YouVersion Logo
Search Icon

መጽሐፈ ነህምያ 5

5
በድኾች ላይ የደረሰ በደል
1በአንድ ወቅት ወንዶችና ሴቶች ወገኖቻቸው በሆኑ የአይሁድ አለቆቻቸው ላይ ከባድ አቤቱታ አሰሙ። 2ከእነርሱም አንዳንዶቹ “ብዙ ቤተሰብ ስላለን ሕይወታችንን ለማትረፍ የሚያስችለን እህል እንፈልጋለን” አሉ።
3ሌሎቹ ደግሞ “ከደረሰብን ብርቱ ራብ ሕይወታችንን ለማትረፍ የሚያስችል እህል ለማግኘት ስንል እርሻችንን፥ የወይን ተክላችንንና ቤታችንን ሁሉ መያዣ አድርገን እስከ መስጠት ደርሰናል” ይሉ ነበር።
4ሌሎችም ደግሞ “ስለ እርሻችንና ስለ ወይን ተክላችን መንግሥት የጠየቀንን ግብር ለመክፈል የገንዘብ ብድር ተበድረናል፤ 5ከአይሁድ ወገኖቻችን ጋር ዘራችን አንድ ነው፤ የእኛ ልጆች ከእነርሱ ልጆች የሚለዩበት ምንም ነገር የለም፤ ይሁን እንጂ የገዛ ልጆቻችንን ለባርነት አሳልፈን ለመስጠት ተገደናል፤ እንዲያውም ከሴቶች ልጆቻችን አንዳንዶቹ ባሪያዎች ሆነዋል፤ ነገር ግን እርሻችንና የወይን ተክል ቦታችን ስለ ተወሰዱ ኀይል የሌለን ሆነናል” በማለት አቤቱታ አሰሙ።
6እኔም አቤቱታቸውን በሰማሁ ጊዜ ተቈጣሁ፤ 7ላደርገው የሚገባኝንም በልቤ ወስኜ የሕዝቡ መሪዎች የሆኑትን ባለሥልጣኖች “እናንተ እኮ የገዛ ወንድሞቻችሁን በመጨቈን አራጣ ታስከፍላላችሁ!” በማለት በቊጣ ገሠጽኳቸው። #ዘፀ. 22፥25፤ ዘሌ. 25፥35-37፤ ዘዳ. 23፥19-20።
ለችግሩም መፍትሔ ለማግኘት ሕዝቡን በአንድነት ሰብስቤ 8“ለአሕዛብ ሕዝቦች የተሸጡ አይሁድ ወገኖቻችንን ራሳችን ልንቤዣቸው በማሰብ የሚቻለንን ሁሉ አደረግን፤ እናንተ ደግሞ እነሆ፥ የገዛ ወንድሞቻችሁ የሆኑት አይሁድን ወገኖቻቸው ለሆናችሁት ለእናንተ ባርያዎች አድርገው ራሳቸውን እንዲሸጡላችሁ በማድረግ ላይ ትገኛላችሁ!” ብዬ ገሠጽኳቸው፤ መሪዎቹም የሚመልሱት ቃል አጥተው ዝም አሉ።
9እኔ ግን ንግግሬን በመቀጠል እንዲህ አልኳቸው፤ “ያደረጋችኹት ነገር ትክክል አይደለም! እግዚአብሔርን መፍራትና ትክክል የሆነውን ነገር ማድረግ በተገባችሁ ነበር፤ ይህን አድርጋችሁ ቢሆን ኖሮ፥ አሕዛብ ጠላቶቻችን ባልተዘባበቱብንም ነበር። 10ሕዝቡ ከእኔ ገንዘብም ሆነ እህል እንዲበደሩ ፈቅጄላቸዋለሁ፤ የሥራ ባልደረቦቼና የእኔ አገልጋዮች የሆኑት ሁሉ እንዲሁ ያደርጉ ዘንድ ፈቅጃለሁ፤ እንግዲህስ ‘የተበደራችሁትን ዕዳ ክፈሉን’ ብለን መጠየቅ ይቅርብን፤ 11ገንዘብም ሆነ እህል ወይም ወይንና የወይራ ዘይት ቢሆን ያበደራችሁትን ሁሉ ወለዱን ተዉላቸው፤ እርሻቸውን የወይንና የወይራ ዘይት ተክላቸውንና ቤታቸውን ሁሉ አሁኑኑ መልሱላቸው።”
12መሪዎቹም “እንዳዘዝከን እናደርጋለን፤ የተወሰደባቸውን ሀብትና ንብረት ሁሉ እንመልስላቸዋለን፤ የተበደሩትንም ዕዳ ክፈሉ ብለን አንጠይቃቸውም” ሲሉ መለሱልኝ።
እኔም ካህናቱን ወደ ውስጥ ጠርቼ፥ መሪዎቹ የገቡትን ቃል ይፈጽሙ ዘንድ እንዲያስምሉአቸው አደረግሁ። 13ለብሼው የነበረውንም ልብስ በማውለቅ አራግፌ “ከእናንተ መካከል ማንም ሰው የገባውን የተስፋ ቃል ቢያፈርስ እግዚአብሔር እንደዚህ ያድርገው፤ ቤት ንብረቱንም ወስዶ ባዶ እጁን ያስቀረው” አልኳቸው።
በዚያም የተገኘው ሰው ሁሉ በአንድ ድምፅ “አሜን!” በማለት እግዚአብሔርን አመሰገነ፤ መሪዎቹም የገቡትን ቃል ፈጸሙ።
ነህምያ ከራስ ወዳድነት ነጻ ስለ መሆኑ
14አርጤክስስ ንጉሠ ነገሥት ከሆነበት ከኻኛው ዓመት ጀምሮ ሠላሳ ሁለት ዓመት እስከ ሆነው ድረስ እኔ የይሁዳ ገዢ በሆንኩበት የዐሥራ ሁለት ዓመት ጊዜ ውስጥ ዘመዶቼም ሆኑ ወይም እኔ ራሴ ለአንድ አገረ ገዢ የሚገባውን ምግብ አልበላንም። 15ከእኔ በፊት የሕዝብ ገዢ ሆኖ የተሾመው ሁሉ በሕዝቡ ላይ ከባድ ሸክም በመሆን፥ በየቀኑ ለምግብና ለመጠጥ የሚሆን አርባ ብር ያስከፍላቸው ነበር፤ የገዢዎቹም አገልጋዮች እንኳ በሕዝቡ ላይ ሠልጥነውባቸው ይጨቊኑአቸው ነበር፤ እኔ ግን እግዚአብሔርን ስለምፈራ እንደዚያ አላደረግሁም። 16ያለኝን ኀይል ሁሉ የኢየሩሳሌምን ቅጽር እንደገና በማሳነጽ ተግባር ላይ አዋልኩት እንጂ ለግሌ ምንም ዐይነት ንብረት አልሰበሰብኩም፤ አገልጋዮቼም ሁሉ በዚህ ሥራ ተባበሩኝ፤ 17ከአካባቢ አገሮች ወደ እኔ ከመጡት ሕዝቦች ሌላ በየዕለቱ ከእኔ ጋር የሚመገቡ አይሁድና የመሪዎቻቸው ቊጥር አንድ መቶ ኀምሳ ነበር። 18በየዕለቱ አንድ በሬ፥ ስድስት ምርጥ በጎችና ብዙ ዶሮች ታርደው ይዘጋጁልኝ ነበር፤ በተጨማሪም በየዐሥር ቀን አንድ ጊዜ የወይን ጠጅ ግብዣ አደርግላቸው ነበር፤ ነገር ግን በሕዝቡ ላይ የተጣለውን ከባድ ሸክም ስለማውቅ፥ ለአገረ ገዢነት የሚገባውን አበል አልጠየቅሁም።
19አምላኬ ሆይ፥ ለዚህ ሕዝብ ያደረግኹትን ቅንነት ሁሉ በማሰብ ቸርነት አድርግልኝ።

Highlight

Share

Copy

None

Want to have your highlights saved across all your devices? Sign up or sign in