YouVersion Logo
Search Icon

ወደ ገላትያ ሰዎች 5

5
በክርስቶስ የሚገኝ ነጻነት
1ክርስቶስ ነጻ ያወጣን በነጻነት እንድንኖር ነው። ስለዚህ ጸንታችሁ ቁሙ፤ እንደገናም በባርነት ቀንበር አትጠመዱ።
2እነሆ! እኔ ጳውሎስ የምላችሁ ይህ ነው፤ “መገረዝ ያስፈልገናል” ብላችሁ ብትገረዙ ክርስቶስ ምንም አይጠቅማችሁም፤ 3“መገረዝ ያስፈልገኛል” ብሎ የሚገረዝ ሁሉ “ሕግን በሙሉ የመፈጸም ግዴታ አለበት” ብዬ እንደገና አስጠነቅቀዋለሁ። 4እናንተ ሕግን በመጠበቅ ለመጽደቅ የምትፈልጉ ሁሉ ከክርስቶስ ተለይታችኋል፤ ከጸጋውም ርቃችኋል። 5እኛ ግን በእግዚአብሔር መንፈስ የጽድቅን ተስፋ በእምነት እንጠባበቃለን። 6በኢየሱስ ክርስቶስ ለሚኖር በፍቅር ላይ ተመሥርቶ የሚሠራ እምነት እንጂ መገረዝም ሆነ አለመገረዝ ምንም ጥቅም አይሰጠውም።
7ደኅና ትራመዱ ነበር፤ ታዲያ አሁን ለእውነት እንዳትታዘዙ የከለከላችሁ ማን ነው? 8እንዲህ ዐይነቱ ምክር ከጠራችሁ ከእግዚአብሔር የመጣ አይደለም። 9ይህም “ጥቂት እርሾ ሊጡን በሙሉ ያቦካዋል” እንደሚባለው ነው። #1ቆሮ. 5፥6። 10ነገር ግን ከዚህ የተለየ ሌላ ሐሳብ እንደማይኖራችሁ እርግጠኛ ሆኜ በጌታ እተማመናለሁ፤ ማንም ግራ የሚያጋባችሁ ቢኖር ቅጣቱን ይቀበላል።
11ወንድሞቼ ሆይ! እኔ እስከ አሁን የምሰብከው “ለመዳን መገረዝ ያስፈልጋል” እያልኩ ቢሆን ኖሮ እስከ አሁን ለምን ያሳድዱኝ ነበር? እንዲህ ቢሆን ኖሮ የክርስቶስ መስቀል ለሰዎች እንቅፋት መሆኑ ይቀር ነበር። 12እንግዲህ እነዚህ ግራ የሚያጋቡአችሁ ሰዎች ቢፈልጉ መገረዝ ብቻ ሳይሆን ራሳቸውን ጃንደረባ ቢያደርጉ እወድ ነበር።
13ወንድሞቼ ሆይ! እናንተ ለነጻነት ተጠርታችኋል፤ ነገር ግን አንዱ ሌላውን በፍቅር ያገልግል እንጂ ይህ ነጻነታችሁ የሥጋን ምኞት መፈጸሚያ ምክንያት አይሁን። 14ሕግ ሁሉ “ሰውን እንደ ራስህ አድርገህ ውደድ” በሚለው በአንድ ቃል ይፈጸማል። #ዘሌ. 19፥18። 15ነገር ግን እርስ በእርሳችሁ ብትነካከሱና ብትበላሉ እርስ በርሳችሁ እንዳትጠፋፉ ተጠንቀቁ።
መንፈሳዊና ሥጋዊ ሕይወት
16እንግዲህ በመንፈስ ተመርታችሁ ኑሩ፤ የሥጋንም ምኞት አትፈጽሙ እላለሁ። 17የሥጋ ምኞት ከመንፈስ ምኞት ጋር ይቃረናል፤ መንፈስና ሥጋ እርስ በእርሳቸው ይቃረናሉ፤ ስለዚህ እናንተ የምትፈልጉትን ማድረግ አትችሉም፤ #ሮም 7፥15-23። 18በመንፈስ ብትመሩ ግን የሕግ ተገዢዎች አትሆኑም።
19የሥጋ ሥራዎች የታወቁ ናቸው፤ እነርሱም ዝሙት፥ ርኲሰት፥ ስድነት 20ጣዖትን ማምለክ፥ ሟርት፥ ጠላትነት፥ ንትርክ፥ ቅናት፥ ቊጣ፥ ራስ ወዳድነት፥ መለያየት፥ አድመኛነት፥ 21ምቀኝነት፥ ስካር፥ ቅጥ ያጣ ፈንጠዝያ እነዚህን የመሳሰሉ ናቸው፤ ከዚህ በፊት እንዳስጠነቀቅኋችሁ አሁንም ደግሜ አስጠነቅቃችኋለሁ፤ እንደ እነዚህ ያሉትን ነገሮች የሚያደርጉ ሰዎች የእግዚአብሔርን መንግሥት አይወርሱም።
22የመንፈስ ቅዱስ ፍሬ ግን ፍቅር፥ ደስታ፥ ሰላም፥ ትዕግሥት፥ ደግነት፥ በጎነት፥ ታማኝነት፥ 23ገርነት፥ ራስን መግዛት ነው። እንደእነዚህ ያሉትን ነገሮች የሚቃረን ሕግ የለም፤ 24የኢየሱስ ክርስቶስ የሆኑት ሰዎች ሥጋን ከፍትወቱና ከምኞቱ ጋር ሰቅለውታል። 25በመንፈስ የምንኖር ከሆንን በመንፈስ እንመራ። 26አንዱ ሌላውን ለክፉ በማነሣሣት እርስ በእርሳችን እየተቀናናን በከንቱ አንመካ።

Highlight

Share

Copy

None

Want to have your highlights saved across all your devices? Sign up or sign in