YouVersion Logo
Search Icon

የሉቃስ ወንጌል 10

10
ኢየሱስ ወንጌልን እንዲያስተምሩ ሰባ ሁለቱን ደቀ መዛሙርት መላኩ
1ከዚህ በኋላ ጌታ፥ ሌሎች ሰባ ሁለት ሰዎችን መረጠ፤ እርሱ ሊሄድበት ወደአሰበውም ከተማና ቦታ ሁሉ ቀድመውት እንዲሄዱ ሁለት ሁለት አድርጎ ላካቸው። #10፥1 ሰባ ሁለት፦ አንዳንድ የብራና ጽሑፎች “ሰባ” ይላሉ። 2እንዲህም አላቸው፦ “እነሆ፥ መከሩ ብዙ ነው፤ የመከሩ ሠራተኞች ግን ጥቂቶች ናቸው፤ ስለዚህ የመከሩ ጌታ ለመከሩ ሥራ ተጨማሪ ሠራተኞችን እንዲልክ ለምኑት። #ማቴ. 9፥37-38። 3እንግዲህ ሂዱ፤ እነሆ፥ እንደ በጎች በተኲላዎች መካከል እልካችኋለሁ፤ #ማቴ. 10፥16። 4ለመንገዳችሁ ምንም አትያዙ፤ የገንዘብ ቦርሳም ቢሆን፥ ከረጢትም ቢሆን፥ ጫማም ቢሆን አትያዙ፤ ከሰው ጋር ሰላምታ በመለዋወጥ በመንገድ ላይ ቆማችሁ ጊዜ አታጥፉ። #ማቴ. 10፥7-14፤ ማር. 6፥8-11፤ ሉቃ. 9፥3-5። 5በገባችሁበት ቤት ሁሉ አስቀድማችሁ ‘ሰላም ለዚህ ቤት ይሁን፥’ በሉ፤ 6ሰላም ወዳድ ሰው በዚያ ቤት ቢኖር ሰላማችሁ ያድርበታል፤ አለበለዚያ ግን ሰላማችሁ ወደ እናንተ ይመለሳል። 7ለሠራተኛ ደመወዝ ይገባዋል፤ ስለዚህ በገባችሁበት ቤት ያቀረቡላችሁን እየበላችሁና እየጠጣችሁ ቈዩ፤ ከቤት ወደ ቤትም አትዘዋወሩ። #1ቆሮ. 9፥14፤ 1ጢሞ. 5፥18። 8በማናቸውም ከተማ ስትገቡና ሰዎችም ሲቀበሉአችሁ የሚያቀርቡላችሁን ብሉ። 9በዚያችም ከተማ የሚገኙትን በሽተኞች ፈውሱ፤ ለሕዝቡም፦ ‘የእግዚአብሔር መንግሥት ወደ እናንተ ቀርባለች፤’ እያላችሁ ተናገሩ። 10ነገር ግን በማናቸውም ከተማ ስትገቡ ሰዎቹ የማይቀበሉአችሁ ቢሆን ወደ ከተማይቱ አደባባይ ውጡና እንዲህ በሉአቸው፦ 11‘እነሆ፥ በእግራችን ላይ ያለውን የከተማችሁን ትቢያ እንኳ እናራግፍላችኋለን፤ ነገር ግን የእግዚአብሔር መንግሥት ወደ እናንተ እንደ ቀረበች ዕወቁ።’ #ሐ.ሥ. 13፥51። 12በፍርድ ቀን ከዚህች ከተማ ይልቅ ለሰዶም ከተማ ቅጣቱ ይቀልላታል እላችኋለሁ።” #ዘፍ. 19፥24-28፤ ማቴ. 11፥24፤ 10፥15።
ባለማመናቸው የተወቀሱ ከተሞች
(ማቴ. 11፥20-24)
13ቀጥሎም ኢየሱስ እንዲህ አለ፦ “ወዮልሽ ኮራዚን! ወዮልሽ ቤተ ሳይዳ! በእናንተ የተደረጉት ተአምራት፥ በጢሮስና በሲዶና ተደርገው ቢሆን ኖሮ በዚያ ይኖሩ የነበሩ ሰዎች የሐዘን ልብስ ለብሰውና ዐመድ ላይ ተቀምጠው፥ ገና ዱሮ ንስሓ በገቡ ነበር። #ኢሳ. 23፥1-8፤ ሕዝ. 26፥1—28፥26፤ ኢዩ. 3፥4-8፤ አሞጽ 1፥9-10፤ ዘካ. 9፥2-4። 14ስለዚህ በፍርድ ቀን ከእናንተ ይልቅ ለጢሮስና ለሲዶና ቅጣቱ ይቀልላቸዋል። 15አንቺም ቅፍርናሆም! እስከ ሰማይ ከፍ ለማለት ፈልገሻልን? ታዲያ ወደ ሲኦል ትወርጂአለሽ።” #ኢሳ. 14፥13-15።
16እንደገናም ኢየሱስ ደቀ መዛሙርቱን፦ “እናንተን የሚሰማ እኔን ይሰማል፤ እናንተን የማይቀበል እኔን አይቀበልም፤ እኔን የማይቀበልም የላከኝን አይቀበልም፤” አላቸው። #ማቴ. 10፥40፤ ማር. 9፥37፤ ሉቃ. 9፥48፤ ዮሐ. 13፥20።
ሰባ ሁለቱ ደቀ መዛሙርት ከተላኩበት ተመልሰው መምጣታቸው
17ሰባ ሁለቱ ደቀ መዛሙርት ከተላኩበት በጣም ደስ ብሎአቸው ተመለሱ፤ ወደ ኢየሱስም ቀርበው፦ “ጌታ ሆይ! በአንተ ስም አጋንንት እንኳ ታዘውልናል” አሉት።
18ኢየሱስም እንዲህ አላቸው፦ “ሰይጣን እንደ መብረቅ ተወርውሮ ከሰማይ ሲወድቅ አየሁት፤ 19እነሆ! እባብንና ጊንጥን እንድትረግጡ፥ የጠላትንም ኀይል ሁሉ እንድትቋቋሙ ሥልጣን ሰጥቻችኋለሁ፤ የሚጐዳችሁ ምንም ነገር የለም። #መዝ. 91፥13። 20ነገር ግን ስማችሁ በሰማይ መዝገብ ስለ ተጻፈ ደስ ይበላችሁ እንጂ አጋንንት ስለ ታዘዙላችሁ አትደሰቱ።”
ኢየሱስ ደስታውን እንደ ገለጠ
(ማቴ. 11፥25-2713፥16-17)
21በዚያን ጊዜ ኢየሱስ በቅዱስ መንፈሱ ተደስቶ እንዲህ አለ፦ “የሰማይና የምድር ጌታ አባት ሆይ! ይህንን ነገር ከጥበበኞችና ከዐዋቂዎች ሰውረህ ላልተማሩት ስለ ገለጽክላቸው አመሰግንሃለሁ፤ አዎ፥ አባት ሆይ፥ ይህን ለማድረግ የአንተ በጎ ፈቃድ ሆኖአል።
22“ሁሉ ነገር ከአባቴ ተሰጥቶኛል፤ ወልድ ማን መሆኑን ከአብ በቀር ማንም የሚያውቅ የለም፤ እንዲሁም አብ ማን መሆኑን ከወልድ በቀር ወይም ወልድ ሊገልጥለት ከሚፈቅድለት ሰው በቀር ሌላ ማንም የሚያውቅ የለም።” #ዮሐ. 3፥35፤ 10፥15።
23ቀጥሎም ኢየሱስ ወደ ደቀ መዛሙርቱ መለስ ብሎ ለብቻቸው እንዲህ አላቸው፦ “እናንተ የምታዩትን የሚያዩ የተባረኩ ናቸው። 24በእውነቱ ብዙዎች ነቢያትና ነገሥታት እናንተ የምታዩትን ለማየት ተመኝተው ነበር፤ ነገር ግን አላዩም፤ እናንተ የምትሰሙትንም ለመስማት ተመኝተው ነበር፤ ነገር ግን አልሰሙም።”
ርኅሩኍ ሳምራዊ
25አንድ ቀን አንድ የሕግ መምህር ወደ ኢየሱስ መጣ፤ ሊፈትነውም ፈልጎ “መምህር ሆይ! የዘለዓለምን ሕይወት ለማግኘት ምን ማድረግ ይገባኛል?” ሲል ጠየቀው። #ማቴ. 22፥35-40፤ ማር. 12፥28-34። 26ኢየሱስም “በሕግ ምን ተጽፎአል? አንብበህስ እንዴት ትረዳዋለህ?” አለው።
27ሰውየውም “ሕጉማ ‘ጌታ አምላክህን በፍጹም ልብህ፥ በፍጹም ነፍስህ፥ በፍጹም ኀይልህ፥ በፍጹም ሐሳብህ ውደድ፤’ እንዲሁም ‘ጐረቤትህን እንደ ራስህ አድርገህ ውደድ፤’ ይላል” አለው። #ዘሌ. 19፥18፤ ዘዳ. 6፥5።
28ኢየሱስም “በትክክል መልሰሃል፤ እንግዲህ አንተም ይህን አድርግ! የዘለዓለም ሕይወትንም ታገኛለህ” አለው። #ዘሌ. 18፥5።
29የሕግ መምህሩ ግን ራሱን ጻድቅ ለማድረግ ፈልጎ፥ “ለመሆኑ ባልንጀራዬ ማን ነው?” ሲል ጠየቀው።
30ኢየሱስም እንዲህ ሲል መለሰለት፦ “አንድ ሰው ከኢየሩሳሌም ወደ ኢያሪኮ ሲወርድ በመንገድ ላይ ሳለ ቀማኞች አግኝተውት ልብሱን ገፈፉት፤ ከደበደቡትም በኋላ ሊሞት ሲያጣጥር ጥለውት ሄዱ። 31እንደ አጋጣሚ አንድ ካህን በዚያ መንገድ ይሄድ ነበር፤ ተደብድቦ የተጣለውን ሰው ባየው ጊዜ ምንም ሳያደርግለት በሌላ በኩል አልፎ ሄደ። 32እንዲሁም አንድ ሌዋዊ በዚያ መንገድ ይሄድ ነበር፤ እርሱም ሰውየውን ባየው ጊዜ ምንም ሳያደርግለት በሌላ በኩል አልፎ ሄደ። 33አንድ ሳምራዊ ግን በዚያ በኩል ሲያልፍ ወደ ሰውየው መጣ፤ ባየውም ጊዜ ራራለት፤ 34ወደ እርሱም ቀርቦ ዘይትና የወይን ጠጅ በቊስሉ ላይ አፈሰሰ፤ በጨርቅም ጠምጥሞ አሠረለት፤ ከዚያም በኋላ በገዛ ራሱ አህያ ላይ አስቀምጦት ወደ አንድ የእንግዶች ማደሪያ ቤት ወሰደው፤ በዚያም በልዩ ጥንቃቄ ተንከባከበው፤ #2ዜ.መ. 28፥15። 35በማግስቱም ሁለት ዲናር አውጥቶ ለእንግዳ ማደሪያው ባለቤት ሰጠና ‘ይህን ሰው በጥንቃቄ አስታምልኝ፤ ተጨማሪ ወጪ ብታደርግም በምመለስበት ጊዜ እከፍልሃለሁ፤’ አለው። #10፥35 ዲናር፦ የአንድ የቀን ሠራተኛ የአንድ ቀን ደመወዝ ነው።
36“ታዲያ፥ ከእነዚህ ከሦስት ሰዎች፥ በቀማኞቹ ተደብድቦ ለወደቀው ሰው ባልንጀራ የሆነለት የትኛው ይመስልሃል?”
37የሕግ መምህሩም “ያ የራራለትና የረዳው ነው፤” ሲል መለሰ፤
ኢየሱስም “እንግዲያውስ ሂድ፤ አንተም እንዲሁ አድርግ!” አለው።
ኢየሱስ በማርታና በማርያም ቤት
38ኢየሱስ ከደቀ መዛሙርቱ ጋር መንገዱን ቀጥሎ ወደ አንዲት መንደር ደረሰ፤ በዚያም ማርታ የምትባል አንዲት ሴት በቤትዋ ተቀበለችው፤ 39እርስዋ ማርያም የምትባል እኅት ነበረቻት፤ ይህች ማርያም በኢየሱስ እግር ሥር ተቀምጣ ትምህርቱን ታደምጥ ነበር። #ዮሐ. 11፥1። 40ማርታ ግን ምግብ በማዘጋጀት በብርቱ ትደክም ነበር፤ ስለዚህ ወደ ኢየሱስ ቀርባ፥ “ጌታ ሆይ! ይህች እኅቴ ሥራውን ሁሉ ለእኔ ትታ ብቻዬን ስደክም እያየህ ዝም ትላለህን? እባክህ እንድታግዘኝ ንገራት!” አለችው።
41ጌታ ኢየሱስ ግን እንዲህ ሲል መለሰላት፦ “ማርታ፥ ማርታ፥ አንቺ በብዙ ነገር ትጨነቂያለሽ፤ ትታወኪያለሽም፤ 42ነገር ግን ተፈላጊው አንድ ነገር ብቻ ነው፤ ማርያም የሚሻለውን ነገር መርጣለች፤ እርሱንም ከእርስዋ የሚወስድባት ማንም የለም።”

Highlight

Share

Copy

None

Want to have your highlights saved across all your devices? Sign up or sign in