YouVersion Logo
Search Icon

ትንቢተ ሚልክያስ 3

3
1የሠራዊት አምላክ እንዲህ ይላል፦ “እነሆ፥ በፊቴ መንገድን ያዘጋጅ ዘንድ መልእክተኛዬን እልካለሁ፤ የምትፈልጉት ጌታም በድንገት ወደ ቤተ መቅደሱ ይመጣል፤ በእርሱ የምትደሰቱበት የቃል ኪዳን መልእክተኛም በእርግጥ ይመጣል።” #ማቴ. 11፥10፤ ማር. 1፥2፤ ሉቃ. 1፥76፤ 7፥27።
2ነገር ግን እርሱ እንደ ብረት ማቅለጫ እሳትና እንደ ልብስ ማጠቢያ ሳሙና ስለ ሆነ በእርሱ የመምጫ ቀን ጸንቶ መቆም የሚችልና እርሱስ ሲገለጥ በፊቱ መቆም የሚችል ማነው? #ኢዩ. 2፥11፤ ራዕ. 6፥17። 3እርሱ እንደ ብረት አቅላጭና እንደ ብር አንጥረኛ ፍርድን ለማጣራት ይቀመጣል፤ የሌዊንም ልጆች የጽድቅ መሥዋዕት ለማቅረብ እስከሚችሉ ድረስ እንደ ወርቅና እንደ ብር ያጠራቸዋል።
4የይሁዳና የኢየሩሳሌም ሕዝብ የሚያቀርቡት መሥዋዕት እንደ ቀድሞ ዘመንና እንዳለፉት ዓመቶች እግዚአብሔርን የሚያስደስት ይሆናል። 5የሠራዊት አምላክ እንዲህ ይላል፦ “ለፍርድ ወደ እናንተ እቀርባለሁ፤ በአስማተኞች፥ በዘማውያን፥ በሐሰት መስካሪዎች፥ የቀን ሠራተኞችን ደመወዝ አታለው በሚያስቀሩ አሠሪዎች፥ ባሎቻቸው የሞቱባቸውን ሴቶች፥ እናትና አባት የሌላቸው ልጆችንና ስደተኞችን በሚጨቊኑና እኔን በማይፈሩ ሰዎች ላይ ፈጣን ፍርዴን አስተላልፋለሁ።
ዐሥራት የመክፈል ግዴታ
6“እኔ እግዚአብሔር አልለወጥም፤ ስለዚህ እናንተ የእስራኤል ልጆች ሆይ! ገና ፈጽማችሁ አልጠፋችሁም። 7ከቀድሞ አባቶቻችሁ ዘመን ጀምሮ ከሕጌ ርቃችኋል፤ አልጠበቃችሁትምም። ‘ወደ እኔ ተመለሱ እኔም ወደ እናንተ እመለሳለሁ’፥ እናንተ ግን ‘ወደ አንተ የምንመለሰው በምን ዐይነት ነው?’ ትላላችሁ። 8ሰው የእግዚአብሔርን ሀብት ይዘርፋልን? ሆኖም እናንተ እኔን ዘርፋችኋል፥ እናንተ ግን እንዴት ከአንተ እንዘርፋለን ብላችሁ ትጠይቃላችሁ፤ ከእኔ የዘረፋችሁት ዐሥራትንና መባን ባለመክፈላችሁ ነው። 9እናንተ፥ ሕዝቡም ሁሉ ከእኔ ስለምትዘርፉ የተረገማችሁ ሆናችኋል። 10በቤተ መቅደሴ ሲሳይ ይበዛ ዘንድ ዐሥራቴን በሙሉ ወደ ጐተራ አግቡ፤ እናንተ ይህን ብታደርጉ እኔ ደግሞ የሰማይን መስኮቶች ከፍቼ መልካም የሆነውን በረከት ሁሉ አብዝቼ ባልሰጣችሁ በዚህ ልትፈትኑኝ ትችላላችሁ። #ዘሌ. 27፥30፤ ዘኍ. 18፥21-24፤ ዘዳ. 12፥6፤ 14፥22-29፤ ነህ. 13፥12። 11እህላችሁን ተባይ እንዳያጠፋው እከለክላለሁ፤ የወይናችሁ ተክል ፍሬ አልባ አይሆንም፤ 12ከዚህ በኋላ ሕዝቦች ሁሉ እናንተን የተባረከ ሕዝብ ብለው ይጠሯችኋል፤” ይህን የተናገርኩ እኔ የሠራዊት አምላክ ነኝ።
እግዚአብሔር ምሕረት እንደሚያደርግ የሰጠው ተስፋ
13እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፥ “በእኔ ላይ የድፍረት ቃል ትናገራላችሁ፤ እንደገና ደግሞ ‘እኛ በአንተ ላይ ምን ክፉ ነገር ተናገርን?’ ብላችሁ ትጠይቃላችሁ፤ 14እናንተ ‘እግዚአብሔርን ማገልገል ከንቱ ነው፤ ትእዛዞቹን መጠበቅና እንደ ሐዘንተኞች በሠራዊት አምላክ ፊት መመላለስ ምን ይጠቅመናል? 15እንደምናየው ከሆነ እነሆ፥ ክፉ አድራጊዎች ዕድለኞች ናቸው፤ በእርግጥም እነርሱ በብልጽግና ይኖራሉ፤ እግዚአብሔርን እንኳ እየተፈታተኑት ምንም ችግር አይደርስባቸውም እያላችሁ ትናገራላችሁ።’ ”
16ከዚያ በኋላ እግዚአብሔርን የሚያከብሩ ሰዎች እርስ በርሳቸው ተነጋገሩ፤ እግዚአብሔርም በጥሞና አዳመጣቸው፤ እግዚአብሔርን የሚፈሩና ስሙንም የሚያከብሩ ሰዎች ለተግባራቸው መታሰቢያ በመጽሐፍ ተጻፈ። 17የሠራዊት አምላክ እንዲህ ይላል፦ “እነርሱ የእኔ ይሆናሉ፤ እኔ በምሠራበት ቀን እነርሱ የእኔ የግሌ ይሆናሉ፤ ወላጆች ለሚያገለግሉአቸው ልጆች ምሕረት እንደሚያደርጉላቸው እኔም ለእነርሱ ምሕረት አደርግላቸዋለሁ። 18በዚያን ጊዜ በጻድቅና በኃጢአተኛ ለእግዚአብሔር በሚታዘዝና በማይታዘዝ ሰው መካከል ያለውን ልዩነት እንደገና ታያላችሁ።”

Highlight

Share

Copy

None

Want to have your highlights saved across all your devices? Sign up or sign in

Videos for ትንቢተ ሚልክያስ 3