YouVersion Logo
Search Icon

የሉቃስ ወንጌል 1

1
1የተከበርክ ቴዎፍሎስ ሆይ፥
በእኛ መካከል የተፈጸሙትን ነገሮች የሚገልጥ ታሪክ ከዚህ ቀደም ብዙዎች ጽፈዋል። 2ይህን መልእክት ለእኛ ያስተላለፉልን ከመጀመሪያው አንሥቶ የዐይን ምስክሮችና የቃሉ አገልጋዮች የነበሩት ናቸው። 3እንዲሁም እኔ ከመጀመሪያው አንሥቼ ሁሉን ነገር በጥንቃቄ ከመረመርኩ በኋላ ታሪኩን በቅደም ተከተል እጽፍልህ ዘንድ መልካም ሆኖ አገኘሁት። 4ይህንንም ማድረጌ የተማርከውን ትምህርት እውነተኛነት በደምብ እንድትረዳ ብዬ ነው።
የመጥምቁ ዮሐንስን መወለድ መልአኩ ገብርኤል አስቀድሞ መናገሩ
5ሄሮድስ በይሁዳ ምድር ንጉሥ በነበረበት ዘመን፥ ከአብያ የክህነት አገልግሎት ክፍል የሆነ ዘካርያስ የሚባል ካህን ነበር። እርሱም ከአሮን ዘር የምትወለድ ኤልሳቤጥ የምትባል ሚስት ነበረችው። #1ዜ.መ. 24፥10። 6ሁለቱም በእግዚአብሔር ፊት ጻድቃን ነበሩ፤ የጌታንም ትእዛዝና ሥርዓት ያለ ነቀፋ ይጠብቁ ነበር። 7ኤልሳቤጥ መኻን ስለ ነበረች ልጅ አልነበራቸውም፤ ደግሞ ሁለቱም በጣም አርጅተው ነበር።
8በዚያን ጊዜ የዘካርያስ የክህነት ቡድን ለቤተ መቅደስ አገልግሎት ተረኛ ነበር፤ ስለዚህ እርሱ በእግዚአብሔር ፊት የክህነቱን አገልግሎት በመፈጸም ላይ ነበር። 9እንደ ካህናት አሠራር ልማድ ወደ ጌታ ቤተ መቅደስ ገብቶ ዕጣን ለማጠን ዕጣ ደረሰው። 10በቤተ መቅደሱም ውስጥ ዕጣን በሚታጠንበት ጊዜ፥ ሕዝቡ ሁሉ በውጪ ቆመው ይጸልዩ ነበር። 11የጌታ መልአክ ዕጣን በሚጤስበት መሠዊያ በስተቀኝ በኩል ቆሞ ለዘካርያስ ታየው። 12ዘካርያስ መልአኩን ባየው ጊዜ ደንግጦ በፍርሃት ተዋጠ። 13መልአኩ ግን እንዲህ አለው፦ “ዘካርያስ ሆይ! አትፍራ! ጸሎትህ ተሰምቶልሃል፤ ሚስትህ ኤልሳቤጥ ወንድ ልጅ ትወልድልሃለች፤ ስሙንም ዮሐንስ ብለህ ትጠራዋለህ። 14የእርሱ መወለድ ለአንተ ተድላና ደስታ ይሆንልሃል፤ ብዙዎችም በመወለዱ እንዲሁ ደስ ይላቸዋል። 15እርሱ በጌታ ፊት ታላቅ ይሆናል፤ የወይን ጠጅና ሌላም የሚያሰክር መጠጥ አይጠጣም፤ ገና በእናቱ ማሕፀን ሳለ በመንፈስ ቅዱስ የተሞላ ይሆናል። #ዘኍ. 6፥3። 16እርሱ ከእስራኤል ሕዝብ ብዙዎቹን ወደ ጌታ ወደ አምላካቸው ይመልሳቸዋል፤ 17ልክ እንደ ነቢዩ ኤልያስ በመንፈስና በኀይል ሆኖ እርሱ የአባቶችን ልብ ወደ ልጆቻቸው፥ የማይታዘዙትንም ሰዎች ልብ ወደ ጻድቃን ጥበብ ይመልሳል፤ ሕዝቡንም በማንቃት ለጌታ እንዲዘጋጅ ያደርጋል።” #ሚል. 4፥5-6።
18ዘካርያስ ግን መልአኩን “ይህ ነገር እርግጥ መሆኑን በምን ዐውቃለሁ? እኔ አርጅቻለሁ፤ ሚስቴም በዕድሜዋ ገፍታለች” አለው።
19መልአኩም እንዲህ ሲል መለሰለት፦ “እኔ በእግዚአብሔር ፊት የምቆመው ገብርኤል ነኝ፤ ይህን የምሥራች እንድነግርህ ከእግዚአብሔር ዘንድ ተልኬ መጥቻለሁ። #ዳን. 8፥16፤ 9፥21። 20አንተ ግን ጊዜው ሲደርስ የሚፈጸመውን ቃሌን አላመንክም፤ ስለዚህ ይህ የነገርኩህ ሁሉ እስከሚፈጸም ድረስ ድዳ ትሆናለህ፤ መናገርም አትችልም።”
21በዚህ ጊዜ ሰዎቹ ዘካርያስን ይጠባበቁ ነበር፤ በቤተ መቅደስ ውስጥ ስለ ዘገየባቸውም ተገረሙ። 22ዘካርያስ ከቤተ መቅደስ በወጣ ጊዜ ከሰዎቹ ጋር መነጋገር አልቻለም፤ ስለዚህ እነርሱ በቤተ መቅደሱ ውስጥ ራእይ የታየው መሆኑን ዐወቁ፤ እርሱ በእጁ እየጠቀሰ ያስረዳቸው ነበር። በዚህም ሁኔታ ዱዳ ሆኖ ቈየ።
23የአገልግሎቱም ጊዜ ከተፈጸመ በኋላ ዘካርያስ ወደ ቤቱ ሄደ። 24ከጥቂት ጊዜም በኋላ ሚስቱ ኤልሳቤጥ ፀነሰች፤ አምስት ወር በቤትዋ ውስጥ ተሸሽጋ ቈየች፤ እንዲህም አለች፦ 25“ጌታ ይህን መልካም ነገር አደረገልኝ፤ በሰዎች መካከል የነበረብኝን ነቀፌታ አስወገደልኝ።”
የኢየሱስን መወለድ መልአኩ ገብርኤል ማብሠሩ
26ኤልሳቤጥ በፀነሰች በስድስተኛው ወር መልአኩ ገብርኤል በገሊላ ምድር ወደምትገኝ ናዝሬት ወደምትባል ከተማ ከእግዚአብሔር ተላከ። 27የተላከውም ከዳዊት ዘር ለሆነ ዮሴፍ ለሚባል ሰው ወደታጨች ወደ አንዲት ድንግል ነበር፤ የድንግሊቱም ስም ማርያም ነበር። #ማቴ. 1፥18። 28መልአኩም ወደ እርስዋ መጥቶ፦ “አንቺ ጸጋን የተሞላሽ፥ ሰላም ለአንቺ ይሁን! ጌታ ከአንቺ ጋር ነው፤ [አንቺ ከሴቶች መካከል የተባረክሽ ነሽ]” አላት።
29እርስዋም በመልአኩ አነጋገር በጣም ደንግጣ፥ “ይህ ምን ዐይነት ሰላምታ ይሆን?” ብላ አሰበች። 30መልአኩም እንዲህ አላት፤ “ማርያም ሆይ! በእግዚአብሔር ፊት ሞገስ አግኝተሻልና አትፍሪ፤ 31እነሆ! ትፀንሺአለሽ፤ ወንድ ልጅም ትወልጃለሽ፤ ስሙንም ኢየሱስ ትዪዋለሽ። #ማቴ. 1፥21። 32እርሱ ታላቅ ይሆናል፤ የልዑል እግዚአብሔር ልጅም ይባላል፤ ጌታ አምላክ የአባቱን የዳዊትን ዙፋን ይሰጠዋል። 33በእስራኤልም ላይ ለዘለዓለም ይነግሣል፤ ለመንግሥቱም መጨረሻ የለውም።” #2ሳሙ. 7፥12-13፤16፤ ኢሳ. 9፥7።
34ማርያም መልአኩን “እኔ ድንግል ነኝ፤ ታዲያ፥ ይህ ነገር እንዴት ሊሆን ይችላል?” አለችው።
35መልአኩም እንዲህ ሲል መለሰ፦ “መንፈስ ቅዱስ በአንቺ ላይ ይመጣል፤ የልዑል እግዚአብሔርም ኀይል በአንቺ ላይ ይሆናል፤ ስለዚህ ከአንቺ የሚወለደው ሕፃን ቅዱስ ነው፤ የእግዚአብሔርም ልጅ ይባላል። 36ዘመድሽ ኤልሳቤጥ እንኳ መኻን ስትባል ኖራ አሁን በስተእርጅናዋ ወንድ ልጅ ፀንሳለች፤ ከፀነሰችም እነሆ፥ ስድስተኛ ወርዋ ነው። 37ለእግዚአብሔር የሚሳነው ነገር የለም።” #ዘፍ. 18፥14።
38ከዚያም በኋላ ማርያም፥ “እነሆ! እኔ የጌታ አገልጋይ ነኝ፤ አንተ እንዳልክ ይሁንልኝ” አለችው። በዚህ ጊዜ መልአኩ ተለይቶአት ሄደ።
ማርያም ኤልሳቤጥን መጐብኘትዋ
39በዚያን ጊዜ ማርያም በተራራማው በይሁዳ አገር ወዳለችው ከተማ በፍጥነት ተነሥታ ሄደች። 40ወደ ዘካርያስ ቤትም ገብታ ለኤልሳቤጥ ሰላምታ ሰጠቻት። 41ኤልሳቤጥ የማርያምን የሰላምታ ቃል በሰማች ጊዜ በማሕፀንዋ የነበረው ሕፃን ዘለለ። ኤልሳቤጥም በመንፈስ ቅዱስ ተሞልታ፥ 42ድምፅዋንም ከፍ አድርጋ እንዲህ አለች፦ “አንቺ ከሴቶች መካከል የተባረክሽ ነሽ፤ ከአንቺ የሚወለደውም የተባረከ ነው። 43የጌታዬ እናት ልትጐበኘኝ መምጣትዋ ለእኔ እንዴት ያለ ታላቅ ክብር ነው፤ 44ገና የሰላምታሽን ድምፅ ከመስማቴ በማሕፀኔ ያለው ሕፃን በደስታ ዘለለ። 45አንቺ ጌታ የተናገረውን ሁሉ የሚፈጽም መሆኑን በማመንሽ ምንኛ የተባረክሽ ነሽ!”
የማርያም የምስጋና ጸሎት
46ማርያምም እንዲህ አለች፦
“ነፍሴ ጌታን ታመሰግናለች፤ #1ሳሙ. 2፥1-10።
47መንፈሴም በአምላኬ በመድኃኒቴ ትደሰታለች፤
48እግዚአብሔር እኔን ዝቅተኛ አገልጋይቱን ተመልክቶአልና፥
ከዛሬ ጀምሮ ትውልድ ሁሉ የተባረክሽ ነሽ ይሉኛል፤ #1ሳሙ. 1፥11።
49ኀያሉ እግዚአብሔር ታላላቅ ነገሮችን አድርጎልኛልና።
ስሙም ቅዱስ ነው።
50እግዚአብሔር ለሚፈሩት ሰዎች ሁሉ
ከትውልድ እስከ ትውልድ ምሕረቱን ያደርጋል።
51በብርቱ ክንዱ ኀይሉን አሳይቶአል፤
ትዕቢተኞችንም ከነሐሳባቸው በትኖአቸዋል።
52ታላላቅ ገዢዎችን ከዙፋናቸው አውርዶአቸዋል፤
ዝቅተኞችን ግን በክብር ከፍ አድርጎአቸዋል። #ኢዮብ 5፥11፤ 12፥19።
53የተራቡትን በመልካም ነገር አጥግቦአቸዋል፤
ሀብታሞችን ግን ባዶ እጃቸውን ሰዶአቸዋል፤
54-55ለአብርሃምና ለዘሩ ለዘለዓለም ያሳየውን ምሕረት በማስታወስ፥
አገልጋዩን እስራኤልን ረድቶታል።
ይህንንም ያደረገው ለቀድሞ አባቶቻችን የሰጠውን የተስፋ ቃል ለመፈጸም ነው።” #ዘፍ. 17፥7።
56ማርያምም ከኤልሳቤጥ ጋር ሦስት ወር ያኽል ከቈየች በኋላ ወደ ቤትዋ ተመልሳ ሄደች።
የመጥምቁ ዮሐንስ መወለድ
57ኤልሳቤጥ የመውለጃዋ ጊዜ ደረሰና ወንድ ልጅ ወለደች። 58ጐረቤቶችዋና ዘመዶችዋ ሁሉ ጌታ ታላቅ ምሕረቱን እንዳደረገላት ሰምተው ከእርስዋ ጋር ተደሰቱ።
59ሕፃኑ በተወለደ በስምንተኛው ቀን፥ በግዝረቱ ሥነ ሥርዓት ላይ ለመገኘት ጐረቤቶችዋና ዘመዶችዋ ተሰብስበው መጡ፤ ባባቱ ስም ዘካርያስ ብለው ሊጠሩት ፈልገው ነበር፤ #ዘሌ. 12፥3። 60እናቱ ግን “እንዲህ አይሆንም፤ ስሙ ዮሐንስ ነው” አለች።
61እነርሱም “ከዘመዶችሽ በዚህ ስም የተጠራ ማንም የለም?” አሉአት። 62ከዚህም በኋላ አባቱን፦ “ልጅህ ማን ተብሎ እንዲጠራ ትፈልጋለህ?” ብለው በምልክት ጠየቁት።
63ዘካርያስም መጻፊያ እንዲሰጡት ጠይቆ፦ “ስሙ ዮሐንስ ነው” ብሎ ጻፈ፤ ሁሉም በዚህ ነገር ተደነቁ። 64በዚያኑ ጊዜ ዘካርያስ አንደበቱ ተፈቶለት መናገር ቻለ፤ እግዚአብሔርንም ማመስገን ጀመረ። 65ከዚህም የተነሣ በጐረቤቶቻቸው ሁሉ ፍርሀት አደረባቸው፤ ዜናውም በተራራማው በይሁዳ ምድር ሁሉ ተሰማ። 66ይህን ነገር የሰሙ ሁሉ፥ “ይህ ሕፃን ምን ሊሆን ይሆን?” እያሉ ይጠያየቁ ነበር። ይህም የሆነው የእግዚአብሔር ረድኤት በእርግጥ ከእርሱ ጋር ስለ ነበር ነው።
ዘካርያስ የተናገረው ትንቢት
67የሕፃኑ አባት ዘካርያስ በመንፈስ ቅዱስ ተሞልቶ እንዲህ ሲል ትንቢት ተናገረ፦
68“ሕዝቡን በምሕረት ስለ ጐበኘና ስላዳነ፥
የእስራኤል አምላክ፥ ጌታ ይመስገን!
69ከአገልጋዩ ከዳዊት ዘር ኀያል አዳኝ አስነሥቶልናል፤
70ከጥንት ዘመን ጀምሮ በነበሩት በቅዱሳን ነቢያቱ አፍ እንደ ተናገረ፤
71ከጠላቶቻችንና ከባላጋራዎቻችን እጅ አድኖናል፤
72ይህንንም ማድረጉ ለአባቶቻችን ምሕረትን እንደሚያደርግና
የተናገረውንም ቅዱስ ቃል ኪዳኑን እንደሚፈጽም በማሰብ ነው።
73ይህንንም ቃል ኪዳን፥ በመሐላ የሰጠው ለአባታችን ለአብርሃም ነበር፤
74የተስፋውም ቃል ከጠላቶቻችን እጅ ነጻ ወጥተን፥
ያለ ፍርሀት እንድናገለግለው ነው፤
75እንዲሁም በሕይወታችን ዘመን ሁሉ፥
በእግዚአብሔር ፊት በቅድስናና በጽድቅ መኖር እንድንችል ነው።
76ደግሞም አንተ ሕፃን፥ የልዑል እግዚአብሔር ነቢይ ትባላለህ።
መንገዱን ለማዘጋጀት ቀድመህ በጌታ ፊት ትሄዳለህ። #ሚል. 3፥1።
77ጌታም ኃጢአታቸውን ይቅር በማለት
የመዳንን ዕውቀት ይሰጣቸዋል።
78አምላካችን መሓሪና ርኅሩኅ በመሆኑ የደኅንነት ብርሃን ከወደላይ እንዲበራልን ያደርጋል።
79እርሱ በጨለማና በሞት ጥላ ሥር ላሉት ሁሉ ያበራል፤
እርምጃችንንም ወደ ሰላም መንገድ ይመራል።”
80ሕፃኑም አደገ፤ በመንፈስም ጠነከረ፤ ለእስራኤል ሕዝብ እስከ ታየበት ጊዜ ድረስ በበረሓ ኖረ።

Highlight

Share

Copy

None

Want to have your highlights saved across all your devices? Sign up or sign in