YouVersion Logo
Search Icon

የዮሐንስ ወንጌል 4

4
ኢየሱስና አንዲት ሳምራዊት ሴት
1በዚያን ጊዜ ኢየሱስ ከዮሐንስ ይበልጥ ብዙ ሰዎችን ደቀ መዛሙርት እንደሚያደርግና እንደሚያጠምቅ ፈሪሳውያን ሰሙ፤ 2ሆኖም ያጠምቁ የነበሩት የእርሱ ደቀ መዛሙርት እንጂ እርሱ ራሱ አያጠምቅም ነበር። 3ስለ እርሱ የተባለውን ፈሪሳውያን እንደ ሰሙ ባወቀ ጊዜ ኢየሱስ የይሁዳን ምድር ትቶ ወደ ገሊላ ተመልሶ ሄደ። 4ወደዚያም ሲሄድ በሰማርያ በኩል ማለፍ ነበረበት።
5ስለዚህ ያዕቆብ ለልጁ ለዮሴፍ በሰጠው ቦታ አጠገብ ወደምትገኝ፥ ሲካር ተብላ ወደምትጠራ የሰማርያ ከተማ መጣ። #ዘፍ. 33፥19፤ ኢያሱ 24፥32። 6በዚያም የያዕቆብ የውሃ ጒድጓድ ነበረ፤ ኢየሱስ መንገድ ከመሄድ የተነሣ ስለ ደከመው በጒድጓዱ አጠገብ ተቀመጠ፤ ጊዜውም ወደ ስድስት ሰዓት ገደማ ነበረ።
7በዚያን ጊዜ አንዲት የሰማርያ አገር ሴት ውሃ ልትቀዳ ወደ ጒድጓዱ መጣች፤ ኢየሱስም “ውሃ አጠጪኝ!” አላት። 8በዚያን ወቅት ደቀ መዛሙርቱ ምግብ ሊገዙ ወደ ከተማ ሄደው ነበር። 9ይህችም ሳምራዊት ሴት ኢየሱስን፦ “አንተ ከአይሁድ ወገን ሆነህ እንዴት እኔን ሳምራዊቷን ‘ውሃ አጠጪኝ!’ ብለህ ትጠይቀኛለህ?” አለችው፤ ይህን ማለትዋ፥ አይሁድ ከሳምራውያን ጋር ስምምነት ስላልነበራቸው ነው። #ዕዝ. 4፥1-5፤ ነህ. 4፥12።
10ኢየሱስም “የእግዚአብሔርን ስጦታና ‘ውሃ አጠጪኝ!’ የሚልሽ ማን እንደ ሆነ ብታውቂው ኖሮ፥ እርሱን መለመን የሚገባሽ አንቺ ነበርሽ፤ እርሱም የሕይወትን ውሃ ይሰጥሽ ነበር” አላት።
11እርስዋም እንዲህ ስትል መለሰች፤ “ጌታ ሆይ! አንተ መቅጃ የለህም፤ ጒድጓዱም ጥልቅ ነው፤ ታዲያ፥ የሕይወት ውሃ ከየት ታገኛለህ? 12አንተ ይህን ጒድጓድ ከሰጠን ከአባታችን ከያዕቆብ ትበልጣለህን? እርሱና ልጆቹ፥ ከብቶቹም ከዚህ ጒድጓድ ጠጥተዋል።”
13ኢየሱስ እንዲህ ሲል መለሰላት፤ “ከዚህ ውሃ የሚጠጣ ሁሉ እንደገና ይጠማዋል፤ 14እኔ ከምሰጠው ውሃ የሚጠጣ ለዘለዓለም ከቶ አይጠማም፤ እኔ የምሰጠው ውሃ፥ ለሚጠጣው ሰው ለዘለዓለም ሕይወት የሚፈልቅ የውሃ ምንጭ ይሆናል።”
15ሴትዮዋም “ጌታ ሆይ! ከእንግዲህ ወዲህ ውሃ እንዳይጠማኝና ወደዚህም ለመቅዳት እንዳልመጣ እባክህ እንዲህ ዐይነቱን ውሃ ስጠኝ!” አለችው።
16ኢየሱስም “ሂጂና ባልሽን ጠርተሽ ተመለሺ” አላት።
17ሴትዮዋም “ባል የለኝም” ስትል መለሰች፤
በዚህ ጊዜ ኢየሱስ እንዲህ አላት፦ “ባል የለኝም ማለትሽ ልክ ነው፤ 18አምስት ባሎች ነበሩሽ፤ አሁንም ከአንቺ ጋር ያለው ሰው ባልሽ አይደለም፤ ስለዚህ እውነቱን ተናግረሻል።”
19ሴትዮዋም እንዲህ አለችው፤ “ጌታ ሆይ! አንተ ነቢይ እንደ ሆንክ አሁን ዐወቅሁ፤ 20አባቶቻችን በዚህ ተራራ ላይ ሰገዱ፤ እናንተ ግን ‘ሰዎች ሊሰግዱ የሚገባቸው በኢየሩሳሌም ነው’ ትላላችሁ።”
21ኢየሱስም እንዲህ አላት፦ “አንቺ ሴት፥ በዚህ ተራራ ላይ ወይም በኢየሩሳሌም ለአብ የማትሰግዱበት ጊዜ እንደሚመጣ እመኚኝ፤ 22እናንተ ለማታውቁት አምላክ ትሰግዳላችሁ፤ እኛ ግን መዳን የሚመጣው ከአይሁድ ስለ ሆነ ለምናውቀው አምላክ እንሰግዳለን። 23ነገር ግን በእውነት የሚሰግዱ፥ ለአብ በመንፈስና በእውነት የሚሰግዱበት ጊዜ ይመጣል፤ እንዲያውም አሁን መጥቶአል፤ አብም የሚፈልገው በዚህ መንገድ የሚሰግዱለትን ነው። 24እግዚአብሔር መንፈስ ነው፤ የሚሰግዱለትም በመንፈስና በእውነት ሊሰግዱለት ይገባቸዋል።”
25ሴትዮዋም “ክርስቶስ የሚባል መሲሕ እንደሚመጣ ዐውቃለሁ፤ እርሱ ሲመጣ ሁሉን ነገር ይነግረናል” አለችው።
26ኢየሱስም “እነሆ! አሁን የማነጋግርሽ እኔ እርሱ ነኝ” አላት።
27በዚህ ጊዜ ደቀ መዛሙርቱ ከሄዱበት ተመልሰው መጡ፤ ኢየሱስ ከሴት ጋር በመነጋገሩ ተገረሙ፤ ይሁን እንጂ “ምን ትፈልጋለህ? ወይም ከእርስዋ ጋር ለምን ትነጋገራለህ?” ብሎ የጠየቀው ማንም አልነበረም።
28ከዚህ በኋላ ሴትዮዋ እንስራዋን ትታ ወደ ከተማ ሄደችና ለሰዎቹ እንዲህ አለች፦ 29“የሠራሁትን ሁሉ የነገረኝን ሰው ኑ እዩ! ምናልባት እርሱ መሲሕ ይሆንን?” 30ሰዎቹም ከከተማ ወጥተው ወደ ኢየሱስ ሄዱ።
31በዚህ ጊዜ ደቀ መዛሙርቱ ኢየሱስን፦ “መምህር ሆይ! አንዳች ምግብ ብላ” ሲሉ ለመኑት።
32እርሱ ግን፥ “እናንተ የማታውቁት እኔ የምበላው ምግብ አለኝ” አላቸው።
33ስለዚህ ደቀ መዛሙርቱ፥ “አንዳች ሰው ምግብ አምጥቶለት ይሆን?” ተባባሉ። 34ኢየሱስም እንዲህ አላቸው፦ “የእኔ ምግብ የላከኝን ፈቃድ ማድረግና ሥራውንም መፈጸም ነው። 35እናንተ ‘ገና አራት ወር ቀርቶታል፤ ከዚያም በኋላ መከር ይሆናል’ ትሉ የለምን? እኔ ግን ‘ቀና በሉና እርሻዎቹ ለመከር እንደ ደረሱ ተመልከቱ’ እላችኋለሁ። 36የሚያጭድ ደመወዙን ይቀበላል፤ ለዘለዓለም ሕይወት የሚሆን ፍሬም ይሰበስባል፤ ስለዚህ የሚዘራውም፥ የሚያጭደውም አብረው ይደሰታሉ። 37በዚህም ምክንያት ‘አንዱ ይዘራል፥ ሌላው ያጭዳል’ የተባለው አባባል እውነት ነው። 38እኔም ያልደከማችሁበትን እንድታጭዱ ላክኋችሁ፤ ሌሎች በሥራ ደከሙ፤ እናንተ ግን በድካማቸው ፍሬ ተጠቀማችሁ።”
39ሴትዮዋ “የሠራሁትን ነገር ሁሉ ነገረኝ” ብላ በመሰከረችው መሠረት ከዚያ ከተማ ብዙዎቹ የሰማርያ ሰዎች አመኑ። 40ስለዚህ የሰማርያ አገር ሰዎች ወደ ኢየሱስ በመጡ ጊዜ ከእነርሱ ጋር እንዲቈይ ለመኑት፤ እርሱም ሁለት ቀን እዚያ ቈየ።
41በቃሉም ምክንያት ሌሎች ብዙ ሰዎችም በእርሱ አመኑ። 42ሴትዮዋንም “ከእንግዲህ ወዲህ እርሱን የምናምነው አንቺ በነገርሽን ቃል ብቻ ሳይሆን እኛ ራሳችን ስለ ሰማንና በእርግጥ እርሱ የዓለም አዳኝ እንደ ሆነ ስላወቅን ነው” አሉአት።
ኢየሱስ የሹሙን ልጅ እንደ ፈወሰ
43ኢየሱስ በሰማርያ ሁለት ቀን ከቈየ በኋላ ወደ ገሊላ ሄደ። 44እርሱ ራሱ “ነቢይ በገዛ አገሩ አይከበርም” ብሎ ተናግሮ ነበር። #ማቴ. 13፥57፤ ማር. 6፥4፤ ሉቃ. 4፥24። 45ነገር ግን ወደ ገሊላ በደረሰ ጊዜ የገሊላ ሰዎች በመልካም ሁኔታ ተቀበሉት፤ ይህም የሆነው ለፋሲካ በዓል ወደ ኢየሩሳሌም ሄደው በነበረበት ጊዜ እርሱ በዚያ ያደረገውን ሁሉ አይተው ስለ ነበር ነው። #ዮሐ. 2፥23።
46ከዚህ በኋላ ኢየሱስ ውሃውን የወይን ጠጅ ወደ ለወጠባት በገሊላ ምድር ወደምትገኘው ወደ ቃና ከተማ እንደገና ተመለሰ፤ በዚያን ጊዜ በቅፍርናሆም ልጁ የታመመበት አንድ የቤተ መንግሥት ሹም ነበረ። #ዮሐ. 2፥1-11። 47እርሱም ኢየሱስ ከይሁዳ ምድር ወደ ገሊላ መምጣቱን ሰምቶ ወደ እርሱ ሄደ፤ ወደ ቅፍርናሆም እንዲወርድና በጠና ታሞ ሊሞት የተቃረበውን ልጁን እንዲፈውስለት ኢየሱስን ለመነው። 48ኢየሱስም “እናንተ ተአምራትና ድንቅ ነገር ካላያችሁ በቀር ምንም አታምኑም!” አለው።
49ሹሙም “ጌታ ሆይ! ልጄ ከመሞቱ በፊት እባክህ ቶሎ ውረድ” አለው።
50ኢየሱስም “ወደ ቤትህ ሂድ! ልጅህ በሕይወት ይኖራል” አለው።
ሰውየውም ኢየሱስ የተናገረውን ቃል አምኖ ወደ ቤቱ ሄደ። 51ሲሄድም አገልጋዮቹ በመንገድ አገኙትና “ልጅህ ድኖአል” ብለው ነገሩት።
52እርሱም ልጁ በጎ የሆነበትን ሰዓት ጠየቃቸው። እነርሱም “ትናንትና በሰባት ሰዓት ላይ ትኲሳቱ ለቀቀው” አሉት። 53አባትየውም ኢየሱስ “ልጅህ በሕይወት ይኖራል” ያለው በዚያኑ ሰዓት እንደ ሆነ ዐወቀ፤ ስለዚህ ከዚያን ቀን ጀምሮ እርሱና ቤተ ሰቡ ሁሉ በኢየሱስ አመኑ።
54ይህ ተአምር ኢየሱስ ከይሁዳ ወደ ገሊላ መጥቶ ያደረገው ሁለተኛው ተአምር ነው።

Highlight

Share

Copy

None

Want to have your highlights saved across all your devices? Sign up or sign in