YouVersion Logo
Search Icon

መጽሐፈ ነህምያ 6

6
በነህምያ ላይ የተደረገው ሤራ መቀጠሉ
1ሰንባላጥ፥ ጦቢያ፥ ዐረባዊው ጌሼምና ሌሎችም ጠላቶቻችን የቅጽሩን ግንብ ሠርቼ መፈጸሜንና ያልተሠራ ክፍት ቦታ አለመኖሩን ሰሙ፤ ይሁን እንጂ በቅጽር በሮቹ ላይ መዝጊያዎችን አላቆምኩም ነበር። 2ከዚህም የተነሣ ሰንባላጥና ጌሼም በተለይ ኦኖ ተብሎ በሚጠራው ሜዳ ከሚገኙት መንደሮች በአንዲቱ እንድንገናኛቸው መልእክት ላኩብኝ፤ ይህም እኔን ለመጒዳት በተንኰል የተዶለተ ዘዴ ነበር። 3እኔም “አስቸኳይ ሥራ ስላለብኝ ተግባሬን አቁሜ እናንተ ወዳላችሁበት ስፍራ መውረድ አልችልም፤ ወደ እናንተ ለመምጣት ተብሎ ለምን ሥራው ይቆማል?” አልኳቸው።
4ያንኑም ዐይነት መልእክት በማከታተል አራት ጊዜ ሲልኩብኝ እኔም ተመሳሳዩን መልስ ሰጠኋቸው።
5ከዚህም በኋላ ሰንባላጥ ከአገልጋዮቹ አንዱን ለአምስተኛ ጊዜ መልእክት አስይዞ ወደ እኔ ላከ፤ የተላከውም ግልጥ ደብዳቤ እንዲህ የሚል ነበር፦
6“አንተና ወገኖችህ የሆኑት አይሁድ ዐመፅ ለማስነሣት ማቀዳችሁንና የቅጽር ግንቦችንም የምትሠሩት በዚሁ ምክንያት መሆኑን ጐረቤቶቻችን በሆኑ ሕዝቦች ዘንድ እንደሚወራ ጌሼም ነግሮኛል፤ ከዚህም ሌላ አንተ ራስህን ለማንገሥ ማሰብህንና፥ 7የይሁዳ ንጉሥ መሆንህንም በኢየሩሳሌም አንዲያውጁ፥ ነቢያት መሾምህን ጌሼም ጨምሮ ነግሮኛል፤ ይህንንም ወሬ ንጉሠ ነገሥቱ እንደሚሰማ የተረጋገጠ ነው፤ ስለዚህ አንተና እኔ ተገናኝተን በጒዳዩ ላይ ብንወያይበት ይሻላል።”
8እኔም “ይህ የምትለው ነገር ሁሉ ምንም እውነትነት የሌለውና አንተ ራስህ የፈለሰፍከው ሐሰት ነው” ብዬ መለስኩለት።
9በዚህም ዐይነት ሥራውን እንድናቆም ለማድረግ ያስፈራሩን ነበር፤ ስለዚህም “እግዚአብሔር አምላክ ሆይ! እባክህ አበርታኝ!” ስል ጸለይኩ።
10በዚህም ጊዜ ከቤቱ እንዳይወጣ ተዘግቶበት ወደነበረው የመሄጣብኤል የልጅ ልጅ ወደ ሆነው ወደ ደላያ ልጅ ሸማዕያ ዘንድ ሄድኩ፤ እርሱም “በሌሊት ሊገድሉህ ስለሚመጡ አንተና እኔ ወደ እግዚአብሔር ቤተ መቅደስ ውስጥ ገብተን በሮቹን በመዝጋት እንደበቅ” አለኝ።
11እኔ ግን “እንደ እኔ ያለ ሰው ሸሽቶ አይደበቅም፤ እንደ እኔ ያለ ሰው ሕይወቱን ለማዳን ወደ ቤተ መቅደስ መግባት አለበትን? ይህን ከቶ አላደርገውም” ስል መለስኩለት።
12በነገሩ ሳሰላስል፥ እርሱ እንዲህ ዐይነቱን የሐሰት ማስጠንቀቂያ እንዲሰጠኝ ጦቢያና ሰንባላጥ በገንዘብ የደለሉት እንጂ ሸማዕያ ከእግዚአብሔር የተላከ ነቢይ አለመሆኑን ተገነዘብኩ። 13ይህን ነገር በማድረግ በደል እንድሠራና በእኔም ላይ ክፉ ወሬ በማውራት እያስፈራራ ስሜን በማጥፋት ያዋርደኝ ዘንድ ጉቦ ተቀብሎ ነበር።
14እኔም “አምላክ ሆይ፥ ጦቢያና ሰንባላጥ ያደረጉትን ሁሉ ተመልከት፤ ፍረድባቸውም፤ ኖዓድያ የተባለችው ሴት ነቢይትና ሌሎቹም ነቢያት እኔን ለማስፈራራት ያደረጉትን ሁሉ አስብ” በማለት ጸለይኩ።
የቅጽር ግንቡ ሥራ ከፍጻሜ መድረስ
15ሥራው ከተጀመረ ከኀምሳ ሁለት ቀኖች በኋላ ኤሉል ተብሎ የሚጠራው ወር በገባ በሃያ አምስተኛው ቀን የቅጽሩ ሥራ በሙሉ ተጠናቀቀ፤ 16በዙሪያችን የሚኖሩ አሕዛብ ጠላቶቻችን ይህን በሰሙ ጊዜ ሥራው አስደናቂ ሥራ መሆኑን ስለ ተገነዘቡና፤ ሥራውም በእግዚአብሔር ርዳታ የተከናወነ መሆኑን ስለ ተረዱ እጅግ ፈርተው ተደናገጡ።
17-18የኢራሕ ልጅ ሴኬን የጦብያ አማች ስለ ነበርና ልጁ ዮሐናንም የቤሬክያን ልጅ የሜሱላንን ሴት ልጅ አግብቶ ስለ ነበረ ከይሁዳ ብዙዎቹ ከእርሱ ጋር ተማምለው ነበር፤ እንዲሁም የይሁዳ ባለ ሥልጣኖች በዚያው ወቅት ከጦብያ ጋር ብዙ የደብዳቤዎች መለዋወጥ ያደርጉ ነበር። 19ጦቢያ ያደረገውን መልካም ነገር በማጋነን በፊቴ እንኳ ሳይቀር ይናገሩለት ነበር፤ እኔም የምለውን ሁሉ ለእርሱ ይነግሩት ነበር፤ ከዚህም የተነሣ እርሱ እኔን ለማስፈራራት ደብዳቤዎችን ከመላክ አልተቈጠበም።

Highlight

Share

Copy

None

Want to have your highlights saved across all your devices? Sign up or sign in

Videos for መጽሐፈ ነህምያ 6