የማቴዎስ ወንጌል 4
4
የኢየሱስ መፈተን
(ማር. 1፥12-13፤ ሉቃ. 4፥1-13)
1ከዚህ በኋላ፥ ኢየሱስ በዲያብሎስ ይፈተን ዘንድ የእግዚአብሔር መንፈስ ወደ በረሓ ወሰደው። #ዕብ. 2፥18፤ 4፥15። 2እዚያም አርባ ቀንና አርባ ሌሊት ከጾመ በኋላ ተራበ። #ዘፀ. 34፥28፤ 1ነገ. 19፥8። 3ፈታኙ ወደ ኢየሱስ መጥቶ፥ “አንተ የእግዚአብሔር ልጅ ከሆንክ፥ እስቲ እነዚህ ድንጋዮች እንጀራ እንዲሆኑ እዘዝ” አለው።
4ኢየሱስ ግን “ ‘ሰው የሚኖረው ከእግዚአብሔር አፍ በሚወጣ ቃል ሁሉ እንጂ፥ በእንጀራ ብቻ አይደለም’ ተብሎ ተጽፎአል” አለው። #ዘዳ. 8፥3።
5ከዚህ በኋላ፥ ዲያብሎስ ኢየሱስን ወደ ቅድስት ከተማ ወደ ኢየሩሳሌም ወስዶ በቤተ መቅደስ ጣራ ጫፍ ላይ አቆመው፤ #ነህ. 11፥1፤ ዳን. 9፥24። 6“ ‘እግሮችህ በድንጋይ እንዳይሰናከሉ፥
በእጆቻቸው ይደግፉህ ዘንድ መላእክቱን ያዝልሃል’
ተብሎ ተጽፎአልና አንተ የእግዚአብሔር ልጅ ከሆንክ፥ ከዚህ ወደታች ራስህን ወርውር” አለው። #መዝ. 91፥11-12።
7ኢየሱስም መልሶ “ ‘ጌታ አምላክህን አትፈታተነው’ ተብሎ ደግሞ ተጽፎአል” አለው። #ዘዳ. 6፥16።
8እንደገናም ዲያብሎስ ኢየሱስን በጣም ከፍ ወዳለ ተራራ ላይ አውጥቶ፥ የዓለምን መንግሥታት ሁሉ ከነክብራቸው አሳየውና፤ 9“ተደፍተህ ብትሰግድልኝ ይህን ሁሉ እሰጥሃለሁ” አለው።
10የዚያን ጊዜ ኢየሱስ “ ‘ለጌታህ ለአምላክህ ስገድ፤ እርሱንም ብቻ አምልክ!’ ተብሎ ተጽፎአልና ወግድ አንተ ሰይጣን!” አለው። #ዘዳ. 6፥13።
11ከዚህ በኋላ ዲያብሎስ ኢየሱስን ተወው፤ መላእክትም መጥተው አገለገሉት።
ኢየሱስ የማስተማር ሥራውን በገሊላ እንደ ጀመረ
(ማር. 1፥14-15፤ ሉቃ. 4፥14-15)
12ኢየሱስ የዮሐንስን መታሰር በሰማ ጊዜ ወደ ገሊላ ምድር ሄደ። #ማቴ. 14፥3፤ ማር. 6፥17፤ ሉቃ. 3፥19-20። 13የናዝሬትንም ከተማ ትቶ፥ በዛብሎንና በንፍታሌም አውራጃ በገሊላ ባሕር አጠገብ ወደምትገኘው ወደ ቅፍርናሆም ከተማ መጥቶ ኖረ። #ዮሐ. 2፥12።
14ይህም የሆነው፥ ነቢዩ ኢሳይያስ እንዲህ ሲል የተናገረው የትንቢት ቃል እንዲፈጸም ነው፤
15“ወደ ባሕሩ በሚወስደው መንገድና ከዮርዳኖስ ወንዝ ማዶ
የሚገኙት የዛብሎን ምድር፥ የንፍታሌም ምድር፥
የአሕዛብም ገሊላ፥
16በጨለማ የሚኖር ሕዝብ ታላቅ ብርሃን አየ፤
የሞት ጥላ በጣለበት ምድር ለሚኖሩትም ብርሃን ወጣላቸው።” #ኢሳ. 9፥1-2።
17ከዚያን ጊዜ ጀምሮ ኢየሱስ፥ “የእግዚአብሔር መንግሥት ቀርባለችና ንስሓ ግቡ!” እያለ መስበክ ጀመረ። #ማቴ. 3፥2።
ኢየሱስ አራት ዓሣ አጥማጆችን እንደ ጠራ
(ማር. 1፥16-20፤ ሉቃ. 5፥1-11)
18ኢየሱስ በገሊላ ባሕር አጠገብ ሲያልፍ፥ ዓሣ አጥማጆች የነበሩትን ሁለት ወንድማማች እነርሱም ጴጥሮስ የተባለውን ስምዖንንና ወንድሙን እንድርያስን፥ መረባቸውን ወደ ባሕር ሲጥሉ አየ። 19ኢየሱስም “ኑ ተከተሉኝ፤ ዓሣን እንደምታጠምዱ ሁሉ ሰዎችን እንድትሰበስቡልኝ አደርጋችኋለሁ” አላቸው። 20እነርሱም ወዲያውኑ መረባቸውን ትተው ተከተሉት።
21ከዚያም እልፍ ብሎ፥ የዘብዴዎስ ልጆች የሆኑትን ሌሎች ሁለት ወንድማማች ያዕቆብንና ዮሐንስን አየ። እነርሱም ከአባታቸው ከዘብዴዎስ ጋር በጀልባ ላይ ሆነው መረባቸውን ሲጠግኑ ሳለ ጠራቸው። 22እነርሱም ወዲያውኑ ጀልባዋንና አባታቸውን ትተው ተከተሉት።
ኢየሱስ ብዙ ሰዎችን እንዳስተማረና እንደ ፈወሰ
(ሉቃ. 6፥17-19)
23ኢየሱስም በምኲራቦቻቸው እያስተማረና የእግዚአብሔርን መንግሥት የምሥራች ቃል እየሰበከ፥ በልዩ ልዩ በሽታና ደዌ የተያዙትንም ሰዎች እየፈወሰ በገሊላ ምድር ሁሉ ይዘዋወር ነበር። #ማቴ. 9፥35፤ ማር. 1፥39። #4፥23 ምኲራቦች፦ በመሠረቱ መሰብሰቢያ ቦታዎች ሲሆኑ፥ የአይሁድ ጸሎት ቤትም ምኲራብ ይባላል። 24ዝናው በሶርያ አገር ሁሉ ስለ ተሰማ፥ ሰዎች በልዩ ልዩ በሽታና ደዌ የሚሠቃዩትን፥ ርኩሳን መናፍስት ያደሩባቸውን፥ የሚጥል በሽታ ያለባቸውንና ሽባዎችንም ሁሉ ወደ እርሱ አመጡ፤ እርሱም ፈወሳቸው። 25ከገሊላ ምድርና ከዐሥሩ ከተሞች ከኢየሩሳሌምና ከይሁዳ፥ ከዮርዳኖስም ወንዝ ማዶ የመጡ ብዙ ሰዎች ኢየሱስን ተከተሉት። #4፥25 ዐሥሩ ከተሞች፦ ግሪክኛ ተናጋሪዎችና አይሁድ ያልሆኑ ሕዝቦች በአንድነት የሚኖሩ ቦታዎች ዐሥር ከተሞች ይባላሉ። እነዚህም ከተሞች አብዛኞቻቸው የሚገኙት በገሊላ ባሕር በስተምሥራቅና በስተሰሜን ምሥራቅ ነው።
Currently Selected:
የማቴዎስ ወንጌል 4: አማ05
Highlight
Share
Copy
Want to have your highlights saved across all your devices? Sign up or sign in
© The Bible Society of Ethiopia, 2005
© የኢትዮጵያ መጽሐፍ ቅዱስ ማኅበር፥ 1997