ትንቢተ ኢሳይያስ 39
39
ከባቢሎን የመጡ መልእክተኞች
(2ነገ. 20፥12-19)
1በዚያን ዘመን የባቢሎን ንጉሥ የባላዳን ልጅ መሮዳክ ባላዳን ንጉሥ ሕዝቅያስ ታሞ መዳኑን ሰማ፤ ስለዚህም ከገጸ በረከት ጋር ደብዳቤ ላከለት። 2ሕዝቅያስም መልእክተኞቹን በደስታ ተቀበላቸው፤ በቤተ መንግሥቱም የዕቃ ግምጃ ቤት ያለውን ሀብት በሙሉ ብሩንና ወርቁን፥ ቅመማ ቅመሙንና፥ ሽቶውን፥ የጦር መሣሪያውንና በዕቃ ቤት ያለውን ንብረት ሁሉ አሳያቸው፤ በቤተ መንግሥቱ ግምጃ ቤትም ሆነ በመንግሥቱ በማንኛውም ስፍራ ካለው ሀብት ሁሉ ሕዝቅያስ ያላሳያቸው ምንም ነገር አልነበረም። 3በዚያም ጊዜ ነቢዩ ኢሳይያስ ወደ ንጉሥ ሕዝቅያስ ሄዶ “እነዚህ ሰዎች ከወዴት መጡ? ምንስ ነገሩህ?” ብሎ ጠየቀው።
ሕዝቅያስም “እነርሱ የመጡት ባቢሎን ከሚባል ከሩቅ አገር ነው” ሲል መለሰለት።
4ኢሳይያስም “በቤተ መንግሥቱ ምን አዩ?” ሲል ጠየቀው።
ሕዝቅያስም “ሁሉን ነገር አይተዋል፤ በግምጃ ቤት ካለው ሀብት ሁሉ ለእነርሱ ያላሳየኋቸው ምንም ነገር የለም” አለው።
5ኢሳይያስም ንጉሡን እንዲህ አለው፦ “የሠራዊት አምላክ እንዲህ ይላል፦ 6የቀድሞ አባቶች እስከዚህች ቀን ያከማቹት በቤተ መንግሥትህ ያለው ሀብት ሁሉ ተጠራርጎ ወደ ባቢሎን የሚወሰድበት ጊዜ ይመጣል፤ ምንም ነገር አይቀርልህም። 7ከአንተም ዘር አንዳንዶቹ ወደ ባቢሎን ተማርከው በመሄድ በባቢሎን ቤተ መንግሥት ጃንደረባ ሆነው እንዲያገለግሉ ይደረጋል።” #ዳን. 1፥1-7፤ 2ነገ. 24፥10-16፤ 2ዜ.መ. 36፥10።
8ንጉሥ ሕዝቅያስ በተለይ በእርሱ ዘመን፥ በሰላም የመኖር ዋስትና እንዳለ ስለ ተረዳ “ከእግዚአብሔር ተልከህ የነገርከኝ ቃል መልካም ነው” አለ።
Currently Selected:
ትንቢተ ኢሳይያስ 39: አማ05
Highlight
Share
Copy
Want to have your highlights saved across all your devices? Sign up or sign in
© The Bible Society of Ethiopia, 2005
© የኢትዮጵያ መጽሐፍ ቅዱስ ማኅበር፥ 1997