YouVersion Logo
Search Icon

የዮሐንስ ወንጌል 14

14
ወደ አብ የሚወስደው መንገድ ኢየሱስ መሆኑ
1ቀጥሎም ኢየሱስ እንዲህ አለ፦ “ልባችሁ አይጨነቅ፤ በእግዚአብሔር እመኑ፤ በእኔም እመኑ፤ 2በአባቴ ቤት ብዙ መኖሪያ አለ፤ አለበለዚያ ግን ‘የምትኖሩበትን ስፍራ ላዘጋጅላችሁ እሄዳለሁ’ ባልኳችሁ ነበር። 3ሄጄ ስፍራ ካዘጋጀሁላችሁ በኋላ እኔ ባለሁበት እንድትኖሩ እንደገና መጥቼ እወስዳችኋለሁ። 4እኔ የምሄድበትንም መንገድ ታውቃላችሁ።”
5ቶማስ “ጌታ ሆይ! ወዴት እንደምትሄድ አናውቅም፤ ታዲያ፥ መንገዱን እንዴት ማወቅ እንችላለን?” አለው። 6ኢየሱስም እንዲህ ሲል መለሰለት፦ “መንገድና እውነት ሕይወትም እኔ ነኝ፤ በእኔ በኩል ካልሆነ በቀር ማንም ወደ አብ የሚመጣ የለም። 7እኔን ዐውቃችሁኝ ቢሆን ኖሮ አባቴንም ባወቃችሁት ነበር፤ ከእንግዲህ ወዲህ ግን ታውቁታላችሁ፤ አይታችሁታልም።”
8ፊልጶስም “ጌታ ሆይ! አብን አሳየንና ይበቃናል” አለው።
9ኢየሱስም እንዲህ ሲል መለሰለት፦ “ፊልጶስ ሆይ! ይህን ያኽል ጊዜ ከእናንተ ጋር ስኖር አታውቀኝምን? እኔን ያየ አብን አየ፤ ታዲያ፥ አንተ ‘አብን አሳየን’ እንዴት ትላለህ? 10እኔ በአብ እንዳለሁ፥ አብም በእኔ እንዳለ አታምንምን? ለእናንተ የምናገረውን ቃል የምናገረው በራሴ ሥልጣን አይደለም፤ ነገር ግን ሥራውን ሁሉ የሚሠራው፥ በእኔ የሚኖረው አብ ነው። 11እኔ በአብ እንዳለሁ፥ አብም በእኔ እንዳለ እመኑ፤ አለበለዚያ በሥራዎቼ ምክንያት እመኑኝ። 12እውነት፥ እውነት እላችኋለሁ በእኔ የሚያምን እኔ የምሠራውን ሥራ ይሠራል፤ እንዲያውም ከዚህ የበለጠ ይሠራል፤ እኔ ወደ አብ እሄዳለሁ። 13አብ በወልድ ምክንያት እንዲከበር በስሜ የምትለምኑትን ሁሉ አደርግላችኋለሁ። 14ማንኛውንም ነገር በስሜ ብትለምኑ እኔ አደርገዋለሁ።”
ኢየሱስ ስለ መንፈስ ቅዱስ የሰጠው ተስፋ
15“የምትወዱኝ ከሆነ ትእዛዜን ጠብቁ፤ 16እኔ አብን እለምነዋለሁ፤ እርሱም ለዘለዓለም ከእናንተ ጋር የሚኖር ሌላ አጽናኝ ይሰጣችኋል። 17ይህም የእውነት መንፈስ ነው፤ ዓለም ስለማያየውና ስለማያውቀው ሊቀበለው አይችልም፤ እናንተ ግን፥ እርሱ ከእናንተ ጋር ስለ ሆነና በውስጣችሁም ስላለ ታውቁታላችሁ።
18“እናትና አባት እንደሌላቸው ልጆች ብቻችሁን አልተዋችሁም፤ ተመልሼ ወደ እናንተ እመጣለሁ። 19ከጥቂት ጊዜ በኋላ ዓለም አያየኝም፤ እናንተ ግን ታዩኛላችሁ፤ እኔ ሕያው ስለ ሆንኩ እናንተም በሕይወት ትኖራላችሁ፤ 20እኔ በአብ እንዳለሁ፥ እናንተም በእኔ እንዳላችሁ፥ እኔም በእናንተ እንዳለሁ በዚያን ቀን ታውቃላችሁ።
21“እኔን የሚወደኝ ትእዛዜን የሚቀበልና በሥራ ላይ የሚያውለው ነው፤ እኔንም የሚወደኝን አባቴ ይወደዋል፤ እኔም እወደዋለሁ፤ ራሴንም እገልጥለታለሁ።”
22አስቆሮታዊው ሳይሆን ሌላው ይሁዳ፥ “ጌታ ሆይ! ራስህን ለዓለም ሳይሆን ለእኛ የምትገልጠው እንዴት ነው?” አለው።
23ኢየሱስም እንዲህ ሲል መለሰለት፦ “የሚወደኝ ቃሌን ይጠብቃል፤ አባቴም ይወደዋል፤ እኛ ወደ እርሱ መጥተን ከእርሱ ጋር አብረን እንኖራለን። 24የማይወደኝ ቃሌን አይጠብቅም፤ ይህ የምትሰሙት ቃል የላከኝ የአብ ነው እንጂ የእኔ አይደለም።
25“አሁን ከእናንተም ጋር እያለሁ ይህን ነገር ነግሬአችኋለሁ፤ 26አብ በእኔ ስም የሚልከው አጽናኙ መንፈስ ቅዱስ ግን ሁሉን ነገር ያስተምራችኋል፤ እኔ የነገርኳችሁንም ሁሉ እንድታስታውሱ ያደርጋችኋል።
27“ሰላምን እተውላችኋለሁ፤ ሰላሜንም እሰጣችኋለሁ፤ እኔ የምሰጣችሁ ሰላም ዓለም እንደሚሰጠው ዐይነት አይደለም፤ ልባችሁ አይጨነቅ፤ ደግሞም አይፍራ። 28‘እኔ እሄዳለሁ፤ ተመልሼም ወደ እናንተ እመጣለሁ’ እንዳልኩ ሰምታችኋል፤ አባቴ ከእኔ ስለሚበልጥ ብትወዱኝስ ኖሮ ወደ አብ በመሄዴ ደስ ባላችሁ ነበር። 29ይህ በሚሆንበት ጊዜ እንድታምኑ፥ ከመሆኑ በፊት አስቀድሜ ነግሬአችኋለሁ። 30የዚህ ዓለም ገዢ ሰይጣን መምጣቱ ስለ ሆነ ከእንግዲህ ወዲህ ከእናንተ ጋር ብዙ አልነጋገርም። እርሱ በእኔ ላይ ምንም ኀይል የለውም፤ 31ነገር ግን እኔ አብን እንደምወድ ዓለም ያውቅ ዘንድ አብ ያዘዘኝን ሁሉ እፈጽማለሁ፤ ተነሡ ከዚህ እንሂድ።

Highlight

Share

Copy

None

Want to have your highlights saved across all your devices? Sign up or sign in