YouVersion Logo
Search Icon

መጽሐፈ ነህምያ 13

13
የእስራኤላውያን ከባዕዳን ሕዝቦች መለየት
1የኦሪት ሕግ ከፍ ባለ ድምፅ በተነበበላቸው ጊዜ ሰዎቹ ሲያዳምጡ “ሞአባውያንና ዐሞናውያን ከእግዚአብሔር ሕዝብ ጋር ለዘለዓለም አይቀላቀሉ” ከሚለው አንቀጽ ደረሱ። 2ይህም ትእዛዝ የተሰጠበት ምክንያት እስራኤላውያን ከግብጽ ምድር በወጡበት ጊዜ በጒዞ ላይ ሳሉ ሞአባውያንና ዐሞናውያን ምግብና ውሃ ስለ ከለከሉአቸው ነበር፤ ይልቁንም ይህን በማድረግ ፈንታ ለበለዓም ገንዘብ ሰጥተው የእስራኤልን ሕዝብ እንዲረግምላቸው አድርገው ነበር፤ እግዚአብሔር ግን መርገሙን ወደ በረከት ለወጠው። #ዘዳ. 23፥5። #ዘኍ. 22፥1-6። 3ይህም ሕግ ሲነበብ እስራኤላውያን በሰሙት ጊዜ ባዕዳን የሆኑ ሕዝቦችን ከመካከላቸው አስወገዱ።
ነህምያ ያደረገው ተሐድሶ
4የቤተ መቅደስ ዕቃ ግምጃ ቤት ኀላፊ የሆነው ካህኑ ኤልያሺብ ለረጅም ጊዜ ከጦቢያ ጋር የጠበቀ ግንኙነት ነበረው፤ 5ከዚህም የተነሣ የእህል መባ፥ ዕጣን፥ የቤተ መቅደስ ንዋያተ ቅድሳት፥ ከእህል፥ ከወይን ጠጅ፥ ከወይራ ዘይት ተውጣጥቶ ለሌዋውያኑ ለቤተ መቅደስ መዘምራንና ለዘብ ጠባቂዎች የሚሰጠው ዐሥራትና ለካህናቱ የሚሰጥ መባ ሁሉ እንዲቀመጥበት ታስቦ በተለይ የተሠራውን ታላቅ ክፍል ጦቢያ በመኖሪያነት ይጠቀምበት ዘንድ ኤልያሺብ ፈቅዶለት ነበር። 6ይህም ሁሉ በሚሆንበት ጊዜ እኔ በኢየሩሳሌም አልነበርኩም፤ አርጤክስስ የባቢሎን ንጉሠ ነገሥት በሆነ በሠላሳ ሁለተኛው ዓመት ወደ ባቢሎን ተመልሼ ሄጄ ነበር፤ ከጥቂት ጊዜ በኋላም ከንጉሡ ፈቃድ ጠይቄ፥ 7ወደ ኢየሩሳሌም ተመለስኩ፤ እዚያም እንደ ደረስኩ ኤልያሺብ ለጦቢያ በቤተ መቅደሱ ግቢ ውስጥ አንድ መኖሪያ ክፍል የፈቀደለት መሆኑን ሰማሁ፤ 8በቊጣ ተነሥቼ የጦቢያን ንብረት ሁሉ ከክፍሉ በማስወጣት አሽቀንጥሬ ጣልኩ፤ 9ክፍሎቹም በሕጉ መሠረት በሥርዓት እንዲነጹና የቤተ መቅደሱም ንዋያተ ቅድሳት፥ የእህል መባውና ዕጣኑ ወደዚያ ተመልሰው እንዲገቡ ትእዛዝ ሰጠሁ።
10እንዲሁም አገልግሎቱን የሚፈጽሙት የቤተ መቅደሱ መዘምራንና ሌሎችም ሌዋውያን ኢየሩሳሌምን ለቀው በመውጣት ወደየእርሻቸው ተመልሰው መግባታቸውን ተገነዘብኩ፤ ይህም የሆነበት ምክንያት ሕዝቡ ለመዘምራኑና ለሌዋውያኑ በቂ መተዳደሪያ ባለመስጠታቸው ነበር። 11ቤተ መቅደሱም ይህን ያኽል ቸል እስኪባል ዝም ብለው በመመልከታቸው ባለሥልጣኖችን ገሠጽኩ፤ ሌዋውያኑንና መዘምራኑንም ወደ ቤተ መቅደስ መልሼ በማምጣት ሥራቸውን እንዲቀጥሉ አደረግሁ፤ 12ከዚህም በኋላ እስራኤላውያን ሁሉ እንደገና ከእህልና ከወይን ጠጅ፥ ከወይራ ዘይትም የሚፈለግባቸውን ከዐሥር አንድ እያወጡ ወደ ቤተ መቅደስ ዕቃ ግምጃ ቤት ማምጣት ጀመሩ። 13ለዕቃ ግምጃ ቤቱም ኀላፊነት ካህኑን ሼሌምያን፥ የሕግ ምሁሩን ሳዶቅንና ሌዋዊውን ፐዳያን መደብሁ፤ የማታንያ የልጅ ልጅ የሆነው የዛኩር ልጅ ሐናንም የእነርሱ ረዳት ነበር፤ እነዚህም ሰዎች ለሥራ ጓደኞቻቸው የሚሆነውን መተዳደሪያ ለማከፋፈል ታማኞች ነበሩ።
14አምላኬ ሆይ፥ ለቤተ መቅደስህና ለአገልግሎቱ መቃናት ስል እነዚህን ሁሉ በታማኝነት ማድረጌን በማሰብ ቸርነት አድርግልኝ።
15በእነዚያም ቀኖች በይሁዳ በሰንበት ቀን ወይን የሚጨምቁ፥ እህልን፥ ወይን ጠጅን፥ የወይን ዘለላን፥ በለስን፥ ሌሎችንም ነገሮች ሁሉ በአህያ የሚጭኑ መሆናቸውን አየሁ፤ እነዚህንም ሁሉ በሰንበት ቀን ወደ ኢየሩሳሌም አምጥተው እንዳይሸጡ አስጠነቀቅኋቸው። 16ከዚህም ጋር በኢየሩሳሌም የሚኖሩ የጢሮስ ተወላጆች ዓሣና ሌሎች ሸቀጦችን በየዐይነቱ በሰንበት ቀን ወደ ከተማይቱ እያስገቡ ለይሁዳ ሕዝብ ይሸጡ ነበር፤ 17እኔም የአይሁድ መሪዎችን በመገሠጽ እንዲህ አልኳቸው፥ “የምታደርጉትን ክፉ ነገር ሁሉ ተመልከቱ! እነሆ ሰንበትን እያረከሳችኋት ነው፤ 18አምላካችን በእኛና በከተማይቱ ላይ ይህን ጥፋት ያመጣው የቀድሞ አባቶቻችሁ ይህን ጥፋት ስላደረጉ አይደለምን? አሁንም እናንተ ሰንበትን ባለማክበራችሁ የእግዚአብሔርን ቊጣ በእስራኤል ላይ ታነሣሣላችሁ።”
19ከዚህም በኋላ በሰንበት ዋዜማ መሸትሸት ሲል የከተማይቱ ቅጽር በሮች እንዲዘጉና የሰንበት ቀን ከማለፉም በፊት እንዳይከፈቱ ትእዛዝ ሰጠሁ፤ በሰንበት ቀን ወደ ከተማይቱ ምንም ሸክም እንዳይገባ ይቈጣጠሩ ዘንድ ከአገልጋዮቼ አንዳንዶቹን በቅጽር በሮች አሰማራሁ። 20በየዐይነቱ ሸቀጣሸቀጦችን ለሺያጭ የሚያቀርቡ ነጋዴዎች ለአንድ ጊዜም ለሁለት ጊዜም የሰንበት ዋዜማ የሆነውን የዓርብን ምሽት ከከተማይቱ ቅጽር ውጪ አሳለፉ፤ 21እኔም “ማለድ ብላችሁ ለመግባት በማሰብ በዚያ ማደራችሁ ጥቅም የለውም፤ እንዲህ ማድረጋችሁን የምትቀጥሉ ከሆነ በእናንተ ላይ የኀይል እርምጃ ለመውሰድ እገደዳለሁ” ብዬ አስጠነቀቅኋቸው፤ ከዚያን ጊዜም ጀምሮ በሰንበት ቀን መምጣታቸውን አቆሙ። 22ሌዋውያኑም በሕጉ መሠረት ራሳቸውን አንጽተው የሰንበት ቀን በቅድስና የተጠበቀች መሆንዋን ለማረጋገጥ የቅጽር በሮቹን እንዲቈጣጠሩ አዘዝኳቸው።
እግዚአብሔር ሆይ! ስለዚህም ሁሉ እንድታስበኝና ስለ ጽኑ ፍቅርህም እንድትታደገኝ እለምንሃለሁ።
23በዚያው ወራት ደግሞ ከአይሁድ ሕዝብ ብዙዎቹ የአሽዶድ፥ የዐሞንና የሞአብ አገር ሴቶችን ማግባታቸውን ተገነዘብኩ፤ #ዘፀ. 34፥11-16፤ ዘዳ. 7፥1-5። 24እኩሌቶች ልጆቻቸው የአሽዶድንና የሌሎችንም አንዳንድንም ቋንቋዎች ይናገሩ ነበር፤ የአይሁድን ቋንቋ መናገር ተስኖአቸው ነበር። 25እነዚህንም ሰዎች ገሠጽኳቸው፤ ረገምኳቸውም፤ ደብድቤም ጠጒራቸውን ነጨሁ፤ ከዚህም በኋላ እነርሱም ሆኑ ልጆቻቸው ከባዕዳን ሕዝብ ጋር ጋብቻ እንዳይፈጽሙ በእግዚአብሔር ስም አስማልኳቸው። 26እንዲህም አልኳቸው፦ “የእስራኤል ንጉሥ ሰሎሞን ኃጢአት የሠራው በእንደዚህ ያለ ጋብቻ አይደለምን? ከብዙ ሕዝቦች መካከል እንደ እርሱ ያለ ንጉሥ አልነበረም። እግዚአብሔርም ወዶት በሕዝቡ በእስራኤል ላይ አነገሠው፤ እርሱ ግን በባዕዳን ሴቶች አማካይነት ኃጢአት ሠራ። በዚህ ዐይነቱ ኃጢአት ላይ ወደቀ፤ #2ሳሙ. 12፥24-25፤ 1ነገ. 11፥1-8። 27ታዲያ እኛስ የእናንተን ምሳሌነት መከተልና የባዕዳን አገሮች ሴቶችን በማግባት የእግዚአብሔርን ትእዛዝ መተላለፍ ይገባናልን?”
28ከሊቀ ካህናቱ ከኤልያሺብ ልጆች አንዱ ዮያዳዕ ነበር፤ ነገር ግን ከእርሱ ልጆች አንዱ የቤትሖሮን ከተማ ነዋሪ የሆነውን የሰንባላጥን ሴት ልጅ አግብቶ ነበር፤ ስለዚህም ዮያዳዕ ኢየሩሳሌምን ለቆ እንዲወጣ አደረግሁ። #ነህ. 4፥1።
29እግዚአብሔር አምላኬ ሆይ፥ ይህ ሕዝብ ክህነትን፥ የክህነትን ሥርዓትንና አንተ ከካህናትና ከሌዋውያን ጋር ያደረግኸውን ቃል ኪዳን እንዴት እንዳረከሰ ተመልከት!
30ከባዕድ አገር ርኲሰት ራሳቸውን እንዲያነጹ አደረግሁ፤ ካህናቱና ሌዋውያኑም እያንዳንዳቸው የሚፈጽሙትን ተግባር ዐውቀው የሚሠሩበትን ደንብ ሁሉ አዘጋጀሁ። 31መሥዋዕት የሚቃጠልበትን ማገዶ በተወሰነው ክፍለ ጊዜ ሁሉ ማቅረብ የሚቻልበትን ሁኔታ አደራጀሁ፤ ሰዎቹም ከሚሰበስቡት ሰብል ሁሉ ከእህሉም ሆነ ከፍራፍሬው በመጀመሪያ የደረሰውን እንዴት ማቅረብ እንደሚገባቸው አዘጋጀሁ።
አምላኬ ሆይ! ይህን ሁሉ አስብ፤ ይህን በማድረጌም ቸርነት አድርግልኝ።

Highlight

Share

Copy

None

Want to have your highlights saved across all your devices? Sign up or sign in

Videos for መጽሐፈ ነህምያ 13