YouVersion Logo
Search Icon

የማቴዎስ ወንጌል 2

2
ከምሥራቅ የመጡ የከዋክብት ተመራማሪዎች
1በንጉሥ ሄሮድስ ዘመን፥ በይሁዳ ምድር በምትገኝ በቤተልሔም ከተማ ኢየሱስ በተወለደ ጊዜ፥ የከዋክብት ተመራማሪዎች ከምሥራቅ ወደ ኢየሩሳሌም መጡ። 2እንዲህም እያሉ ጠየቁ፦ “የተወለደው የአይሁድ ንጉሥ የት ነው? ኮከቡን በምሥራቅ አይተን ለእርሱ ልንሰግድለት መጥተናል።” #ኤር. 23፥5፤ ዘካ. 9፥9፤ ዘኍ. 24፥17።
3ንጉሡ ሄሮድስ ይህን ነገር በሰማ ጊዜ ደነገጠ፤ የኢየሩሳሌምም ሰዎች ሁሉ ከእርሱ ጋር ደነገጡ። 4የካህናት አለቆችን ሁሉና የሕዝቡን የሕግ መምህራን ሰብስቦ መሲሕ የሚወለደው ወዴት እንደ ሆነ ጠየቃቸው።
5እነርሱም እንዲህ ሲሉ መለሱለት፦ “በነቢይ እንዲህ የሚል ትንቢት ስለ ተጻፈ፥ መሲሕ የሚወለደው በይሁዳ ምድር፥ በቤተልሔም ከተማ ነው፤
6‘በይሁዳ ክፍለ ሀገር የምትገኚ አንቺ ቤተልሔም ሆይ!
ሕዝቤን እስራኤልን የሚጠብቅ መሪ ከአንቺ ስለሚወጣ፥
ከይሁዳ ታላላቅ ከተሞች በምንም አታንሺም።’ ” #ሚክ. 5፥2።
7ከዚህ በኋላ ሄሮድስ እነዚያን የከዋክብት ተመራማሪዎች በስውር አስጠርቶ፥ ኮከቡ የታየበትን ትክክለኛ ጊዜ ጠይቆ ተረዳ፤ 8እንዲህ ብሎም ወደ ቤተልሔም ላካቸው፦ “ሂዱና፤ ስለ ሕፃኑ በጥንቃቄ መርምሩ፤ ባገኛችሁትም ጊዜ፥ እኔም ሄጄ እንድሰግድለት መጥታችሁ ንገሩኝ።”
9እነርሱም የንጉሡን ቃል ከሰሙ በኋላ፥ ወጥተው ሄዱ፤ እነሆ! በምሥራቅ ያዩት ኮከብ ሕፃኑ በነበረበት ቦታ ላይ እስኪቆም ድረስ፥ እፊት እፊታቸው እየሄደ ይመራቸው ነበር። 10ኮከቡንም ባዩ ጊዜ እጅግ በጣም ደስ አላቸው፤ 11ወደ ቤትም ገብተው ሕፃኑን ከእናቱ ከማርያም ጋር ሆኖ አዩት፤ ተደፍተውም ሰገዱለት፤ ሣጥኖቻቸውንም ከፍተው የወርቅ፥ የዕጣንና የከርቤ ስጦታ አቀረቡለት።
12ወደ ሄሮድስም እንዳይመለሱ እግዚአብሔር በሕልም ስላስጠነቀቃቸው፥ ተመራማሪዎቹ በሌላ መንገድ ወደ አገራቸው ተመልሰው ሄዱ።
ሕፃኑን ይዘው ወደ ግብጽ መሸሻቸው
13የከዋክብት ተመራማሪዎቹ ከሄዱ በኋላ፥ የጌታ መልአክ ለዮሴፍ በሕልም ተገልጦ፥ “ሄሮድስ ሕፃኑን ለመግደል ስለሚፈልገው፥ ተነሥና ሕፃኑን ከእናቱ ጋር ይዘህ ወደ ግብጽ ሽሽ፤ እስክነግርህም ድረስ በዚያ ቈይ” አለው።
14ስለዚህ ዮሴፍም በሌሊት ተነሣና፥ ሕፃኑን ከእናቱ ጋር ይዞ፥ ወደ ግብጽ ሄደ። 15እዚያም ሄሮድስ እስኪሞት ድረስ ቈየ፤ ይህም የሆነው ጌታ በነቢይ “ልጄን ከግብጽ ጠራሁት” ያለው ቃል እንዲፈጸም ነው። #ሆሴዕ 11፥1።
ሄሮድስ ሕፃናትን እንዳስገደለ
16ከዚያ በኋላ ሄሮድስ፥ የከዋክብት ተመራማሪዎቹ እንዳታለሉት በተገነዘበ ጊዜ፥ በጣም ተቈጣ፤ ወደ ቤተልሔምና በዙሪያዋም ወዳሉት መንደሮች ሁሉ ወታደሮቹን ልኮ፥ ከከዋክብት ተመራማሪዎቹ በተረዳው ዘመን መሠረት፥ ዕድሜአቸው ሁለት ዓመት የሆናቸውንና ከዚያ በታች የሆኑትን በቤተልሔምና በአካባቢው የነበሩትን ወንዶች ሕፃናትን አስገደለ። 17በዚያን ጊዜ፥ በነቢዩ ኤርምያስ እንዲህ ሲል የተነገረው ትንቢት ተፈጸመ፦
18“ራሔል ለልጆችዋ ስታለቅስ፥
የዋይታና፥ የመራራ ለቅሶ ድምፅ በራማ ተሰማ፤
ልጆችዋም በሕይወት ስለሌሉ ለመጽናናት እምቢ አለች።” #ኤር. 31፥15።
ከግብጽ ወደ ናዝሬት መመለስ
19ሄሮድስ ከሞተ በኋላ የጌታ መልአክ በግብጽ ለዮሴፍ በሕልም ተገልጦለት፥ 20“ሕፃኑን ለመግደል የሚፈልጉት ሰዎች ስለ ሞቱ፥ ተነሥና ሕፃኑን ከእናቱ ጋር ይዘህ፥ ወደ እስራኤል አገር ሂድ” አለው። 21ዮሴፍም ተነሣና ሕፃኑን ከእናቱ ጋር ይዞ፥ ወደ እስራኤል አገር ተመለሰ።
22ነገር ግን አርኬላዎስ በአባቱ በሄሮድስ ምትክ በይሁዳ ምድር ላይ መንገሡን በሰማ ጊዜ፥ ዮሴፍ ወደዚያ መሄድ ፈራ። ሆኖም በሕልም መመሪያ ስለ ተሰጠው፥ ወደ ገሊላ ምድር ሄደ። 23“ናዝራዊ ይባላል” ተብሎ በነቢያት የተነገረው ይፈጸም ዘንድ፥ ናዝሬት ወደምትባል ከተማ መጥቶ ኖረ። #ኢሳ. 11፥1፤ ማር. 1፥24፤ ሉቃ. 2፥39፤ ዮሐ. 1፥45።

Highlight

Share

Copy

None

Want to have your highlights saved across all your devices? Sign up or sign in