YouVersion Logo
Search Icon

ኦሪት ዘፍጥረት 38

38
ይሁዳና ትዕማር
1በዚያም ወራት ይሁዳ ከወንድሞቹ ተለይቶ ሒራ ወደሚሉት ዐዱላማዊ ሰው ዘንድ ሄዶ መኖሪያውን እዚያ አደረገ። 2እዚያም ይሁዳ የከነዓናዊውን የሹዓን ሴት ልጅ አየ፤ እርስዋንም አግብቶ ወደርስዋ ገባ። 3እርስዋም ፀንሳ ወንድ ልጅ ወለደችለት፤ ስሙንም ዔር ብላ ጠራችው። 4እንደገናም ፀነሰችና ወንድ ልጅ ወለደችለት፤ ስሙንም ኦናን ብላ ጠራችው፤ 5እንደገናም ወንድ ልጅ ወለደች ስሙንም ሴላ ብላ ጠራችው፤ እርሱንም የወለደችው ይሁዳ አክዚብ በሚባል ቦታ በሚኖርበት ጊዜ ነው።
6ይሁዳ የመጀመሪያ ልጁን ዔርን ትዕማር ከምትባል ልጃገረድ ጋር አጋባው። 7ዔር በእግዚአብሔር ፊት ክፉ ሰው ስለ ነበረ፥ እግዚአብሔር በሞት ቀሠፈው። 8ይሁዳ የዔርን ወንድም ኦናንን “ሂድና ወደ ወንድምህ ሚስት ገብተህ በደንቡ መሠረት ለወንድምህ መጠሪያ የሚሆን ዘር አስቀርለት” አለው። 9ኦናን የሚወለዱት ልጆች የእርሱ ያለመሆናቸውን በማወቁ ወደ ወንድሙ ሚስት ሲገባ ዘሩን ወደ ምድር ያፈሰው ነበር፤ በዚህ ዐይነት በወንድሙ ስም ልጆች እንዳይወለዱ አደረገ። 10ይህን በማድረጉ እግዚአብሔርን ስላሳዘነ እግዚአብሔር እርሱንም በሞት ቀሠፈው። 11ከዚህ በኋላ ይሁዳ ምራቱን ትዕማርን “ልጄ ሴላ እስከሚያድግበት ጊዜ ድረስ ሂጂና በአባትሽ ቤት መበለት ሆነሽ ኑሪ” አላት። ይህንንም ያለው እንደ ወንድሞቹ ይሞትብኛል ብሎ ስለ ሰጋ ነበር፤ ስለዚህ ትዕማር ሄዳ በአባቷ ቤት ተቀመጠች።
12በርከት ካሉ ዓመቶች በኋላ የሴዋ ልጅ የሆነችው የይሁዳ ሚስት ሞተች፤ ይሁዳ ከሐዘኑ ከተጽናና በኋላ ከወዳጁ ከዐዱላማዊው ከሒራ ጋር በጎቹን ወደሚሸልቱ ሰዎች ወደ ቲምና ሄደ። 13ሰዎቹም ለትዕማር “አማትሽ በጎቹን ለማሸለት ወደ ቲምና ይሄዳል” ብለው ነገሩአት። 14ስለዚህ ትዕማር የመበለትነት ልብሷን ለውጣ ፊቷን በሻሽ ሸፈነች፤ ወደ ቲምና በሚወስደው መንገድ ዳር በዔናይም ደጅ ተቀመጠች፤ ይህንንም ያደረገችው ሴላ አድጎ ሳለ ለእርሱ በሚስትነት እንድትሰጥ አለመፈቀዱን ስለ ተረዳች ነው።
15ፊቷን በሻሽ ሸፍና ስለ ነበር ይሁዳ ባያት ጊዜ አመንዝራ ሴት መሰለችው። 16ምራቱ እንደ ሆነች ሳያውቅ እርስዋ ወደተቀመጠችበት ወደ መንገድ ዳር ወጣ አለና “እባክሽ ወደ አንች እንድገባ ፍቀጂልኝ” ብሎ ጠየቃት።
እርስዋ “ፈቃድህን ብፈጽም ምን ትሰጠኛለህ?” አለችው።
17እርሱም “ከመንጋዎቼ መካከል አንድ የፍየል ጠቦት እልክልሻለሁ” አላት።
እርስዋም “እሺ እንግዲያውስ ጠቦቱን እስክትልክልኝ ድረስ መያዣ የሚሆን ነገር ስጠኝ” አለችው።
18እርሱም “ታዲያ፥ መያዣ የሚሆን ነገር ምን ልስጥሽ?” አላት።
እርስዋም “የማኅተም ቀለበትህን ከነማሰሪያውና ይህን የያዝከውን በትር ስጠኝ” አለችው።
ስለዚህ የጠየቀችውን ሁሉ ሰጣትና ወደ እርስዋ ገባ፤ እርስዋም ፀነሰችለት 19ከዚያ በኋላ ሻሽዋን ከፊቷ ላይ አንሥታ የመበለትነት ልብሷን እንደገና ለበሰች።
20ይሁዳ በመያዥያ መልክ የሰጣትን ነገሮች ለማስመለስ የፍየል ጠቦት በዐዱላማዊው ሰው እጅ ወደ ሴትዮዋ ላከ፤ ሰውየው ግን ሊያገኛት አልቻለም። 21ሰውየውም እዚያ የሚኖሩትን ሰዎች “በዔናይም ደጅ በመንገድ ዳር የነበረችው አመንዝራ ሴት ወዴት ሄደች?” ብሎ ጠየቀ።
ሰዎቹም “በዚህ አካባቢ እንደዚህ ያለች አመንዝራ ሴት የለችም” አሉት።
22ስለዚህ ሰውየው ወደ ይሁዳ ተመልሶ ሄደና “ላገኛት አልቻልኩም፤ በዚያ የሚኖሩትም ሰዎች ‘እንደዚህ ያለች አመንዝራ ሴት እዚህ የለችም’ አሉኝ” ብሎ ነገረው።
23ይሁዳም “እንግዲህ ጠቦቱን ልኬላት ነበር፤ ነገር ግን ልታገኛት አልቻልክም፤ ስለዚህ ሰዎች መሳቂያ እንዳያደርጉን የወሰደችውን መያዣ እዚያው ታስቀረው” አለ።
24በሦስተኛው ወር ገደማ ሰዎች “ምራትህ ትዕማር የዝሙት ሥራ ፈጸመች፤ ከዚህም የተነሣ ፀንሳለች” ብለው ለይሁዳ ነገሩት።
ይሁዳም “ወደ ውጪ አውጥታችሁ በእሳት አቃጥላችሁ ግደሉአት” አለ።
25እርስዋም ተይዛ ውጪ በምትወጣበት ጊዜ “እኔ የፀነስኩት የእነዚህ ዕቃዎች ባለቤት ከሆነ ሰው ነው፤ ይህን የማኅተም ቀለበት ከነማሰሪያውና ይህንንም በትር ተመልክተህ የማን እንደ ሆኑ ዕወቅ” ብላ ለዐማቷ ለይሁዳ ላከችለት።
26ይሁዳም ዕቃዎቹ የማን እንደ ሆኑ ዐውቆ “ከልጄ ከሴላ ጋር ስላላጋባኋት እርስዋ ከእኔ ይልቅ ትክክለኛ ሆና ተገኘች” አለ፤ ወደ እርስዋም ዳግመኛ አልገባም።
27የመውለጃዋ ቀን በተቃረበ ጊዜ በማሕፀንዋ ውስጥ መንታ ልጆች መኖራቸው ታወቀ። 28በምትወልድበትም ጊዜ ከመንትያዎቹ አንዱ እጁን አወጣ፤ አዋላጂቱም ሴት ቀይ ክር በእጁ ላይ አሰረችለትና “ይህ በመጀመሪያ ወጣ” አለች። 29ነገር ግን እጁን በመለሰው ጊዜ ወንድሙ ቀድሞት ተወለደ፤ አዋላጂቱም ሴት “እንዴት ጥሰህ ወጣህ!” አለች፤ ስለዚህ የመጀመሪያው ልጅ ስም “ፋሬስ” ተባለ። #38፥29 ፋሬስ፦ በዕብራይስጥ “ፋሬጽ” ሲሆን “ጣሰ” ማለት ነው። 30ከዚህ በኋላ በእጁ ላይ ቀይ ክር የነበረው ወንድሙ ተወለደ፤ ስሙም ዛራሕ ተባለ።

Highlight

Share

Copy

None

Want to have your highlights saved across all your devices? Sign up or sign in