YouVersion Logo
Search Icon

የማቴዎስ ወንጌል 5

5
ኢየሱስ በተራራ ላይ ሆኖ ያስተማረው ትምህርት
(ማቴ. 5፥1—7፥29)
1ኢየሱስ የሚከተለውን ብዙ ሕዝብ ባየ ጊዜ፥ ወደ ተራራ ወጥቶ ተቀመጠ፤ ደቀ መዛሙርቱም ወደ እርሱ ቀረቡ። 2እንዲህ እያለም ያስተምራቸው ጀመር፤
እውነተኛውን በረከት የሚያገኙ ሰዎች
(ሉቃ. 6፥20-23)
3“መንግሥተ ሰማይ የእነርሱ ስለ ሆነች በመንፈሳዊ ኑሮአቸው
ድኾች መሆናቸው የሚሰማቸው የተባረኩ ናቸው።
4እግዚአብሔር መጽናናትን ስለሚሰጣቸው የሚያዝኑ
የተባረኩ ናቸው። #ኢሳ. 61፥2።
5ትሑቶች ምድርን ስለሚወርሱ የተባረኩ ናቸው። #መዝ. 37፥11።
6ጽድቅን የሚራቡና የሚጠሙ ስለሚጠግቡ
የተባረኩ ናቸው። #ኢሳ. 55፥1-2።
7ምሕረትን ስለሚያገኙ ምሕረትን የሚያደርጉ የተባረኩ ናቸው።
8እግዚአብሔርን ስለሚያዩት ንጹሕ ልብ ያላቸው የተባረኩ ናቸው። #መዝ. 24፥3-4።
9በሰዎች መካከል ዕርቅና ሰላምን የሚያደርጉ፥
የእግዚአብሔር ልጆች ስለሚባሉ የተባረኩ ናቸው።
10ስለ ጽድቅ የሚሰደዱ፥ መንግሥተ ሰማይ የእነርሱ ስለ ሆነች
የተባረኩ ናቸው። #1ጴጥ. 3፥14።
11“በእኔ ምክንያት ሰዎች ሲሰድቡአችሁና ሲያሳድዱአችሁ፥ በውሸትም ስማችሁን ሲያጠፉት ደስ ይበላችሁ። #1ጴጥ. 4፥14። 12በመንግሥተ ሰማይ የምታገኙት ዋጋ ትልቅ ስለ ሆነ ደስ ይበላችሁ፤ ሐሴትም አድርጉ። ከእናንተ በፊት የነበሩትን ነቢያት እንዲሁ ስደትና መከራ አድርሰውባቸዋል።” #2ዜ.መ. 36፥16፤ ሐ.ሥ. 7፥52።
ስለ ጨውና ስለ ብርሃን ምሳሌነት
(ማር. 9፥50ሉቃ. 14፥34-35)
13ቀጥሎም ኢየሱስ እንዲህ አለ፦ “እናንተ እንደ ምድር ጨው ናችሁ፤ ነገር ግን ጨው ጣዕሙን ካጣ እንዴት ጣዕሙን መልሶ ሊያገኝ ይችላል? ወደ ውጪ ከመጣልና በሰው እግር ከመረገጥ በቀር ወደፊት ለምንም አይጠቅምም። #ሉቃ. 14፥34-35። 14እናንተ የዓለም ብርሃን ናችሁ፤ በተራራ ላይ የተሠራች ከተማ ልትሰወር አይቻላትም። #ዮሐ. 8፥12፤ 9፥5። 15ሰዎች መብራት አብርተው በቤት ውስጥ ላሉት ሁሉ እንዲያበራ በከፍተኛ ቦታ ያስቀምጡታል እንጂ ከእንቅብ በታች አያኖሩትም። #ማር. 4፥21፤ ሉቃ. 8፥16፤ 11፥33። 16እንዲሁም ሰዎች መልካም ሥራችሁን አይተው የሰማይ አባታችሁን እንዲያመሰግኑት፥ የእናንተም ብርሃን በሰው ፊት ይብራ።” #1ጴጥ. 2፥12።
ስለ ኦሪት ሕግ
17ደግሞም ኢየሱስ እንዲህ አለ፦ “የኦሪትን ሕግና የነቢያትን ትምህርት ለመሻር የመጣሁ አይምሰላችሁ፤ እኔ እንዲፈጸሙ ላደርጋቸው መጣሁ እንጂ ልሽራቸው አልመጣሁም። 18በእውነት እላችኋለሁ፤ ሰማይና ምድር እስኪያልፍ ድረስ ሕግ ሁሉ ይፈጸማል እንጂ ከሕግ አንዲት ጭረት ወይም አንዲት ነጥብ አትሻርም። #ሉቃ. 16፥17። 19ስለዚህ ከእነዚህ ትእዛዞች አነስተኛ የሆነችውን አንድዋን እንኳ የሚያፈርስና ሌሎችም ሰዎች እንዲህ እንዲያደርጉ የሚያስተምር ሰው በመንግሥተ ሰማይ አነስተኛ ይሆናል። ነገር ግን ትእዛዞችን ሁሉ የሚፈጽምና ሌሎችም ሰዎች እንዲሁ እንዲፈጽሙ የሚያስተምር ሰው በመንግሥተ ሰማይ ታላቅ ይሆናል። 20ስለዚህ የእናንተ ጽድቅ ከሕግ መምህራንና ከፈሪሳውያን ጽድቅ ካልበለጠ ከቶ ወደ መንግሥተ ሰማይ እንደማትገቡ እነግራችኋለሁ።
21“በቀድሞ ጊዜ ለነበሩ ሰዎች የተባለውን ሰምታችኋል፤ ይኸውም ‘አትግደል፤ ሰውን የገደለ ይፈረድበታል’ የሚል ነው። #ዘፀ. 20፥13፤ ዘዳ. 5፥17፤ 16፥18። 22እኔ ግን እላችኋለሁ፤ በወንድሙ ላይ የሚቈጣ ሁሉ ይፈረድበታል፤ ደግሞም ወንድሙን፥ ‘አንተ የማትረባ!’ ብሎ የሚሳደብ በሸንጎ ይፈረድበታል፤ ‘ደደብ!’ ብሎ የሚሳደብ ሁሉ በገሃነመ እሳት ይፈረድበታል። #5፥22 በወንድሙ ላይ የሚቈጣ፦ አንዳንድ የጥንት ጽሑፎች “በከንቱ” የሚል ቃል ይጨምራሉ። 23ስለዚህ አንተ መባህን በመሠዊያው ላይ ለእግዚአብሔር በምታቀርብበት ጊዜ፥ ያዘነብህ ወንድም መኖሩን ብታስታውስ፥ 24መባህን በመሠዊያው ፊት አስቀምጥና፥ ሄደህ በመጀመሪያ ከዚያ ከወንድም ጋር ታረቅ፤ ከዚያም በኋላ ተመልሰህ መባህን አቅርብ። 25ባላጋራህ ከሶህ ከእርሱ ጋር ወደ ፍርድ ቤት ስትሄድ በመንገድ ላይ ሳለህ ቶሎ ብለህ ከባላጋራህ ጋር ተስማማ። አለበለዚያ ባላጋራህ ለዳኛ፥ ዳኛውም ለአሳሪ አሳልፎ ይሰጥህና ወደ ወህኒ ቤት ትገባለህ። 26በእውነት እልሃለሁ፥ የተፈረደብህን የመጨረሻዋን ሳንቲም ከፍለህ እስክትጨርስ ድረስ ከቶ ከዚያ አትወጣም።”
ስለ ማመንዘር የተሰጠ ትምህርት
27ቀጥሎም ኢየሱስ እንዲህ አለ፦ “ ‘አታመንዝር!’ እንደ ተባለ ሰምታችኋል። #ዘፀ. 20፥14፤ ዘዳ. 5፥18። 28እኔ ግን ‘ሴትን ተመልክቶ የተመኛት ሁሉ፥ ያን ጊዜ በልቡ ከእርስዋ ጋር አመነዘረ’ እላችኋለሁ። 29የቀኝ ዐይንህ ለኃጢአት ምክንያት ቢሆንብህ፥ አውጥተህ ጣለው! ሰውነትህ በሙሉ ወደ ገሃነም ከሚጣል ይልቅ ከሰውነትህ አንዱን ክፍል ብታጣ ይሻልሃል። #ማቴ. 18፥9፤ ማር. 9፥47። 30ቀኝ እጅህ የኃጢአት ምክንያት ቢሆንብህ፥ ቈርጠህ ጣለው! ሰውነትህ በሙሉ ወደ ገሃነም ከሚጣል ይልቅ ከሰውነትህ አንዱን ክፍል ብታጣ ይሻልሃል። #ማቴ. 18፥8፤ ማር. 9፥43።
ስለ መፋታት የተሰጠ ትምህርት
(ማቴ. 19፥9ማር. 10፥11-12ሉቃ. 16፥18)
31“ሚስቱን የሚፈታ ሁሉ የፍችዋን ማስረጃ ይስጣት” ተብሏል። #ዘዳ. 24፥1-4፤ ማቴ. 19፥7፤ ማር. 10፥4። 32እኔ ግን “በዝሙት ምክንያት ካልሆነ በቀር፥ ሚስቱን የሚፈታ ሁሉ እንድታመነዝር ያደርጋታል፤ የተፈታችውንም የሚያገባ ሁሉ አመንዝራ ይሆናል” እላችኋለሁ። #ማቴ. 19፥9፤ ማር. 10፥11-12፤ ሉቃ. 16፥18፤ 1ቆሮ. 7፥10-11።
ስለ መሐላ የተሰጠ ትምህርት
33ደግሞም ለቀደሙ ሰዎች “በሐሰት አትማሉ፤ ነገር ግን መሐላችሁን ለጌታ ፈጽሙ” የተባለውን ሰምታችኋል። #ዘሌ. 19፥12፤ ዘኍ. 30፥2፤ ዘዳ. 23፥21። 34እኔ ግን “በፍጹም አትማሉ” እላችኋለሁ። ሰማይ የእግዚአብሔር ዙፋን ስለ ሆነች፥ በሰማይም ቢሆን፥ #ያዕ. 5፥12፤ ኢሳ. 66፥1፤ ማቴ. 23፥22። 35ምድርም የጌታ እግር ማሳረፊያ ስለ ሆነች በምድርም አትማሉ፤ የታላቁ ንጉሥ ከተማ ስለ ሆነች በኢየሩሳሌምም አትማሉ፤ #ኢሳ. 66፥1፤ መዝ. 48፥2። 36ከጸጒርህ አንዲቱን እንኳ ነጭ ወይም ጥቊር ማድረግ ስለማትችል በራስህም ቢሆን አትማል። 37ስለዚህ ንግግራችሁ “አዎ” ከሆነ “አዎ፥” ወይም “አይደለም” ከሆነ “አይደለም” ይሁን። ከዚህ የተረፈ ቃል ግን ከሰይጣን ነው። #ዘሌ. 19፥12፤ ዘኍ. 30፥2፤ ዘዳ. 23፥21።
ቂም በቀል መያዝ የማይገባ ስለ መሆኑ
(ሉቃ. 6፥29-30)
38“ ‘ዐይን ስለ ዐይን፥ ጥርስ ስለ ጥርስ’ እንደ ተባለ ሰምታችኋል። #ዘፀ. 21፥24፤ ዘሌ. 24፥20፤ ዘዳ. 19፥21። 39እኔ ግን እንዲህ እላችኋለሁ፤ ክፉ የሚያደርግባችሁን ሰው አትበቀሉት። ነገር ግን ቀኝ ጒንጭህን ለሚመታህ፥ ግራ ጒንጭህን አዙርለት። 40አንድ ሰው ሸሚዝህን ለመውሰድ ፈልጎ ቢከስህ፥ ኮትህንም እንዲወስድ ተውለት። 41አንድ ሰው ‘ከእኔ ጋር ጥቂት መንገድ ሂድ’ ብሎ ቢያስገድድህ፥ አንተ ደግሞ እጥፍ መንገድ ሂድለት። 42ለሚለምንህ ስጥ፤ ከአንተ መበደር ለሚፈልግ እምቢ አትበለው።” #ዘዳ. 15፥8፤ ምሳ. 24፥29።
ጠላትን ስለ መውደድ
(ሉቃ. 6፥27-36)
43ቀጥሎም ኢየሱስ እንዲህ አለ፦ “ ‘ባልንጀራህን ውደድ፤ ጠላትህን ጥላ’ እንደ ተባለ ሰምታችኋል። #ዘሌ. 19፥18። 44እኔ ግን ጠላቶቻችሁን ውደዱ፤ የሚረግሙአችሁን መርቁ፤ ለሚጠሉአችሁ በጎ አድርጉ፤ ክፉ ለሚያደርጉባችሁና ለሚያሳድዱአችሁ ጸልዩ” እላችኋለሁ። #ምሳ. 25፥21-22። 45ይህን ብታደርጉ፥ በሰማይ ላለው አባታችሁ ልጆች ትሆናላችሁ። እርሱ ለክፉዎችና ለደጎች ፀሐዩን ያወጣል፤ እንዲሁም ለጻድቃንና ለግፈኞች ዝናቡን ያዘንባል። 46የሚወዱአችሁን ሰዎች ብቻ ብትወዱ ምን ዋጋ አላችሁ? ኃጢአተኞችስ ይህንኑ ያደርጉ የለምን? 47ለወንድሞቻችሁ ብቻ ሰላምታ የምትሰጡ ከሆነ ምን ብልጫ ያለው ነገር ታደርጋላችሁ? አሕዛብስ ይህንኑ ያደርጉ የለምን? 48ስለዚህ የሰማይ አባታችሁ ፍጹም እንደ ሆነ እናንተም ፍጹሞች ሁኑ። #ዘሌ. 19፥2፤18፤ ዘዳ. 18፥13።

Highlight

Share

Copy

None

Want to have your highlights saved across all your devices? Sign up or sign in