YouVersion Logo
Search Icon

መጽሐፈ ነህምያ 1

1
ነህምያ ስለ ኢየሩሳሌም የነበረው ጭንቀት
1የሐካልያ ልጅ ነህምያ የተናገረው ቃል ይህ ነው፦
አርጤክስስ የፋርስ ንጉሠ ነገሥት በሆነ በሃያኛው ዓመት ኪስሌው ተብሎ በሚጠራው ወር እኔ ነህምያ ዋና ከተማ በሆነችው በሱሳ ውስጥ ነበርኩ። 2ከወንድሞቼ አንዱ ሐናኒ ተብሎ የሚጠራው ሌሎች ሰዎችን አስከትሎ ከይሁዳ ወደ እኔ መጣ፤ እኔም ስለ ኢየሩሳሌምና ወደ ባቢሎን ተማርከው ከመወሰድ ስለ ተረፉትና በሕይወት ስላሉት አይሁድ ሁኔታ ጠየቅኋቸው። 3እነርሱም “ተማርከው ወደ ባቢሎን ሳይወሰዱ የቀሩትና በሕይወት ያሉት አይሁድ በታላቅ ችግርና ኀፍረት ላይ ወድቀው ይገኛሉ፤ የኢየሩሳሌምም ቅጽሮች ፈራርሰው ወድቀዋል፤ የቅጽር በሮቹም በእሳት ጋይተዋል” ሲሉ መለሱልኝ። 4እኔም ይህን ሁሉ በሰማሁ ጊዜ ተቀምጬ አለቀስኩ። ለብዙ ቀኖችም በጾምና በሐዘን ቈየሁ፤ ወደ እግዚአብሔርም እንዲህ ስል ጸለይኩ፦
5“እግዚአብሔር የሰማይ አምላክ ሆይ! አንተ ታላቅ ነህ፤ እኛም በፍርሃት በፊትህ እንቆማለን፤ አንተ ከሚወዱህና ትእዛዞችህንም ከሚጠብቁ ሁሉ ጋር ቃል ኪዳንህን ትጠብቃለህ። 6እግዚአብሔር ሆይ! አገልጋዮችህ ስለ ሆኑት የእስራኤል ሕዝብ ደኅንነት ቀንና ሌሊት የማቀርበውን ጸሎቴን ስማ፤ እኔንም አስበኝ፤ እኛ እስራኤላውያን የሠራነውንም ኃጢአት እናዘዛለሁ፤ በእርግጥም እኔና የቀድሞ አባቶቼ በደል ሠርተናል። 7በአንተ ላይ በማመፅ ትእዛዞችህን ሁሉ ተላልፈናል፤ በአገልጋይህ በሙሴ አማካይነት የሰጠኸንንም ሕግና ሥርዓት አልጠበቅንም። 8-9‘እናንተ የእስራኤል ልጆች ሆይ፥ እኔን በእምነት ባትከተሉ በአረማውያን ሕዝቦች መካከል እበትናችኋለሁ፤ ነገር ግን ወደ እኔ ተመልሳችሁ ያዘዝኳችሁን ትእዛዞች ብትፈጽሙ እስከ ምድር ዳርቻ ድረስ የተበታተናችሁ ብትሆኑም እንኳ ለስሜ መጠሪያ እንዲሆን ወደ መረጥሁት ስፍራ እንደገና በመሰብሰብ መልሼ አመጣችኋለሁ’ ስትል ለሙሴ የተናገርከውን ቃል አስብ። #ዘሌ. 26፥33። #ዘዳ. 30፥1-5።
10“እግዚአብሔር ሆይ! እነዚህ የአንተ አገልጋዮችና የገዛ ሕዝብህ ናቸው፤ ከዚህ በፊትም በታላቁ ኀይልህና በብርቱ ክንድህ በመታደግ አድነሃቸዋል። 11እነሆ፥ አሁንም የእኔን ጸሎት ስማ፤ አንተን ማክበር የሚወዱትን የሌሎችንም አገልጋዮችህን ጸሎት አድምጥ፤ ዛሬ ልሠራው ያቀድኩት ይሳካልኝ ዘንድ የንጉሠ ነገሥቱን ልብ በማራራት እርዳኝ።”
እነሆ፥ እኔ በዚህ ጊዜ የንጉሠ ነገሥቱ ወይን ጠጅ አሳላፊ ነበርኩ።

Highlight

Share

Copy

None

Want to have your highlights saved across all your devices? Sign up or sign in