YouVersion Logo
Search Icon

ትንቢተ ኤርምያስ 10

10
ባዕድ አምልኮና እውነተኛ አምልኮ
1የእስራኤል ሕዝብ ሆይ! እነሆ እግዚአብሔር የሚነግራችሁን ቃል ስሙ፤ 2እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦
“የአሕዛብን አካሄድ አትከተሉ፤
መቼም አሕዛብ ያልተለመደ አዲስ ነገር በሰማይ ባዩ ጊዜ
በፍርሃት መንቀጥቀጥ ልማዳቸው ነው፤
እናንተ ግን በዚህ አትሸበሩ።
3የአሕዛብ ልማዳዊ እምነት ከንቱ ነው፤
ዛፍ ከደን ይቈረጣል፤
አናጢ በመሮ ቅርጽ ያወጣለታል፤
4በብርና በወርቅ ያስጌጡታል፤
እንዳይወድቅም በምስማር ያጠብቁታል።
5እንደነዚህ ያሉት ምስሎች በዱባ ተክል ውስጥ
ለወፍ ማስፈራሪያ እንደሚተከሉ ነገሮች ናቸው፤
መናገር አይችሉም፤
መራመድ ስለማይችሉ ሰዎች ይሸከሙአቸዋል፤
ጒዳት ማድረስም ሆነ ጥቅም ማስገኘት ስለማይችሉ፥
ፈጽሞ አትፍሩአቸው።”
6እግዚአብሔር ሆይ! አንተን የሚመስል ማንም የለም፤
አንተ ኀያል ነህ፤
ስምህም ታላቅና አስፈሪ ነው።
7የመንግሥታት ሁሉ ንጉሥ ስለ ሆንክ አንተን የማይፈራ ማን ነው?
በአሕዛብ ጠቢባንም ሆነ በንጉሦቻቸው መካከል
አንተን የሚመስል ስለሌለ ክብር ይገባሃል። #ራዕ. 15፥4።
8ሁሉም ሞኞችና አላዋቂዎች ሆነው ነው እንጂ
ከእንጨት ከተሠሩ ምስሎች ከቶ ምን ትምህርት ማግኘት ይችላሉ?
9ምስሎቻቸው ከተርሴስ በመጣ ጥሬ ብርና
ከኡፋዝ በተገኘ ወርቅ ተለብጠዋል፤
በብልኀተኞችም ሥራ አጊጠዋል፤
ጥበበኞች ሸማኔዎች በሠሩአቸውም
የወይን ጠጅና ሐምራዊ ልብስ ተሸፍነዋል።
10እግዚአብሔር ሆይ! አንተ ግን እውነተኛ አምላክ ነህ፤
አንተ ሕያው አምላክ፥ ዘለዓለማዊ ንጉሥ ነህ፤
አንተ በምትቈጣበት ጊዜ ዓለም ይናወጣል፤
የአሕዛብ መንግሥታትም የአንተን ቊጣ ችለው አይቆሙም።
11“ጣዖቶች ሰማይንና ምድርን ያልፈጠሩ መሆናቸውንና
አንተ እግዚአብሔር ጣዖቶችን ሁሉ እንደምትደመስስ
ንገራቸው” አልከኝ።
ለእግዚአብሔር የቀረበ ምስጋና
12እግዚአብሔር በኀይሉ ምድርን ሠራ፤
በጥበቡም ዓለምን ፈጠረ፤
በማስተዋሉም ሰማያትን ዘረጋ፤
13በእርሱ ትእዛዝ ከሰማይ በላይ ያሉ ውሃዎች የመናወጥ ድምፅ ያሰማሉ፤
እርሱ ደመናዎችን ከምድር ዳርቻ ያመጣል፤
በዝናብ ጊዜም መብረቅ እንዲበርቅ ያደርጋል፤
ነፋስንም ከማከማቻው ይልካል።
14ሁሉም ሞኞችና አላዋቂዎች ሆኑ፤
የሠሩአቸው ምስሎች ሐሰተኞች ስለ ሆኑና ሕይወትም ስለሌላቸው
አንጥረኛው በሠራቸው ጣዖቶች አፍሮባቸዋል።
15እነዚህ አማልክት ዋጋ ቢሶችና የፌዝ ዕቃዎች ናቸው፤
እግዚአብሔር እነርሱን ለመቅጣት በሚገለጥበትም ጊዜ ይደመሰሳሉ።
16የያዕቆብ አምላክ ግን እንደ እነርሱ አይደለም፤
እርሱ የሁሉ ነገር ፈጣሪ ነው።
እስራኤልንም የራሱ ሕዝብ እንዲሆን መርጦታል፤
ስሙም የሠራዊት ጌታ እግዚአብሔር ነው።
ሊመጣ የተቃረበ ስደት
17እናንተ በተከበበችው በኢየሩሳሌም ከተማ የምትኖሩ ሕዝብ ሆይ!
ከዚያ ለመውጣት ንብረታችሁን በፍጥነት ሰብስቡ!
18እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦
“በዚህ ጊዜ በዚህች አገር
የሚኖሩትን ሰዎች አስወጣለሁ፤
እነርሱን አስጨንቄ እንዲማረኩ አደርጋለሁ።”
19የኢየሩሳሌም ሕዝብ እየጮሁ እንዲህ ይላሉ፥
“በብርቱ ስለ ቈሰልን ወዮልን!
ቊስላችንም የማይፈወስ ነው፤
እኛ ግን ይህን ሁሉ መከራ መታገሥ የምንችል መስሎን ነበር።
20ድንኳኖቻችን ፈራረሱ፤
መወጠሪያ ገመዶችም ተቈራረጡ፤
ልጆቻችን በሙሉ ተሰደው ስለ ሄዱ፥
ድንኳኖቻችንን መልሶ የሚተክልልንና
መጋረጃዎቻችንን የሚሰቅልልን አንድ እንኳ አልቀረም።”
21እኔም እንዲህ ስል መለስኩ፥
“መሪዎቻችን ሞኞች ከመሆናቸው የተነሣ፥
የእግዚአብሔርን ርዳታ አልጠየቁም፤
ውድቀት የደረሰባቸውና ሕዝባችንም ተበትኖ የቀረው ስለዚህ ነው።
22አድምጡ አዲስ ዜና መጥቶአል!
የሰሜን መንግሥት የይሁዳን ከተሞች
ወደ ምድረበዳነት ለውጦ የቀበሮዎች መመሰጊያ ለማድረግ
በመራወጥ ላይ ይገኛል።”
23እግዚአብሔር ሆይ! ሰው በራሱ ሕይወት እንደማያዝበትና
አካሄዱንም በራሱ ሥልጣን መቈጣጠር እንደማይችል ዐውቃለሁ።
24እግዚአብሔር ሆይ፥ አንተ ትክክለኛ ፈራጅ እንደ መሆንህ ገሥጸን፤
ነገር ግን ፈጽመን እንዳንጠፋ በምትቈጣበት ጊዜ አይሁን።
25ቊጣህን አንተን በማያውቁና ስምህን በማይጠሩ ሕዝቦች ላይ አፍስሰው፤
እነርሱ ሕዝብህን ፈጅተዋል፤
ሁላችንንም ፈጽመው በመደምሰስ፥ አገራችንን አውድመዋል።

Highlight

Share

Copy

None

Want to have your highlights saved across all your devices? Sign up or sign in