መጽሐፈ ኢያሱ 11
11
ኢያሱ ያቢንንና የጦር ተባባሪዎቹን ድል ማድረጉ
1የሐጾር ንጉሥ ያቢን የእስራኤልን ድል አድራጊነት በሰማ ጊዜ፥ ወደ ማዶን ንጉሥ ዮባብ፥ ወደ ሺምሮንና ወደ አክሻፍ ነገሥታት፥ 2በሰሜን በኩል በኮረብታማው አገር፥ ከገሊላ ባሕር በስተ ደቡብ ወደ ነበሩበት ነገሥታት፥ በዮርዳኖስ ሸለቆ፥ በኮረብታዎቹ ግርጌ በስተምዕራብም በፎት ዳር ወደ ነበሩት ነገሥታት ላከ። 3እንዲሁም ከዮርዳኖስ በስተ ምሥራቅና በስተ ምዕራብ ወደሚገኙት ወደ ከነዓናውያን፥ ወደ አሞራውያን፥ ወደ ሒታውያን፥ ወደ ፈሪዛውያንና፥ በኮረብታማው አገር ወደሚገኙት ወደ ኢያቡሳውያን፥ እንዲሁም በምጽጳ ምድር በሔርሞን ተራራ ግርጌ ወደሚገኙት ወደ ሒዋውያን ሁሉ መልእክት ላከ። 4እነርሱም ከነወታደሮቻቸው ስለ መጡ፥ የሠራዊቱ ብዛት እንደ ባሕር አሸዋ ሆነ፤ ከዚህም ሁሉ ጋር ብዙ ፈረሶችና ሠረገሎች ነበራቸው። 5እነዚህም ሁሉ ነገሥታት ኀይላቸውን አስተባብረው እስራኤላውያንን ለመውጋት በሜሮም ምንጭ አጠገብ ሰፈሩ።
6እግዚአብሔርም ኢያሱን “እነርሱን አትፍራ፤ ስለ እስራኤል በመዋጋት ነገ ይህን ጊዜ ሁሉንም እንደ ሞቱ አድርጌ በእስራኤል እጅ አሳልፌ እሰጣቸዋለሁ፤ አንተም የፈረሶቻቸውን ቋንጃ ትቈርጣለህ፤ ሠረገሎቻቸውንም በእሳት ታቃጥላለህ” አለው። 7ስለዚህም ኢያሱና መላ ሠራዊቱ ዘምተው በሜሮም ድንገተኛ አደጋ ጣሉባቸው። 8እግዚአብሔርም እስራኤላውያን በእነርሱ ላይ ድልን እንዲቀዳጁ አደረጋቸው፤ እስራኤላውያንም መተው በሰሜን እስከ ሚስረፎትማይምና እስከ ታላቂቱ ሲዶና፥ በምሥራቅም እስከ ምጽጳ ሸለቆ ድረስ አሳደዱአቸው፤ ከእነርሱም አንድ ሰው እንኳ ሳይተርፍ ሁሉንም ፈጁአቸው። 9ኢያሱም በእነርሱ ላይ እግዚአብሔር ያዘዘውን ሁሉ አደረገ። ይኸውም የፈረሶቻቸውን ቋንጃ ቈረጠ፤ ሠረገሎቻቸውንም በእሳት አቃጠለ።
10ኢያሱም ወደ ኋላ ተመልሶ ሐጾርን ድል ነሥቶ ያዘ፤ ንጉሥዋንም በሰይፍ ገደለ፤ ሐጾር በዚያን ዘመን ከነበሩት የዘውድ መንግሥታት ሁሉ የሚበልጥ ኀይል ያላት ነበረች። 11እስራኤላውያን በሐጾር የተገኘውን ሰው ሁሉ ስለ ገደሉ በሕይወት የተረፈ አልነበረም፤ ከተማይቱም በእሳት ተቃጠለች።
12የእግዚአብሔር አገልጋይ ሙሴ ባዘዘው መሠረት ኢያሱ እነዚህን ከተሞችና ንጉሦቻቸውን ሁሉ ማረከ፤ በሰይፍም መታቸው፤ ፈጽሞም አጠፋቸው። 13ይሁን እንጂ ኢያሱ ካቃጠላት ከሐጾር በቀር እስራኤላውያን በኮረብታ ላይ የተሠሩ ከተሞችን አላቃጠሉም። 14የእስራኤል ሕዝብ ዋጋ ያለውን ንብረትና ከብቱን ሁሉ ከእነዚህ ከተሞች ወስደው የራሳቸው ንብረት አደረጉት፤ ሰዎቹን ሁሉ ግን በሰይፍ ስለት ፈጽመው አጠፉ፤ አንድ ሰው እንኳ ሳይቀር ሁሉንም ገደሉ። 15እግዚአብሔር ትእዛዙን ለአገልጋዩ ለሙሴ ሰጠ፤ ሙሴም ለኢያሱ ሰጠ፤ ኢያሱም ትእዛዞችን ፈጸመ፤ እግዚአብሔር ሙሴን ባዘዘው መሠረት ኢያሱ ሁሉን ነገር አደረገ፤ አንዳችም አላስቀረም።
ኢያሱ የያዛቸው አገሮች ዝርዝር
16ኢያሱ እነዚያን አገሮች፦ ተራራማውን፥ ኔጌብን፥ የጎሼንን ምድር፥ ቈላማውን፥ የዮርዳኖስን ሸለቆ፥ ቈላማውንና ደጋማውን የእስራኤልን ምድር ሁሉ ያዘ። 17እርሱም ወደ ኤዶም ከሚያወጣው ከሐላቅ ተራራ ጀምሮ ከሔርሞን ተራራ በታች እስከ ሊባኖስ ሸለቆ እስከ ባዓልጋድ ድረስ ያሉትን ነገሥታት ሁሉ ማርኮ መታቸው፤ ገደላቸውም፤ 18ኢያሱም ከእነዚህ ነገሥታት ሁሉ ጋር ይዋጋ ነበር። 19ከእስራኤል ሕዝብ ጋር ስምምነት አድርጋ በሰላም የኖረች አገር ከሒዋውያን ወገን የገባዖን ኑዋሪዎች በቀር ሌላ አልነበረም፤ ሌሎቹ በሙሉ በጦርነት ድል ሆነው የተያዙ ናቸው። 20እነዚህም ሁሉ ከእስራኤላውያን ጋር ጦርነት እንዲገጥሙ እግዚአብሔር ልባቸውን እልኸኛ አድርጎ አነሣሣቸው። ስለዚህም በአጠቃላይ እንዲደመሰሱ ተፈርዶባቸው ያለ ምሕረት ተገደሉ፤ እግዚአብሔርም አስቀድሞ ለሙሴ የሰጠው ትእዛዝ ይኸው ነበር። #ዘዳ. 7፥16።
21በዚህን ጊዜ ዘምቶ ረጃጅሞች የሆኑትን የዐናቅን ዘሮች ደመሰሰ፤ እነርሱም በኮረብታማው አገር በኬብሮን፥ በደቢር፥ በዐናብ፥ በይሁዳና በእስራኤል ኮረብታማ አገሮች የሚኖሩ ነበሩ። ኢያሱ እነዚህን ሕዝቦችና ከተሞቻቸውን ሁሉ ደመሰሰ። 22ከዐናቅ ዘሮች በእስራኤል ምድር የተረፈ አልነበረም፤ ነገር ግን ጥቂቶች ብቻ በጋዛ፥ በጋትና በአሽዶድ ይኖሩ ነበር።
23እግዚአብሔር ሙሴን ባዘዘው መሠረት ኢያሱ ምድሩን ሁሉ በእጁ አደረገ፤ ለእያንዳንዱ ነገድ አንዳንድ ድርሻ ርስት አድርጎ በመስጠት ለእስራኤላውያን በሙሉ አከፋፈለ።
ስለዚህም ምድሪቱ ከጦርነት ዐረፈች።
Currently Selected:
መጽሐፈ ኢያሱ 11: አማ05
Highlight
Share
Copy
Want to have your highlights saved across all your devices? Sign up or sign in
© The Bible Society of Ethiopia, 2005
© የኢትዮጵያ መጽሐፍ ቅዱስ ማኅበር፥ 1997