋውያን መቈጠር
14እግዚአብሔር ሙሴን በሲና ተራራ ላይ እንዲህ አለው፦ 15“ሌዋውያንን በየወገናቸውና በየቤተሰባቸው መድበህ ቊጠር፤ ከተወለደ አንድ ወር የሞላውንና ከዚያ በላይ የሆነውን ወንድ ሁሉ ቊጠር።” 16ሙሴም በእግዚአብሔር ቃል እንደታዘዘው ቈጠረ። 17ሌዊ ሦስት ወንዶች ልጆች ነበሩት፤ እነርሱም ጌርሾን፥ ቀዓትና ሜራሪ ይባላሉ። 18የጌርሾንም ወንዶች ልጆች ሊብኒና ሺምዒ ይባሉ ነበር፤ 19የቀዓትም ወንዶች ልጆች ዓምራም፥ ይጽሐር፥ ኬብሮንና ዑዚኤል ይባሉ ነበር። 20የሜራሪ ወንዶች ልጆች ማሕሊናና ሙሺ ይባሉ ነበር፤ እነዚህም በየስማቸው የቤተሰብ አባቶች ነበሩ።
21የሊብኒና የሺምዒ ቤተሰቦች በጌርሾን ጐሣ ውስጥ ተጠቃለው ነበር፤ 22ዕድሜው አንድ ወር ከሆነው ሕፃን አንሥቶ የተመዘገቡት የወንዶች ብዛት ሰባት ሺህ አምስት መቶ ነበር። 23የጌርሾናውያን ወገን የሚሰፍረው ከድንኳኑ በስተጀርባ በምዕራብ በኩል ነበር። 24የጌርሾናውያን ወገን መሪ የላኤል ልጅ ኤልያሳፍ ነበር። 25በመገናኛው ድንኳን የጌርሾን ልጆች ኀላፊነት የነበረው በመገናኛው ድንኳን፥ ከውጪና ከውስጥ በኩል ባለው መሸፈኛ፥ በመግቢያው ደጃፍ መጋረጃ፥ 26በቅጥር ግቢው መጋረጃዎች፥ በድንኳኑና በመሠዊያው ዙሪያ ባለው የቅጥር ግቢው በር መጋረጃ፥ በአውታሮቹ፥ እንዲሁም ለእነርሱ መጠቀሚያ በሚሆኑ ዕቃዎች ሁሉ ላይ ነው።
27የዓምራም፥ የይጽሃር፥ የኬብሮንና የዑዚኤል ቤተሰቦች በቀዓት ጐሣ ውስጥ ተጠቃለው ነበር፤ 28አንድ ዓመትና ከዚያም በላይ የሆኑት ወንዶች ቊጥር ስምንት ሺህ ስድስት መቶ ነበር፤ እነርሱም የመገናኛውን ድንኳን ይጠብቁት ነበር። 29የቀዓት ልጆች ቤተሰቦች የሚሰፍሩት በድንኳኑ በስተደቡብ በኩል ነበር። 30የቀዓትም ጐሣ መሪ የዑዚኤል ልጅ የሆነው ኤሊጻፋን ነበር። 31የእነርሱም ኀላፊነት በቃል ኪዳኑ ታቦት፥ በገበታው፥ በመቅረዙ፥ በመሠዊያዎቹ፥ ካህናቱ በተቀደሰው ስፍራ በሚገለገሉባቸው ንዋያተ ቅድሳት፥ ወደ ቅድስተ ቅዱሳን በሚያስገባው መጋረጃ ላይ ሲሆን፥ በአጠቃላይ እነዚህን ነገሮች በሚመለከት አገልግሎት ኀላፊነቱ የእነርሱ ነበር።
32የሌዋውያን ሁሉ አለቃ የካህኑ የአሮን ልጅ አልዓዛር ነበር፤ እርሱ በተቀደሰው ስፍራ ለሚያገለግሉት ሰዎች ሁሉ የበላይ ኀላፊ ነበር።
33የማሕሊና የሙሺ ቤተሰቦች በሜራሪ ጐሣ ውስጥ ተጠቃለው ነበር። እነዚህ የሜራሪ ቤተሰቦች ናቸው። 34ከእነርሱም ዕድሜው አንድ ወር ከሆነው ሕፃን አንሥቶ፥ የተቈጠሩት የወንዶች ብዛት ስድስት ሺህ ሁለት መቶ ነበር፤ 35የሜራሪ ጐሣ መሪ የጹርኤል ልጅ አቢኤል ነበር፤ እነርሱም የሚሰፍሩት በድንኳኑ በስተሰሜን ነበር። 36የእነርሱም ኀላፊነት በድንኳኑ ተራዳዎችና በመወርወሪያዎቻቸው፥ በምሰሶቹና ምሰሶቹ በሚቆሙባቸው እግሮች፥ እንዲሁም በሌሎች የመገልገያ ዕቃዎች ላይ ሲሆን፥ በአጠቃላይ እነዚህን ነገሮች በሚመለከት ሥራ ኀላፊነቱ የእነርሱ ነበር። 37እንዲሁም በቅጥር ግቢው ዙሪያ ባሉት፥ ምሰሶች፥ የተራዳ እግሮች፥ ካስማዎችና አውታሮች ላይ ኀላፊነት ነበራቸው።
38በመገናኛው ድንኳን በስተምሥራቅ፥ በፀሐይ መውጫ በኩል የሚሰፍሩት ሙሴ አሮንና የአሮን ልጆች ነበሩ፤ በመቅደሱ ውስጥ ስለ እስራኤል ሕዝብ ለሚፈጸም ማንኛውም ዐይነት የአገልግሎት ሥነ ሥርዓት ኀላፊዎች እነርሱ ነበሩ፤ ማንም ሌላ ሰው ወደ መቅደሱ ቢቀርብ በሞት ይቀጣል። 39እግዚአብሔር ባዘዛቸው መሠረት ሙሴና አሮን ዕድሜው አንድ ወር ከሆነው ሕፃን አንሥተው በየቤተሰባቸው የመዘገቡአቸው ሌዋውያን ወንዶች በሙሉ ኻያ ሁለት ሺህ ነበሩ።
ሌዋውያን በኲር ሆነው ለሚወለዱ እስራኤላውያን ምትክ መሆናቸው
40እግዚአብሔር ሙሴን እንዲህ አለው፤ “በኲር ሆነው የተወለዱትን የእስራኤላውያን ወንዶች ልጆች ዕድሜአቸው አንድ ወርና ከዚያም በላይ የሆነውን ቈጥረህ በየስማቸው መዝግብ፤ 41በእስራኤል የበኲር ልጆች ሁሉ ምትክ ሌዋውያንን እንዲሁም በእስራኤላውያን የእንስሶች በኲር ሁሉ ምትክ የሌዋውያንን እንስሶች ውሰድ፤ እኔ እግዚአብሔር ነኝ።” 42ሙሴም እግዚአብሔር እንዳዘዘው ከእስራኤላውያን መካከል በኲር ሆኖ የተወለደውን ሁሉ ቈጠረ። 43ዕድሜአቸው አንድ ወርና ከዚያ በላይ የሆናቸውን በኲር ሆነው የተወለዱትን ወንዶች ሁሉ በስማቸው ዝርዝር መሠረት ኻያ ሁለት ሺህ ሁለት መቶ ሰባ ሦስት ነበር።
44እግዚአብሔር ሙሴን እንዲህ አለው፦ 45“እንግዲህ በኲር ሆነው በሚወለዱት እስራኤላውያን ወንዶች ልጆች ምትክ ሌዋውያንን ለእኔ ለይልኝ፤ እንዲሁም በኲር ሆነው በሚወለዱት የእስራኤላውያን እንስሶች ምትክ የሌዋውያንን እንስሳት ለእኔ የተለዩ እንዲሆኑ አድርግ። 46በኲር ሆነው የተወለዱት የእስራኤላውያን ወንዶች ልጆች ብዛት፥ ከሌዋውያን ብዛት በሁለት መቶ ሰባ ሦስት ስለሚበልጥ እነዚህን ትርፍ የሆኑትን ወንዶች ልጆች በገንዘብ መዋጀት ይኖርብሃል። 47ለያንዳንዱ መዋጃ በመቅደሱ ሚዛን መሠረት አምስት ሰቅል የሚመዝን ብር ትወስዳለህ፤ አንዱ ሰቅል ኻያ ጌራ ነው (ጌራ 0.6 ግራም ነው)። #3፥47 ሰቅል፦ 11.5 ግራም 48ይህንንም የመዋጃ ገንዘብ ለአሮንና ለልጆቹ ስጥ።” 49ሙሴም በሌዋውያን ከተዋጁት የተረፉት ሁለት መቶ ሰባ ሦስት ሰዎች የተሰበሰበውን የመዋጃ ገንዘብ ተቀበለ። 50ከእስራኤላውያን በኲሮች በመቅደሱ ሚዛን መሠረት ገንዘቡን አንድ ሺህ ሦስት መቶ ሥልሳ አምስት ሰቅል ብር ወሰደ። 51እግዚአብሔር ባዘዘው ቃል መሠረት ሙሴ የመዋጃውን ገንዘብ ለአሮንና ለልጆቹ ሰጠ።

Highlight

Share

Copy

None

Want to have your highlights saved across all your devices? Sign up or sign in