ትንቢተ ኢሳይያስ 34
34
እግዚአብሔር በሕዝቦች ላይ እንደሚፈርድ
1እናንተ ሕዝቦች ቀርባችሁ አድምጡ! እናንተም ወገኖች ልብ በሉ፤ ምድርና በእርስዋ ያሉ፥ ዓለምና ከእርስዋም የተገኙ ሁሉ ይስሙ። 2እግዚአብሔር በሕዝቦች ሁሉ ላይ ተቈጥቶአል፤ ኀይለኛ ቊጣውም በሠራዊቶቻቸው ሁሉ ላይ ነው፤ ፈጽሞ ያጠፋዋል፤ በሰይፍም እንዲገደሉ አሳልፎ ይሰጣቸዋል። 3ሬሳቸው የትም ተጥሎ ይበሰብሳል እንጂ አይቀበርም፤ ተራራዎችም በደማቸው ይጥለቀለቃሉ። 4ፀሐይ፥ ጨረቃና ከዋክብት ሁሉ ይጠፋሉ፤ ሰማይም እንደ ብራና ተጠቅሎ ይወገዳል፤ ከዋክብትም እንደ ወይንና እንደ በለስ ዛፍ ቅጠል ይረግፋሉ።
5የእግዚአብሔር ሰይፍ በሰማያት ያቀደውን ካደረገ በኋላ ጥፋትን በወሰነበት በኤዶም ሕዝብ ላይ ለመፍረድ ይወርዳል። #ኢሳ. 63፥1-6፤ ኤር. 49፥7-22፤ ሕዝ. 25፥12-14፤ 35፥1-15፤ አሞጽ 1፥11-12፤ ሚል. 1፥2-5። 6ለመሥዋዕት የቀረቡ የበግና የፍየል ጠቦቶች በሚሠዉበት ጊዜ ደማቸውና ስባቸው ሰይፉን እንደሚሸፍን የእርሱም ሰይፍ በኤዶማውያን ደምና ስብ ይሸፈናል፤ እግዚአብሔር ይህን መሥዋዕት በቦጽራ ከተማ፥ ይህንንም ታላቅ ዕርድ በኤዶም ምድር ያቀርባል። 7የኤዶም ሕዝብ እንደ ጐሽ፥ እንደ ኰርማና እንደ ወይፈን ይወድቃሉ፤ ነገር ግን ከሌሎች ጋር አብረው ይሞታሉ፤ ሀገሪቱም በደማቸው ትነከራለች፤ ምድሪቱም በስባቸው ትዳብራለች። 8እግዚአብሔር ለጽዮን ለመከላከልና የበቀል እርምጃ ለመውሰድ የሚመጣበትን ዓመትና ቀን ወስኖአል።
9የኤዶም ጅረቶች ወደ ቅጥራንነት፥ ዐፈሩም ወደ ዲንነት ይለወጣሉ፤ ከዚያም ሀገሪቱ በመላ ትቃጠላለች። 10ቀንና ሌሊት ትቃጠላለች፤ ጢስም ከእርስዋ መውጣቱን ለዘለዓለም አያቋርጥም፤ ምድሪቱም በዘመናት ሁሉ የማትጠቅም ባድማ ትሆናለች፤ ዳግመኛ በእርስዋ ውስጥ አልፎ የሚሄድ አይኖርም። #ራዕ. 14፥11፤ 19፥3። 11ጭልፊትና ጃርት ይወርሱአታል፤ የጒጒትና የቊራም መጮኺያ ትሆናለች፤ በላይዋም የመፍረስዋ መለኪያ የሆነ ገመድና የባዶነትዋ መመዘኛ የሆነ ቱምቢ ይዘረጉባታል፤ 12አገሪቱንም የሚያስተዳድር ንጉሥ አይገኝም፤ መሪዎችም ሁሉ ይወገዳሉ። 13ቤተ መንግሥቶችዋና በቅጽር የተመሸጉ ከተሞችዋ ሁሉ እሾኽና ሳማ ይበቅልባቸዋል፤ የቀበሮና የሰጐን መኖሪያዎች ይሆናሉ። 14አነሮች ከጅቦች ጋር አብረው ይኖራሉ፤ አጋንንትም እርስ በርሳቸው ይጠራራሉ፤ የሌሊት ምትሐቶች በፍርስራሾች መካከል ይኖራሉ። 15በዚያም ጒጒቶች ጎጆ ሠርተው እንቊላል ይጥላሉ፤ እንቁላሎቻቸውንም ፈልፍለው በክንፎቻቸው ጥላ ሥር ይንከባከባሉ፤ አሞራዎችም ከጓደኞቻቸው ጋር በዚያ ይሰባሰባሉ።
16ስለ ሕያዋን ፍጥረት ሁሉ በእግዚአብሔር መጽሐፍ የተጻፈውን ፈልጋችሁ አንብቡ፤ ከእነዚህ ፍጥረቶች አንዱ እንኳ አይጠፋም፤ የኑሮ ጓደኛ አጥቶ ብቻውን የሚኖርም አይገኝም፤ እግዚአብሔር ራሱ ይህ እንዲሆን ስላዘዘ እርሱ ራሱ በኅብረት እንዲኖሩ ያደርጋቸዋል። 17እግዚአብሔር እያንዳንዳቸው የት መኖር እንደሚገባቸው ወሰነ፤ ከትውልድ ወደ ትውልድ እየተላለፈ ለዘለዓለም ይኖሩበታል።
Currently Selected:
ትንቢተ ኢሳይያስ 34: አማ05
Highlight
Share
Copy
Want to have your highlights saved across all your devices? Sign up or sign in
© The Bible Society of Ethiopia, 2005
© የኢትዮጵያ መጽሐፍ ቅዱስ ማኅበር፥ 1997