ትንቢተ ኤርምያስ 18
18
ኤርምያስ በሸክላ ሠሪው ቤት
1ከእግዚአብሔር ወደ ኤርምያስ የመጣው ቃል ይህ ነው፦ 2“ተነሥተህ ወደ ሸክላ ሠሪው ቤት ውረድ፤ እዚያም መልእክቴን እነግርሃለሁ።” 3እኔም እዚያ ሄጄ ሸክላ ሠሪው በመንኰራኲሩ ላይ ሲሠራ አየሁት፤ 4የሸክላውም ዕቃ በእጁ ላይ በሚበላሽበት ጊዜ እንደገና ለውሶ በሚፈልገው ዐይነት ሌላ ዕቃ አድርጎ ይሠራው ነበር።
5በዚያን ጊዜ እግዚአብሔር እንዲህ አለኝ፦ 6“የእስራኤል ሕዝብ ሆይ! ሸክላ ሠሪው ሸክላውን በፈለገው ዐይነት እንደሚሠራው፥ እኔስ በእናንተ ላይ የፈለግኹትን ማድረግ አልችልምን? የሸክላው ጭቃ በሸክላ ሠሪው እጅ እንደሚገኝ እናንተም፥ በእኔ እጅ ናችሁ። 7እኔ አንድን ሕዝብ ወይም መንግሥት፥ ‘እነቅላለሁ ወይም ሰባብሬ አጠፋለሁ’ ብዬ በተናገርኩ ጊዜ፥ 8ያ ሕዝብ ተጸጽቶ ከክፋቱ የሚመለስ ከሆነ፥ አመጣበታለሁ ብዬ ያቀድኩትን ክፉ ነገር አላደርግበትም። 9በሌላ በኩል ደግሞ እኔ አንድን ሕዝብ ወይም መንግሥት ‘እተክላለሁ ወይም እገነባለሁ’ በምልበት ጊዜ፥ 10ያ ሕዝብ ለእኔ የማይታዘዝና ክፋትንም የሚያደርግ ሆኖ ከተገኘ ላደርግለት ያቀድኩትን መልካም ነገር አላደርግለትም። 11ስለዚህም እኔ እነርሱን ለመቅጣት በእነርሱ ላይ ክፉ ነገር የማደርግ መሆኔን ለይሁዳና ለኢየሩሳሌም ሕዝብ ንገራቸው፤ ኃጢአት መሥራትን እንዲተዉና አካሄዳቸውንና አሠራራቸውን ሁሉ እንዲለውጡ ምከራቸው። 12እነርሱም ‘ስለምን ብለን ይህን እናደርጋለን? እንዲያውም ያቀድነውን ሁሉ በመፈጸም ከምንጊዜውም ይልቅ እልኸኞችና ዐመፀኞች መሆን እንችላለን’ ብለው ይመልሱልሃል።”
የእስራኤል ሕዝብ እግዚአብሔርን መተዉ
13ስለዚህ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦
“ይህን የመሰለ ነገር በሕዝቦች መካከል ተሰምቶ እንደ ሆነ ጠይቁ፤ የተለዩ የእስራኤል ሕዝብ በጣም አጸያፊ የሆነ ነገር አድርገዋል።
14የሊባኖስ ጭንጫማ ተራራዎች በበረዶ ያልተሸፈኑበት ጊዜ አለን?
ከየተራራው ላይ የሚወርዱትስ ቀዝቃዛ ምንጮች ደርቀው ያውቃሉን?
15ሕዝቤ ግን እኔን ረስተዋል፤
ከንቱ ለሆኑ ጣዖቶችም ዕጣን ያጥናሉ፤
እነርሱም ባልታወቀ መንገድ እንዲሄዱ አድርገዋቸዋል፤
ተሰናክለውም የቀድሞውን መንገድ ትተዋል።
16ምድራቸው የዘለዓለም መሳለቂያ፥ ባድማ ትሆናለች፤
በአጠገብዋ የሚያልፉ ሁሉ በማፌዝ ራሳቸውን ይነቀንቃሉ፤
17ትቢያ በምሥራቅ ነፋስ እንደሚበተን፥
ሕዝቤን በጠላቶቻቸው ፊት እበትናቸዋለሁ።
ፊቴን ከእነርሱ መልሼ ጀርባዬን እሰጣቸዋለሁ።
ጥፋት በሚመጣባቸውም ጊዜ ፈጽሞ አልረዳቸውም።”
በኤርምያስ ላይ የታቀደ ሤራ
18ከሕዝቡ መካከል አንዳንድ ሰዎች፦ “ኑ በኤርምያስ ላይ ዕቅድ እናውጣ! የእግዚአብሔርን ሕግ የሚያስተምሩ ካህናት፥ ምክር የሚሰጡ ጥበበኞች፥ የእግዚአብሔርን መልእክት የሚናገሩ ነቢያት ሁልጊዜ እናገኛለን፤ ስለዚህ ከእንግዲህ ወዲያ ኤርምያስን ከማድመጥ ይልቅ በንግግሩ አጥምደን በወንጀል እንክሰሰው ተባባሉ።”
19ስለዚህ እንዲህ በማለት ጸለይኩ “እግዚአብሔር ሆይ! ልመናዬን ስማ፤ ጠላቶቼም በእኔ ላይ የሚናገሩትን ክፉ ነገር አድምጥ። 20ታዲያ የደግ ሥራ ዋጋው ክፉ ነገር ማድረግ ነውን? አንተ በእነርሱ ላይ እንዳትቈጣ እኔ በፊትህ ቆሜ ስለ እነርሱ እንደማለድኩህ አስብ፤ እነርሱ ግን እነሆ እኔ የምወድቅበትን ጒድጓድ ቈፈሩ። 21አምላክ ሆይ! አሁን ግን ልጆቻቸው በራብ እንዲያልቁ፥ እነርሱም በጦርነት እንዲወድቁ አድርግ፤ ሴቶቻቸው ያለ ባልና ያለ ልጅ ይቅሩ፤ ወንዶቻቸው በበሽታ ወጣቶቻቸውም በጦርነት ይደምሰሱ። 22ወራሪዎችን በድንገት ላክባቸው፤ ከቤታቸው ጩኸት ይሰማ፤ እነርሱ እኔ የምወድቅበትን ጒድጓድ ቆፍረዋል፤ የምያዝበትንም ወጥመድ አዘጋጅተዋል። 23አምላክ ሆይ! እነርሱ እኔን ለመግደል የሸረቡትን ሤራ ታውቀዋለህ፤ ስለዚህ ክፋታቸውን ይቅር አትበል፤ ኃጢአታቸውም እንዲሰረይላቸው አታድርግ፤ በፊትህ እንዲሸነፉና በብርቱ ቊጣህ እንዲወድቁ አድርግ።”
Currently Selected:
ትንቢተ ኤርምያስ 18: አማ05
Highlight
Share
Copy
Want to have your highlights saved across all your devices? Sign up or sign in
© The Bible Society of Ethiopia, 2005
© የኢትዮጵያ መጽሐፍ ቅዱስ ማኅበር፥ 1997