YouVersion Logo
Search Icon

የዮሐንስ ወንጌል 13

13
ኢየሱስ የደቀ መዛሙርቱን እግር ማጠቡ
1እነሆ፥ ጊዜው ከአይሁድ ፋሲካ በዓል በፊት ነበር፤ ኢየሱስ ይህን ዓለም ትቶ ወደ አብ የሚሄድበት ሰዓት መድረሱን ዐወቀ። በዚህ በዓለም ያሉትን የራሱን ወገኖች ወዶአቸው ነበር፤ እስከ መጨረሻም ወደዳቸው።
2ኢየሱስና ደቀ መዛሙርቱ ራት ይበሉ ነበር፤ የስምዖን ልጅ አስቆሮታዊው ይሁዳ ግን ኢየሱስን አሳልፎ እንዲሰጥ ዲያብሎስ በልቡ ክፉ ሐሳብ አሳደረበት። 3አብ ሥልጣንን ሁሉ እንደ ሰጠውና ከእግዚአብሔር ወጥቶ እንደመጣ፥ ወደ እግዚአብሔርም እንደሚሄድ ኢየሱስ ያውቅ ነበር። 4ስለዚህ ከማእድ ተነሣና ልብሱን አስቀመጠ፤ ማበሻ ጨርቅም አንሥቶ በወገቡ ታጠቀ። 5ከዚህ በኋላ በመታጠቢያ ዕቃ ውሃ አድርጎ የደቀ መዛሙርቱን እግር ማጠብ ጀመረ፤ በታጠቀውም ማበሻ ጨርቅ እግራቸውን አበሰ። 6ኢየሱስ ወደ ስምዖን ጴጥሮስ በመጣ ጊዜ ስምዖን ጴጥሮስ፥ “ጌታ ሆይ! አንተ የእኔን እግር ታጥባለህን?” አለው። 7ኢየሱስም “እኔ የማደርገውን አንተ አሁን አታውቅም፤ በኋላ ግን ታስተውላለህ” አለው። 8ጴጥሮስም “አንተ የእኔን እግር ከቶ አታጥብም!” አለው። ኢየሱስም “እኔ እግርህን ካላጠብኩህ ከእኔ ድርሻ የለህም” አለው። 9ስምዖን ጴጥሮስም “ጌታ ሆይ! እንዲህስ ከሆነ እግሬን ብቻ ሳይሆን እጄንም፥ ራሴንም እጠበኝ!” አለው። 10ኢየሱስም “ሰውነቱን የታጠበ ሁለመናውም ንጹሕ በመሆኑ እግሩን ከመታጠብ በቀር ሌላ አያስፈልገውም፤ እናንተም ንጹሖች ናችሁ፤ ነገር ግን ሁላችሁም ንጹሖች አይደላችሁም” አለው። 11ኢየሱስ “ሁላችሁም ንጹሖች አይደላችሁም” ያለው አሳልፎ የሚሰጠው ማን እንደ ሆነ ያውቅ ስለ ነበር ነው።
12እግራቸውን ካጠበ በኋላ ልብሱን ለበሰና ወደ ቦታው ተመልሶ ተቀመጠ፤ እንዲህም አላቸው፦ “ምን እንዳደረግሁላችሁ አስተዋላችሁን? #ሉቃ. 22፥27። 13እናንተ ‘መምህርና ጌታ’ ትሉኛላችሁ፤ እኔ መምህርና ጌታ ስለ ሆንኩ ያላችሁት ትክክል ነው። 14እንግዲህ እኔ ጌታችሁና መምህራችሁ ስሆን እግራችሁን ካጠብኩ እናንተም እርስ በርሳችሁ እግራችሁን መተጣጠብ ይገባችኋል። 15እኔ ለእናንተ እንዳደረግሁት እናንተም እንድታደርጉ ምሳሌ ሰጥቻችኋለሁ። 16እውነት፥ እውነት እላችኋለሁ፤ አገልጋይ ከጌታው አይበልጥም፤ መልእክተኛም ከላኪው አይበልጥም። #ማቴ. 10፥24፤ ሉቃ. 6፥40፤ ዮሐ. 15፥20። 17ይህን ነገር ብታውቁና በሥራ ላይ ብታውሉት የተባረካችሁ ናችሁ። 18ይህን የምናገረው ስለ ሁላችሁም አይደለም፤ እኔ የመረጥኳችሁን ዐውቃለሁ፤ ነገር ግን ‘እንጀራዬን የበላ በእኔ ላይ በጠላትነት ተነሣብኝ’ የሚለው የቅዱስ መጽሐፍ ቃል መፈጸም አለበት። #መዝ. 41፥9። 19ይህ ከመሆኑ በፊት አሁን አስቀድሜ የምነግራችሁ፤ ከተፈጸመ በኋላ፥ በእኔ ማንነት እንድታምኑ ነው። 20እውነት፥ እውነት እላችኋለሁ፤ እኔ የምልከውን የሚቀበል እኔን ይቀበላል፤ እኔንም የሚቀበል የላከኝን ይቀበላል።” #ማቴ. 10፥40፤ ማር. 9፥37፤ ሉቃ. 9፥48፤ 10፥16።
ኢየሱስ አሳልፎ የሚሰጠው ማን እንደ ሆነ አስቀድሞ መናገሩ
(ማቴ. 26፥20-25ማር. 14፥17-21ሉቃ. 22፥21-23)
21ኢየሱስ ይህን ካለ በኋላ በመንፈሱ ተጨነቀና “እውነት፥ እውነት እላችኋለሁ፤ ከእናንተ አንዱ አሳልፎ ይሰጠኛል” ሲል ገልጦ ተናገረ።
22ደቀ መዛሙርቱ ይህን ስለ ማን እንደ ተናገረ ባለማወቃቸው እርስ በእርሳቸው ተያዩ። 23ኢየሱስ ይወደው የነበረው፥ ከደቀ መዛሙርቱ አንዱ በኢየሱስ ጐን ተቀምጦ ነበር። 24ስምዖን ጴጥሮስ እርሱን ጠቀሰና “ስለ ማን እንደ ተናገረ እስቲ ጠይቅ” አለው።
25ስለዚህ እርሱ አንገቱን ወደ ኢየሱስ አስጠጋና “ጌታ ሆይ! አሳልፎ የሚሰጥህ ማን ነው?” ሲል ጠየቀው።
26ኢየሱስም “እርሱ ይህን እንጀራ በወጥ አጥቅሼ የማጐርሰው ነው” አለ። ይህንንም ብሎ እንጀራ በወጥ አጠቀሰና የአስቆሮታዊው ስምዖን ልጅ ለሆነው ለይሁዳ አጐረሰው። 27ይሁዳ ጉርሻውን ከተቀበለ በኋላ ወዲያውኑ ሰይጣን ዐደረበት፤ ኢየሱስም ይሁዳን፥ “ለማድረግ ያሰብከውን ቶሎ ብለህ አድርግ!” አለው። 28ኢየሱስ ስለምን ይህን እንዳለ በማእድ ከተቀመጡት ማንም የገባው የለም። 29ይሁዳ ገንዘብ ያዥ ስለ ነበረ ከደቀ መዛሙርቱ አንዳንዶቹ ኢየሱስ “ለበዓሉ የሚያስፈልገንን ግዛ ወይም ለድኾች ምጽዋት ስጥ” ያለው መስሎአቸው ነበር።
30ይሁዳም ጉርሻውን እንደ ተቀበለ ወዲያውኑ ወጥቶ ሄደ፤ ጊዜውም ሌሊት ነበረ።
አዲሱ ትእዛዝ
31ይሁዳ ወጥቶ ከሄደ በኋላ ኢየሱስ እንዲህ አለ፦ “አሁን የሰው ልጅ ከብሮአል፤ በእርሱም አማካይነት እግዚአብሔር ከብሮአል፤ 32እግዚአብሔር በእርሱ አማካይነት ከከበረ እግዚአብሔርም እርሱን ያከብረዋል፤ ሳይዘገይም ያከብረዋል። 33ልጆቼ ሆይ፥ ከእናንተ ጋር ብዙ ጊዜ አልቆይም፤ እናንተም ትፈልጉኛላችሁ፤ ለአይሁድ ባለሥልጣኖች ‘እኔ ወደምሄድበት እናንተ ልትመጡ አትችሉም’ እንዳልኳቸው፥ አሁንም ለእናንተ እንዲሁ እላችኋለሁ። #ዮሐ. 7፥34። 34እርስ በርሳችሁ እንድትዋደዱ አዲስ ትእዛዝ እሰጣችኋለሁ፤ እኔ እንደ ወደድኳችሁ እናንተም እርስ በእርሳችሁ ተዋደዱ። #ዮሐ. 15፥12፤17፤ 1ዮሐ. 3፥23፤ 2ዮሐ. 5። 35እርስ በእርሳችሁ ከተዋደዳችሁ የእኔ ደቀ መዛሙርት እንደ ሆናችሁ ሰው ሁሉ ያውቃል።”
ጴጥሮስ እንደሚክደው ኢየሱስ አስቀድሞ መናገሩ
(ማቴ. 26፥31-35ማር. 14፥27-31ሉቃ. 22፥31-34)
36ከዚህ በኋላ ስምዖን ጴጥሮስ ኢየሱስን፥ “ጌታ ሆይ! ወዴት ነው የምትሄደው?” ሲል ጠየቀው።
ኢየሱስም “እኔ ወደምሄድበት አሁን ልትከተለኝ አትችልም፤ በኋላ ግን ትከተለኛለህ” ሲል መለሰለት።
37ጴጥሮስም “ጌታ ሆይ! ስለምን አሁን ልከተልህ አልችልም? እኔ ሕይወቴን እንኳ ስለ አንተ አሳልፌ እሰጣለሁ” አለው።
38ኢየሱስም “አንተ ሕይወትህን ስለ እኔ አሳልፈህ ትሰጣለህን? እውነት፥ እውነት እልሃለሁ፤ ዛሬ ዶሮ ከመጮሁ በፊት ሦስት ጊዜ ትክደኛለህ” ሲል መለሰ።

Highlight

Share

Copy

None

Want to have your highlights saved across all your devices? Sign up or sign in