ኦሪት ዘኊልቊ 2
2
የነገዶች ሰፈር አመዳደብ
1እግዚአብሔር ሙሴንና አሮንን እንዲህ አላቸው፦ 2እስራኤላውያን በየተመደቡበት ቡድን ሰንደቅ ዓላማና በየነገዳቸው ዐርማ ሥር ይሰፍራሉ፤ አሰፋፈራቸውም የመገናኛው ድንኳን በዙሪያው ሆኖ ፊታቸው ከድንኳኑ ትይዩ ይሆናል።
3ፀሐይ በሚወጣበት በስተምሥራቅ በኩል የሚሰፍሩት በይሁዳ ሥር የተመደቡት ነገዶች ናቸው። የይሁዳ ነገድ መሪም የአሚናዳብ ልጅ ነአሶን ነው። 4የእርሱም ክፍል የሰው ብዛት ሰባ አራት ሺህ ስድስት መቶ ነበር። 5በእርሱም አጠገብ የሚሰፍሩት የይሳኮር ነገድ ይሆናሉ፤ የይሳኮር መሪም የጾዓር ልጅ ናትናኤል ነበር፤ 6የእርሱም ክፍል የሰው ብዛት ኀምሳ አራት ሺህ አራት መቶ ነበር። 7ከዚያም የዛብሎን ነገድ ይቀጥላል፤ የዛብሎንም ልጆች መሪ የኬሎን ልጅ ኤልያብ ነበር። 8የእርሱም ክፍል ሰው ብዛት ኀምሳ ሰባት ሺህ አራት መቶ ነበር። 9እንደየክፍላቸው በይሁዳ ሰፈር እንዲሰፍሩ የተደረጉት ሰዎች ብዛት መቶ ሰማኒያ ስድስት ሺህ አራት መቶ ነበር። በመጀመሪያ የሚጓዘው ይህ ቡድን ነበር።
10በስተ ደቡብ በኩል በሮቤል ክፍል ዓርማ ሥር በየቡድናቸው ይሰፍራሉ፤ የሮቤል ነገድ መሪ የሸዴኡር ልጅ ኤሊጹር ነው፤ 11የእነርሱም ብዛት አርባ ስድስት ሺህ አምስት መቶ ነበር። 12በእነርሱም አጠገብ የሚሰፍሩት የስምዖን ልጆች ይሆናሉ፤ የስምዖን ነገድ መሪ የጹሪሻዳይ ልጅ ሸሉሚኤል ነው፤ 13የእነርሱም ብዛት ኀምሳ ዘጠኝ ሺህ ሦስት መቶ ነበር። 14ከዚያም የጋድ ነገድ ይቀጥላል፤ የጋድ ነገድ መሪ የደዑኤል ልጅ ኤልያሳፍ ነው፤ 15የእነርሱም ብዛት አርባ አምስት ሺህ ስድስት መቶ ኀምሳ ነበር። 16እንደየክፍላቸው በሮቤል ሰፈር እንዲሰፍሩ የተደረጉት ሰዎች ብዛት አንድ መቶ ኀምሳ አንድ ሺህ አራት መቶ ኀምሳ ነበር።
በዚህ ዐይነት የሮቤል ክፍል ሁለተኛ ተራ ተጓዥ ይሆናል።
17በመጀመሪያዎቹ ሁለት ክፍሎችና በመጨረሻዎቹ ሁለት ክፍሎች መካከል ሌዋውያን የመገናኛውን ድንኳን ይዘው ይጓዛሉ፤ እያንዳንዱም ክፍል ሰፈሩ ተለይቶ በሚታወቅበት ዓርማ ሥር ምድብ ተራውን ጠብቆ ይጓዛል።
18በስተምዕራብ በኩል በኤፍሬም ክፍል ዓርማ ሥር በየቡድናቸው ይሰፍራሉ፤ የኤፍሬም ነገድ መሪ የዓሚሁድ ልጅ ኤሊሻማዕ ነው፤ 19የእነርሱም ብዛት አርባ ሺህ አምስት መቶ ነበር።
20በእነርሱም አጠገብ የሚሰፍሩት የምናሴ ልጆች ይሆናሉ፤ የምናሴ ነገድ መሪ የጴዳጹር ልጅ ገማልኤል ነው፤ 21የእነርሱም ብዛት ሠላሳ ሁለት ሺህ ሁለት መቶ ነበር፤ 22ከዚያም የብንያም ነገድ ይቀጥላል፤ የብንያም ነገድ መሪ የጊድዖን ልጅ አቢዳን ነበር፤ 23የእነርሱም ብዛት ሠላሳ አምስት ሺህ አራት መቶ ነበር። 24እንደየክፍላቸው በኤፍሬም ሰፈር እንዲሰፍሩ የተደረጉት ሰዎች ብዛት አንድ መቶ ስምንት ሺህ አንድ መቶ ነበር። በዚህ ዐይነት የኤፍሬም ክፍል ሦስተኛ ተራ ተጓዥ ይሆናል።
25በስተ ሰሜን በኩል በዳን ክፍል ዓርማ ሥር የሚሰፍሩ ወገኖች ናቸው፤ የዳን ነገድ መሪ የዓሚሻዳይ ልጅ አሒዔዜር ነው፤ 26ብዛታቸውም ሥልሳ ሁለት ሺህ ሰባት መቶ ነበር። 27በእነርሱም አጠገብ የሚሰፍሩት የአሴር ልጆች ይሆናሉ፤ የአሴር ነገድ መሪ የዖክሪን ልጅ ፋግዒኤል ነው፤ 28የእነርሱም ብዛት አርባ አንድ ሺህ አምስት መቶ ነበር። 29ከዚያም የንፍታሌም ነገድ ይቀጥላል፤ የንፍታሌም ነገድ መሪ የዔናን ልጅ አሒራዕ ነው፤ 30የእነርሱም ብዛት ኃምሳ ሦስት ሺህ አራት መቶ ነበር። 31እንደየክፍላቸው በዳን ሰፈር እንዲሰፍሩ የተደረጉት ሰዎች ብዛት አንድ መቶ ኀምሳ ሰባት ሺህ ስድስት መቶ ነበር። በዚህ ዐይነት የዳን ክፍል የመጨረሻ ተራ ተጓዥ ይሆናል። 32እስራኤላውያን በየነገዳቸውና በየክፍላቸው የተቈጠሩት ስድስት መቶ ሦስት ሺህ አምስት መቶ ኀምሳ ነበር። 33ሌዋውያን ግን እግዚአብሔር ሙሴን ባዘዘው መሠረት፥ ከሌሎቹ የእስራኤል ሕዝብ ጋር አልተቈጠሩም።
34በዚህ ዐይነት የእስራኤል ሕዝብ እግዚአብሔር ሙሴን ባዘዘው መሠረት አደረጉ፤ እያንዳንዱ ነገድ ዓርማውን በመከተል ይሰፍር ነበር፤ እያንዳንዱም በየቤተሰቡ ተመድቦ ይጓዝ ነበር።
Currently Selected:
ኦሪት ዘኊልቊ 2: አማ05
Highlight
Share
Copy
Want to have your highlights saved across all your devices? Sign up or sign in
© The Bible Society of Ethiopia, 2005
© የኢትዮጵያ መጽሐፍ ቅዱስ ማኅበር፥ 1997