YouVersion Logo
Search Icon

የማርቆስ ወንጌል 5

5
ኢየሱስ አንድ ርኩስ መንፈስ ያደረበትን ሰው እንደ ፈወሰ
(ማቴ. 8፥28-34ሉቃ. 8፥26-39)
1የገሊላን ባሕር በጀልባ ተሻግረው ወደ ጌርጌሴኖን አገር ደረሱ። 2ኢየሱስ ከጀልባው እንደ ወረደ አንድ በርኩስ መንፈስ የተያዘ ሰው ወዲያውኑ ከመቃብር ቦታ ወጥቶ ተገናኘው። 3ይህ ሰው በመቃብር ቦታ ይኖር ነበር፤ ማንም በሰንሰለት እንኳ አስሮ ሊያቈየው አይችልም ነበር። 4ብዙ ጊዜ በእግር ብረትና በሰንሰለት ይታሰር ነበር፤ ነገር ግን ሰንሰለቱን እየበጣጠሰና እግር ብረቱንም እየሰባበረ ይጥል ነበር፤ ስለዚህ ይዞ ሊያቆመው የሚችል ማንም አልነበረም። 5ሁልጊዜም ሌሊትና ቀን ባለማቋረጥ በየመቃብር ቦታና በየተራራው ላይ እየተዘዋወረ ይጮኽ ነበር፤ ሰውነቱን በድንጋይ እየቈራረጠ ያቈስል ነበር።
6እርሱም ኢየሱስን በሩቅ ባየው ጊዜ ወደ እርሱ ሮጠና በጒልበቱ ተንበርክኮ ሰገደለት። 7በታላቅ ድምፅም እየጮኸ፥ “አንተ የልዑል እግዚአብሔር ልጅ ኢየሱስ ሆይ! አንተ ከእኔ ጋር ምን ጉዳይ አለህ? በእግዚአብሔር ስም እለምንሃለሁ፤ እባክህ አታሠቃየኝ!” አለው። 8ይህንንም ያለበት ምክንያት፥ “አንተ ርኩስ መንፈስ ከዚህ ሰው ውጣ!” ብሎ አዞት ስለ ነበር ነው።
9ኢየሱስም “ስምህ ማን ነው?” ብሎ ጠየቀው፤ እርሱም “ብዙዎች ስለ ሆንን ስሜ ሌጌዎን ነው፤” ሲል መለሰለት። #5፥9 ሌጌዎን፦ ሌጌዎን ማለት ሠራዊት ወይም ጭፍራ ማለት ነው።
10ከዚያም አገር እንዳያባርራቸው አጥብቆ ለመነው።
11በዚያም ስፍራ በኮረብታዎች ጥግ ብዙ የዐሣማ መንጋ ተሰማርቶ ነበር፤ 12ስለዚህ “እባክህ ሄደን ወደ ዐሣማዎቹ እንድንገባ ፍቀድልን፤” ብለው ለመኑት፤ 13ኢየሱስም ፈቀደላቸው፤ ርኩሳን መናፍስቱም ከዚያ ሰው ወጥተው በዐሣማዎቹ ውስጥ ገቡ፤ በመንጋዎቹ የነበሩት ሁለት ሺህ የሚያኽሉ ዐሣማዎች ከገደሉ በመንደርደር ወርደው በባሕሩ ውስጥ ሰጠሙ።
14የዐሣማዎቹ እረኞች ሸሽተው ሄዱ፤ በከተማና በገጠር ወሬውን አወሩ፤ ሰዎቹም የሆነውን ነገር ለማየት ከየቤታቸው ወጡ፤ 15ወደ ኢየሱስም መጥተው ያ በርኩሳን መናፍስት ተይዞ የነበረው ሰው ከአእምሮው ሕመም ድኖ፥ ልብሱን ለብሶ፥ ተቀምጦም ባዩት ጊዜ ደነገጡ። 16ይህንንም ቀደም ብለው ያዩ ሰዎች ርኩስ መንፈስ ባደረበት ሰውና በዐሣማዎቹ የሆነውን ሁሉ አወሩላቸው።
17በዚያን ጊዜ የአገሩ ሰዎች ኢየሱስ ከአገራቸው ወጥቶ እንዲሄድላቸው ለመኑት።
18ኢየሱስ ወደ ጀልባው በመግባት ላይ ሳለ አጋንንት አድረውበት የነበረው ሰው፦ “እባክህ ልከተልህ!” ብሎ ለመነው።
19ኢየሱስ ግን አልፈቀደለትም፤ ነገር ግን፥ “ወደ ቤትህ ሂድና ጌታ ምን ያኽል ታላቅ ነገር እንዳደረገልህና እንዴትስ እንደማረህ ለቤተሰብህ አውራላቸው፤” አለው።
20ሰውየውም ኢየሱስ ያደረገለትን ነገር “ዐሥር ከተሞች” በሚባል አገር ማውራት ጀመረ፤ የሰሙትም ሁሉ ይደነቁ ነበር።
የኢያኢሮስ ልጅና የኢየሱስን ልብስ የነካች ሴት
(ማቴ. 9፥18-26ሉቃ. 8፥40-56)
21ኢየሱስ በጀልባ ወደ ባሕሩ ማዶ እንደገና በተመለሰ ጊዜ ብዙ ሰዎች ወደ እርሱ ተሰበሰቡ፤ በዚያ ጊዜ እርሱ በባሕሩ አጠገብ ነበር። 22እዚያም ከምኲራብ አለቆች አንዱ የነበረ፥ ኢያኢሮስ የተባለ ሰው ኢየሱስን ባየው ጊዜ በእግሩ ሥር ወድቆ 23“ትንሽዋ ልጄ በሞት አፋፍ ላይ ናት፤ እንድትድንና በሕይወት እንድትኖር እባክህ መጥተህ እጅህን ጫንባት!” ሲል አጥብቆ ለመነው።
24ኢየሱስም አብሮት ሄደ፤ ብዙ ሰዎችም ተከትለውት በዙሪያው ያጣብቡት ነበር።
25ለዐሥራ ሁለት ዓመት ደም እየመታት የምትሠቃይ አንዲት ሴት ነበረች። 26ከሐኪም ወደ ሐኪም በመሄድ ብዙ ተሠቃይታና ገንዘብዋንም ሁሉ ጨርሳ ነበር። ነገር ግን እየባሰባት ሄደ እንጂ ምንም አልተሻላትም። 27እርስዋም የኢየሱስን ዝና ሰምታ ስለ ነበር በሚጋፋው ሕዝብ መካከል ከበስተኋላው መጥታ ልብሱን ነካች። 28ይህንንም ያደረገችው፦ “ልብሱን እንኳ ብነካ እድናለሁ፤” በሚል እምነት ነበረ።
29የሚፈሰው ደምዋም ወዲያውኑ ቆመ፤ ከሕመምዋም እንደ ዳነች በሰውነትዋ ተሰማት። 30ኢየሱስም ወዲያውኑ ኀይል ከእርሱ እንደ ወጣ ዐወቀ፤ ወደ ሕዝቡም ዘወር ብሎ፦ “ልብሴን የነካ ማን ነው?” ሲል ጠየቀ።
31ደቀ መዛሙርቱም፦ “ሕዝቡ እየተጋፋ ሲከተልህ እያየህ፥ ‘ማን ነው የነካኝ?’ ትላለህን?” አሉት።
32እርሱም ይህን ያደረገው ማን እንደ ሆነ ለማየት ዘወር ብሎ ተመለከተ። 33ሴትዮዋ ግን በእርስዋ የሆነውን በማወቅዋ በፍርሃት እየተንቀጠቀጠች በፊቱ ወድቃ እውነቱን ሁሉ ነገረችው። 34እርሱም “ልጄ ሆይ፥ እምነትሽ አድኖሻል፤ በሰላም ሂጂ፤ ከሥቃይሽም ተፈወሺ፤” አላት።
35ኢየሱስ ገና ይህን በመናገር ላይ ሳለ ከምኲራብ አለቃው ቤት የመጡ ሰዎች የምኲራብ አለቃውን፦ “ልጅህ ሞታለች፤ እንግዲህ ስለምን መምህሩን ታደክመዋለህ?” አሉት።
36ኢየሱስ ግን ይህን ሰምቶ የምኲራቡን አለቃ፦ “እመን ብቻ እንጂ አትፍራ!” አለው። 37ኢየሱስ ከጴጥሮስና ከያዕቆብ፥ ከያዕቆብም ወንድም ከዮሐንስ በቀር፥ ማንም እንዲከተለው አልፈቀደም። 38ወደ ምኲራብ አለቃው ቤት በደረሱ ጊዜ ኢየሱስ ሰዎቹ ሲንጫጩና ሲያለቅሱ፥ ሲጮኹም ተመለከተ። 39ወደ ውስጥ ገብቶም፦ “ይህ ሁሉ ሁካታና ለቅሶ ስለምንድን ነው? ልጅትዋ አንቀላፍታለች እንጂ አልሞተችም፤” አላቸው።
40ሰዎቹም በማፌዝ ሳቁበት፤ ኢየሱስ ግን ሁሉንም ከቤት አስወጣ፤ የልጅትዋን አባትና እናት ከእርሱም ጋር የነበሩትን አስከትሎ፦ ልጅትዋ ወደነበረችበት ክፍል ገባ። 41የልጅትዋንም እጅ ይዞ፥ “ጣሊታ ቁሚ!” አላት፤ ትርጒሙም “አንቺ ልጅ ተነሺ እልሻለሁ፤” ማለት ነው።
42እርስዋ የዐሥራ ሁለት ዓመት ልጅ ስለ ነበረች ወዲያውኑ ተነሥታ ወዲያና ወዲህ ማለት ጀመረች፤ ይህም በሆነ ጊዜ ሰዎቹ እጅግ ተደነቁ። 43ኢየሱስ ግን ይህን ነገር ማንም እንዳያውቅ አዘዛቸውና “የምትበላውን ስጡአት!” አላቸው።

Highlight

Share

Copy

None

Want to have your highlights saved across all your devices? Sign up or sign in