YouVersion Logo
Search Icon

የሉቃስ ወንጌል 21

21
የመበለቲቱ ስጦታ
(ማር. 12፥41-44)
1ኢየሱስ ቀና ብሎ ሲመለከት ሀብታሞች መባቸውን በምጽዋት መቀበያ ሣጥን ውስጥ ሲጨምሩ አየ። 2እንዲሁም አንዲት ድኻ መበለት፥ ሁለት ሳንቲም የሚያኽል የናስ ገንዘብ በሣጥኑ ውስጥ ስትጨምር አየ። 3እንዲህም አለ፦ “በእውነት እላችኋለሁ፤ ይህች ድኻ መበለት፥ ከሁሉም አብልጣ ሰጥታለች። 4እነርሱ የሰጡት ከሀብታቸው የተረፋቸውን ነው፤ እርስዋ ግን ድኻ ሆና ሳለች ምንም ሳታስቀር ያላትን ሁሉ ሰጠች።”
ስለ ቤተ መቅደስ መፍረስ የኢየሱስ ትንቢት
(ማቴ. 24፥1-2ማር. 13፥1-2)
5አንዳንድ ሰዎች፥ “ይህ ቤተ መቅደስ እንዴት ውብ ነው? በከበሩ ድንጋዮችና ለእግዚአብሔር በቀረቡ ስጦታዎች አጊጦአል” እያሉ ይነጋገሩ ነበር። 6ኢየሱስ ግን “ይህ የምታዩት ሁሉ ድንጋይ በድንጋይ ላይ ተነባብሮ የማይቀርበት ጊዜ ይመጣል፤ እነዚህ ድንጋዮች ሁሉ አንድ ቀን ይፈራርሳሉ።”
7እነርሱም “መምህር ሆይ! ይህ የሚሆነው መቼ ነው? ይህስ የሚሆንበት ጊዜ መቃረቡን የምናውቅበት ምልክት ምንድን ነው?” ሲሉ ጠየቁት።
ከጌታ መምጣት በፊት የሚደርስ ስደትና መከራ
(ማቴ. 24፥3-14ማር. 13፥3-13)
8ኢየሱስ እንዲህ ሲል መለሰላቸው፦ “እንዳትሳሳቱ ተጠንቀቁ! ብዙዎች ‘እኔ ክርስቶስ ነኝ! እነሆ፥ ጊዜው ቀርቦአል!’ እያሉ በስሜ ይመጣሉ፤ እነርሱን አትከተሉአቸው። 9ስለ ጦርነትና ስለ ሁከት በምትሰሙበት ጊዜም አትደንግጡ፤ አስቀድሞ ይህ ይሆን ዘንድ ይገባል፤ ይሁን እንጂ ፍጻሜው ወዲያውኑ አይሆንም።”
10ቀጥሎም ኢየሱስ እንዲህ አለ፦ “ሕዝብ በሕዝብ ላይ፥ መንግሥት በመንግሥት ላይ ይነሣል። 11በየቦታውም ብርቱ የምድር መናወጥ፥ ራብና ወረርሽኝ ይሆናል። የሚያስፈሩ ነገሮችና ታላላቅ ምልክቶች በሰማይ ላይ ይታያሉ። 12ነገር ግን ይህ ሁሉ ከመሆኑ በፊት ሰዎች እናንተን ይይዙአችኋል፤ ያሳድዱአችኋል፤ ወደ ምኲራብና ወደ ወህኒ ቤትም አሳልፈው ይሰጡአችኋል፤ ስለ ስሜም ወደ ነገሥታትና ወደ ገዥዎች ይወስዱአችኋል። 13ይህም ስለ ስሜ ለመመስከር መልካም አጋጣሚ ይሆንላችኋል። 14ስለዚህ በሚቀርብባችሁ ክስ ስለምትሰጡት መልስ መጨነቅ እንደማይገባችሁ አስቀድማችሁ ልብ አድርጉ። #ሉቃ. 12፥11-12። 15ከጠላቶቻችሁ ማንም ሊቋቋመው ወይም ሊቃወመው የማይችለውን አንደበትና ጥበብ እኔ እሰጣችኋለሁ። 16ወላጆቻችሁና ወንድሞቻችሁ፥ ዘመዶቻችሁና ወዳጆቻችሁም ሳይቀሩ አሳልፈው ይሰጡአችኋል፤ ከእናንተ አንዳንዶቹ ይገደላሉ። 17ስለ ስሜም በሰው ሁሉ ዘንድ የተጠላችሁ ትሆናላችሁ። 18ነገር ግን ከራሳችሁ ጠጒር አንዲት እንኳ አትጠፋም። 19በትዕግሥታችሁ ነፍሳችሁን ታድናላችሁ” አለ።
ኢየሱስ ስለ ኢየሩሳሌም መጥፋት አስቀድሞ እንደ ተናገረ
(ማቴ. 24፥15-21ማር. 13፥14-19)
20ቀጥሎም ኢየሱስ እንዲህ አለ፦ “ኢየሩሳሌም በጠላት ወታደሮች ተከባ ባያችሁ ጊዜ ለመጥፋት እንደ ተቃረበች ዕወቁ፤ 21በዚያን ጊዜ በይሁዳ ምድር ያሉ ወደ ተራራዎች ይሽሹ፤ በከተማይቱ ውስጥ ያሉ ከዚያ ይውጡ፤ ከከተማ ውጪ ያሉትም ወደ ከተማይቱ አይግቡ። 22ስለዚህ ጥፋት የተጻፈው ትንቢት እንዲፈጸም ይህ የበቀልና የቅጣት ጊዜ ነው። #ሆሴዕ 9፥7። 23በዚያን ጊዜ ለነፍሰጡሮችና ለሚያጠቡ እመጫቶች ወዮላቸው! በምድር ላይ ታላቅ መከራ ይሆናል፤ በዚህም ሕዝብ ላይ የእግዚአብሔር ቊጣ ይመጣል። 24ከእነርሱም ብዙዎች በሰይፍ ይገደላሉ፤ ሌሎችም ተማርከው ወደየአገሩ ይወሰዳሉ። የአሕዛብ ዘመን እስኪፈጸም ድረስ ኢየሩሳሌም በአሕዛብ የተረገጠች ትሆናለች።”
የሰው ልጅ ዳግመኛ መምጣት
(ማቴ. 24፥29-31ማር. 13፥24-27)
25ቀጥሎም ኢየሱስ እንዲህ አለ፦ “በፀሐይና በጨረቃ፥ በከዋክብትም ላይ ድንቅ ምልክቶች ይታያሉ፤ በምድርም ላይ ሕዝቦች ሁሉ ከባሕርና ከማዕበሉ አስደንጋጭ ድምፅ የተነሣ ፈርተው ይጨነቃሉ። #ኢሳ. 13፥10፤ ሕዝ. 32፥7፤ ኢዩ. 2፥31፤ ራዕ. 6፥12-13። 26በዓለም ላይ የሚመጣውን ነገር በመጠባበቅ ሰዎች በፍርሃት ይሸበራሉ፤ በዚያን ጊዜ የሰማይ ኀይሎች ይናወጣሉ፤ 27ከዚህም በኋላ የሰው ልጅ በታላቅ ኀይልና ክብር በደመና ላይ ሆኖ ሲመጣ ሰዎች ያዩታል። #ዳን. 7፥13፤ ራዕ. 1፥7። 28ይህ ሁሉ መሆን በሚጀምርበት ጊዜ መዳናችሁ ቀርቦአልና ቀና ብላችሁ ወደ ላይ ተመልከቱ።”
የጌታን መምጫ የምታመለክት የበለስ ዛፍ ምሳሌ
(ማቴ. 24፥32-35ማር. 13፥28-31)
29ቀጥሎም ኢየሱስ ይህን ምሳሌ ነገራቸው፦ “የበለስን ዛፍና የሌሎችንም ዛፎች ሁኔታ ልብ ብላችሁ ተመልከቱ፤ 30ቅጠሎቻቸው ሲያቈጠቊጡ ባያችሁ ጊዜ በጋ እንደ ቀረበ ታውቃላችሁ። 31በዚህ ዐይነት ይህ ሁሉ ነገር መሆን ሲጀምር ባያችሁ ጊዜ የእግዚአብሔር መንግሥት ልትመጣ መቃረብዋን ዕወቁ።
32“በእውነት እላችኋለሁ፤ ይህ ሁሉ እስኪፈጸም ድረስ ይህ ትውልድ አያልፍም። 33ሰማይና ምድር ያልፋሉ፤ ቃሌ ግን አያልፍም።”
ተግቶ ስለ መጠበቅ
34ቀጥሎም ኢየሱስ እንዲህ አለ፦ “በመብልና በመጠጥ ብዛት በስካርም በመባከንና ስለ ዓለማዊ ኑሮ በመጨነቅ ልባችሁ እንዳይዝል ተጠንቀቁ! አለበለዚያ ያ ቀን እንደ ወጥመድ በድንገት ይይዛችኋል። 35ያ ቀን በምድር ላይ የሚገኙትን ሰዎች ሁሉ በድንገት ያጠምዳቸዋል። 36ስለዚህ ከሚመጣው ክፉ ነገር ሁሉ ለማምለጥ ኀይል እንድታገኙና በሰው ልጅ ፊት ለመቆም እንድትችሉ እየጸለያችሁ ዘወትር ትጉ።”
37ኢየሱስ በየቀኑ በቤተ መቅደስ ያስተምር ነበር፤ ሲመሽ ግን ደብረ ዘይት ወደምትባል ተራራ ላይ እየወጣ ያድር ነበር። #ሉቃ. 19፥47። 38ሰዎቹ ሁሉ ኢየሱስን ለመስማት ጠዋት በማለዳ ወደ ቤተ መቅደስ ወደ እርሱ ይሄዱ ነበር።

Highlight

Share

Copy

None

Want to have your highlights saved across all your devices? Sign up or sign in