YouVersion Logo
Search Icon

ትንቢተ ሚልክያስ 2

2
1እግዚአብሔር ለካህናቱ እንዲህ ይላል፦ “ካህናት ሆይ! አሁንም ይህ ትእዛዝ ለእናንተ ነው። 2ባታዳምጡ፥ ለስሜም ክብር ለመስጠት ቃሌን በልባችሁ ባታኖሩት መርገም እልክባችኋለሁ፤ በረከታችሁንም ወደ ርግማን እለውጣለሁ፤ እኔን ማክበር በልባችሁ ውስጥ ስለሌለ በእርግጥ ይህን ሁሉ አደርግባችኋለሁ። 3በእናንተ ምክንያት ልጆቻችሁን እቀጣለሁ፤ ለመሥዋዕት ያመጣችኋቸውን እንስሶች እበት በፊታችሁ ላይ እበትናለሁ፤ ከፊቴም አስወግዳችኋለሁ። 4ከሌዊና ከተወላጆቹ ጋር ያለኝ ቃል ኪዳን ጸንቶ ይኖር ዘንድ ይህን ትእዛዝ እኔ የላክሁላችሁ መሆኑን ታውቃላችሁ። #ዘኍ. 3፥11-13።
5“የሰጠኋቸው ቃል ኪዳን የሕይወትና የሰላም ቃል ኪዳን ነው፤ እንዲሁም እኔን የማክበር ግዴታ አለባቸው፤ እነርሱም እኔን እየፈሩ ስሜን አክብረው ኖረዋል። #ዘኍ. 25፥12። 6እነርሱ እውነትን ያስተምሩ ነበር፤ በአንደበታቸውም ስሕተት አልተገኘም፤ ከእኔ ጋር በሰላምና በቅንነት ተመላልሰዋል፤ በትምህርታቸው ብዙዎችን ከበደል መልሰዋል። 7ካህን የሠራዊት አምላክ መልእክተኛ ስለ ሆነና ሕዝብም ከእርሱ ዕውቀትን ስለሚፈልግ የካህን አንደበት ዕውቀትን ጠብቆ ማኖር አለበት። 8እናንተ ግን ከመንገድ ወጥታችሁ በትምህርታችሁ ብዙዎችን አሰናክላችኋል፤ ከሌዊ ጋር የገባሁትን ቃል ኪዳን አፍርሳችኋል። 9የእኔን ሥርዓት ባለመከታተል በሕግ ጉዳይ አድልዎ ስለምትፈጽሙ እኔ ደግሞ በሕዝብ ሁሉ ፊት እንድትናቁና እንድትዋረዱ አደርጋችኋለሁ።”
የሕዝቡ በእግዚአብሔር አለመታመን
10ለሁላችንም አንድ አባት ያለን አይደለምን፤ የፈጠረንስ አንድ አምላክ አይደለምን? ታዲያ ለምን የቀድሞ አባቶቻችንን ቃል ኪዳን በማፍረስ እርስ በርሳችን እምነተቢሶች እንሆናለን? 11የይሁዳ ሕዝብ እምነተቢስ ሆኖአል፤ በእስራኤልና በኢየሩሳሌም አጸያፊ የርኲሰት ሥራ ፈጽመዋል፤ ይህም የሆነው ጣዖት አምላኪዎች የሆኑ የባዕድ ሴቶችን በማግባት ይሁዳ እግዚአብሔር የሚወደውን ቤተ መቅደስ ስላረከሰ ነው። 12ይህን የሚያደርገውን ሰው ለሠራዊት አምላክ መሥዋዕት ቢያቀርብም እንኳ እግዚአብሔር ከእስራኤል ሕዝብ መካከል ያጥፋው።
13እንዲህም ታደርጋላችሁ፦ እግዚአብሔር መሥዋዕታችሁን ስለማይቀበለው የእግዚአብሔርን መሠዊያ በእንባ፥ በለቅሶና በሐዘን ትሸፍናላችሁ። 14“ስለምን መሥዋዕታችንን አይቀበልም?” ብላችሁ ትጠይቃላችሁ፤ እግዚአብሔር መሥዋዕታችሁን የማይቀበለው የቃል ኪዳን ጓደኞቻችሁ ለሆኑት ለወጣትነት ሚስቶቻችሁ ታማኝነታችሁን ስላፈረሳችሁ ነው፤ በእናንተም መካከል እግዚአብሔር ምስክር ነበር። 15ታዲያ እግዚአብሔር እናንተና ሚስቶቻችሁ አንድ አካልና አንድ መንፈስ እንዲኖራችሁ አድርጎ አልነበረምን? በዚህስ የእርሱ ዓላማ ምን ነበር? ዋና ዓላማው የእግዚአብሔር ሕዝቦች የሆኑ ልጆችን እንድትወልዱ በመፈለግ ነበር፤ ስለዚህ ከእናንተ እያንዳንዱ ለሚስቱ የገባውን ቃል ኪዳን አያፍርስ። 16“እኔ የባልና የሚስትን መፋታት እጠላለሁ፤ ልብስን በፍትሕ አልባነት መሸፈንንም እጠላለሁ ሰውነቱን በልብስ እንደሚሸፍን በግፍ ሥራ የሚሸፍንን ሰው እጠላለሁ፤ ስለዚህ እምነተቢስ ከመሆን ተጠንቀቁ።” ይላል የእስራኤል አምላክ እግዚአብሔር።
የፍርድ ቀን መቅረቡ
17በቃላችሁ እግዚአብሔርን አሰልችታችሁታል፤ “እርሱን ያሰለቸነው በምንድን ነው?” ትላላችሁ፤ እርሱን ያሰለቻችሁት፦ “ክፉ አድራጊ ሁሉ በእግዚአብሔር ዘንድ መልካም ነው፤ እግዚአብሔርንም ያስደስተዋል” በማለት ወይም “የፍትሕ አምላክ የት አለ?” ብላችሁ በመጠየቅ ነው።

Highlight

Share

Copy

None

Want to have your highlights saved across all your devices? Sign up or sign in

Videos for ትንቢተ ሚልክያስ 2