መጽሐፈ ነህምያ 2
2
የነህምያ ወደ ኢየሩሳሌም መሄድ
1አርጤክስስ በነገሠ በሃያኛው ዓመት ኒሳን ተብሎ በሚጠራው ወር ከዕለታት በአንዱ ቀን ለንጉሠ ነገሥቱ የወይን ጠጅ አቀረብኩለት፤ ከዚያች ቀን በቀር ከዚህ ቀደም በፊቴ ላይ ምንም ዐይነት የሐዘን ምልክት አይቶብኝ አያውቅም ነበር። 2ስለዚህም “አንዳች የልብ ሐዘን ቢደርስብህ ነው እንጂ ሳትታመም እንዴት ይህን ያኽል በፊትህ የሐዘን ምልክት ይታያል?” ሲል ጠየቀኝ።
እኔም እጅግ በመፍራት፥ 3“ንጉሠ ነገሥቱ ለዘለዓለም ይኑር! የቀድሞ አባቶቼ የተቀበሩባት ከተማ ፍርስራሽ ሆና ስትቀርና የቅጽሮችዋም በሮች በእሳት ሲወድሙ እንዴት አላዝንም?” ስል መለስኩለት። #2ነገ. 25፥8-10፤ 2ዜ.መ. 36፥19፤ ኤር. 52፥12-14።
4ንጉሠ ነገሥቱም “ታዲያ፥ አሁን የምትፈልገው ምንድን ነው?” ሲል ጠየቀኝ፤ እኔም ወደ ሰማይ አምላክ ከጸለይሁ በኋላ፥ 5ንጉሠ ነገሥቱን፦ “ንጉሥ ሆይ፥ በአንተ ፊት ሞገስን አግኝቼ ከሆነና ጥያቄዬን ከተቀበልከኝ፥ የቀድሞ አባቶቼ ወደተቀበሩባት በይሁዳ ወደምትገኘው ወደ ኢየሩሳሌም ከተማ እንድሄድና ከተማይቱን እንደገና መሥራት እንድችል ፍቀድልኝ” ብዬ ለመንኩት።
6በዚህን ጊዜ ንግሥቲቱ በንጉሠ ነገሥቱ አጠገብ ተቀምጣ ነበር፤ ንጉሠ ነገሥቱም ጥያቄዬን በመቀበል፦ “ጒዞህ ምን ያኽል ጊዜ ይወስድብሃል? እስከ መቼስ ትመለሳለህ?” ብሎ ጠየቀኝ። እኔም የሚወስድብኝን ጊዜና መቼ እንደምመለስ ነገርኩት።
7ከዚያም በመቀጠል ወደ ይሁዳ ማለፍ እንዲፈቅዱልኝ ከኤፍራጥስ ወንዝ በስተ ምዕራብ በሚገኘው ክፍለ ሀገር ላሉት አገረ ገዢዎች የይለፍ ደብዳቤ እንዲሰጠኝ ለንጉሠ ነገሥቱ ልመና አቀረብኩ፤ 8እንዲሁም አሳፍ የተባለው፥ የመንግሥት ደን ጠባቂ የሆነው፥ ለቤተ መቅደሱ ቅጽር በርና ለከተማይቱ ቅጽር በሮች ሁሉ እኔም ለማርፍበት ቤት ጭምር መጠበቂያዎች ማሠሪያ የሚሆን የጥድና የዝግባ እንጨት ለመቊረጥ እንዲፈቅድልኝ የሚያዝ ደብዳቤ እንዲሰጠኝም ጠየቅሁ፤ እግዚአብሔርም በቸርነቱ ስለ ረዳኝ፥ ንጉሠ ነገሥቱ የጠየቅሁትን ነገር ሁሉ ሰጠኝ።
9ንጉሠ ነገሥቱም ጥቂት የጦር መኰንኖችና ፈረሰኞች ከእኔ ጋር እንዲሄዱ አደረገ፤ እኔም ከኤፍራጥስ በስተ ምዕራብ ወደሚገኘው ክፍለ ሀገር ጒዞዬን ቀጠልኩ፤ እዚያ እንደ ደረስኩም ደብዳቤዎቹን ለአገረ ገዢዎቹ አስረከብኩ፤ 10ነገር ግን የቤትሖሮን ከተማ ነዋሪ የሆነው ሰንባላጥና የዐሞን ክፍለ ሀገር ባለሥልጣን የሆነው ጦቢያ ለእስራኤል ሕዝብ ደኅንነት መልካም ነገር የሚሠራ ሰው መምጣቱን ሰምተው እጅግ ተቈጡ።
11እኔም ወደ ኢየሩሳሌም ሄጄ ሦስት ቀን እዚያ ከቈየሁ በኋላ 12ለኢየሩሳሌም ስለማከናውነው ሥራ ሁሉ እግዚአብሔር ለእኔ የገለጠልኝን ምሥጢር ለማንም ሳልናገር ቈየሁ፤ ከዚያም በኋላ ከጓደኞቼ ጥቂቶቹን በማስከተል፥ በእኩለ ሌሊት ተነሥቼ ሄድኩ፤ የነበረን የጭነት እንስሳ እኔ የተቀመጥኩበት ብቻ ነበር፤ 13በሸለቆ ቅጽር በር ወጥቼ የዘንዶ ምንጭ ተብሎ የሚጠራውን ስፍራ በማለፍ፥ በስተ ደቡብ ወደሚገኘው የጒድፍ መጣያ ተብሎ ወደሚጠራው ስፍራ ሄድኩ፤ ጊዜውም ገና ሌሊት ነበር፤ በማልፍበትም ጊዜ የፈራረሱትን የከተማይቱን ቅጽሮችና በእሳት የወደሙትን የቅጽር በሮች ጐበኘሁ። 14ቀጥሎም ከከተማይቱ በስተ ምሥራቅ በኩል በሰሜን ወደሚገኘው “የውሃ ምንጭ ቅጽር በር” ተብሎ በሚጠራው ስፍራና ወደ ንጉሡ ኲሬ ሄድኩ፤ ነገር ግን ተቀምጬበት የነበረው እንስሳ የፍርስራሹን ክምር ለማለፍ የሚያስችለው መንገድ ማግኘት አልቻለም። 15ስለዚህ ሌሊቱን ወደ ቄድሮን ወንዝ በመውረድ፥ ቅጽሮችን እየጐበኘሁ አልፌ ሄድኩ፤ በመጨረሻም በዚያው በመጣሁበት መንገድ ተመልሼ በሸለቆው ቅጽር በር በኩል ወደ ከተማይቱ ገባሁ።
16በሀገሪቱ ከነበሩትም ባለሥልጣኖች መካከል የት እንደ ነበርኩና ምን እንዳደረግሁ ያወቀ ማንም አልነበረም፤ ከዚህም በቀር ከአይሁድ ጓደኞቼ ይኸውም ከካህናቱ፥ ከመሪዎቹም ሆነ ከባለሥልጣኖቹ ወይም የሥራው ተካፋዮች ከሚሆኑት ሌሎች ሰዎች ለአንዱም እንኳ የነገርኩት ምንም ነገር አልነበረም። 17ከዚህ በኋላ ግን “እንግዲህ ያለውን ችግር ሁሉ ተመልከቱት! ኢየሩሳሌም የፍርስራሽ ክምር ሆናለች፤ የቅጽር በሮችዋም በእሳት ወድመዋል፤ ስለዚህ ተነሥተን የከተማይቱን ቅጽሮች እንሥራ፤ የደረሰብንንም ኀፍረት እናስወግድ” አልኳቸው። 18ቀጠል አድርጌም እግዚአብሔር ከእኔ ጋር መሆኑንና እንዴትም እንደ ረዳኝ፥ ንጉሠ ነገሥቱም የነገረኝን ሁሉ ገለጥሁላቸው።
እነርሱም “እንደገና መሥራቱን እንጀምር!” ካሉኝ በኋላ፥ ይህን በጎ ሥራ ለመጀመር ተዘጋጁ።
19ነገር ግን ሰንባላጥና ጦቢያ እንዲሁም ጌሼም ተብሎ የሚጠራው አንድ የዐረብ ተወላጅ እኛ ያወጣነውን የሥራ ዕቅድ በሰሙ ጊዜ በእኛ ላይ እየዘበቱ በመሳቅ “ይህ የምትሠሩት ሥራ ምንድን ነው? ወይስ በንጉሠ ነገሥቱ ላይ ማመፅ ትፈልጋላችሁን?” ሲሉ ጠየቁን።
20እኔም “የሰማይ አምላክ ሥራችንን ለማከናወን ይረዳናል፤ እኛ የእርሱ አገልጋዮች ነን፤ ስለዚህም ሥራውን እንጀምራለን፤ እናንተ ግን በኢየሩሳሌም ምንም ዐይነት ንብረት የማግኘት መብት ሆነ የታሪክ መታሰቢያነት አይኖራችሁም” ብዬ መለስኩላቸው።
Currently Selected:
መጽሐፈ ነህምያ 2: አማ05
Highlight
Share
Copy
Want to have your highlights saved across all your devices? Sign up or sign in
© The Bible Society of Ethiopia, 2005
© የኢትዮጵያ መጽሐፍ ቅዱስ ማኅበር፥ 1997