YouVersion Logo
Search Icon

መጽሐፈ ዕዝራ 3

3
እግዚአብሔርን የማምለክ ሥነ ሥርዓት እንደገና መጀመሩ
1በሰባተኛው ወር እስራኤላውያን በሙሉ በከተሞቻቸው በመስፈር በአንድነት በኢየሩሳሌም ተሰበሰቡ፤ 2የኢዮጼዴቅ ልጅ ኢያሱም ከወገኖቹ ካህናትና የሰላትያል ልጅ ዘሩባቤልም ከዘመዶቹ ጋር በመተባበር የእስራኤልን አምላክ የእግዚአብሔርን መሠዊያ እንደገና ሠሩ፤ የእግዚአብሔር ሰው ለሆነው ለሙሴ በተሰጠው የሕግ መጽሐፍ በተጻፈውም መመሪያ መሠረት በዚያ መሠዊያ ላይ የሚቃጠል መሥዋዕት ለማቅረብ ቻሉ። #ዘፀ. 27፥1። 3የተመለሱት ምርኮኞች በምድሪቱ ከሚኖሩት አሕዛብ ተቃውሞ የተነሣ ፍርሀት ቢያድርባቸውም እንኳ መሠዊያውን በዚያው ቀድሞ በቆመበት ቦታ መልሰው ሠሩት፤ ከዚያም በኋላ የሚቃጠል መሥዋዕት ዘወትር ጠዋትና ማታ በዚያ ላይ እንደገና ማቅረብ ጀመሩ። #ዘኍ. 28፥1-8። 4ሕጉም በሚያዘው መሠረት የዳስ በዓልን አከበሩ፤ ለእያንዳንዱም ቀን የተመደበውን መሥዋዕት አቀረቡ፤ #ዘኍ. 29፥12-38። 5በተጨማሪም ዘወትር በሙሉ የሚቃጠለውን መሥዋዕት፥ በወር መባቻ በዓልና በሌሎችም የተቀደሱ የእግዚአብሔር በዓላት የሚቀርብ መሥዋዕትን በበጎ ፈቃድ ለእግዚአብሔር ከሚቀርበው ከሌላው መሥዋዕት ሁሉ ጋር አቀረቡ። #ዘኍ. 28፥11—29፥39። 6እነርሱ የቤተ መቅደሱን ሕንጻ እንደገና መሥራት ባይጀምሩም እንኳ ሰባተኛው ወር በገባ በመጀመሪያው ቀን ለእግዚአብሔር የሚቃጠል መሥዋዕት ማቅረባቸውን ጀመሩ።
የቤተ መቅደሱ ሕንጻ እንደገና መሠራት መጀመሩ
7እንዲሁም ሕዝቡ ለግንበኞችና ለአናጢዎች የሚከፈለውን ገንዘብ ሰጡ፤ ከሊባኖስ ዛፍ ቈርጠው በኢዮጴ የባሕር ጠረፍ በኩል እንዲልኩላቸው ለጢሮስና ለሲዶና ከተሞች ነዋሪዎች ምግብን፥ መጠጥንና የወይራ ዘይትን ላኩ፤ ይህም ሁሉ የሆነው የፋርስ ንጉሠ ነገሥት ቂሮስ በሰጣቸው ፈቃድ መሠረት ነበር። 8ስለዚህም በኢየሩሳሌም የእግዚአብሔር ቤተ መቅደስ ተሠርቶ ወደነበረበት ስፍራ በደረሱበት በሁለተኛው ዓመት፥ በሁለተኛው ወር፥ ዘሩባቤል፥ ኢያሱና ሌሎቹም የሀገራቸው ልጆች፥ ካህናቱና ሌዋውያኑ፥ ባጠቃላይም ወደ ኢየሩሳሌም ተመልሰው የመጡት ምርኮኞች ሥራውን ጀመሩ። ዕድሜአቸው ኻያ ዓመት ወይም ከዚያ በላይ የሆነ ሌዋውያን ሁሉ የቤተ መቅደሱ ሕንጻ ሥራ ኀላፊዎች ሆነው ተመደቡ። 9ሌዋዊው ኢያሱና ወንዶች ልጆቹ፥ እንዲሁም ዘመዶቹ፥ ቃድሚኤልና ከሖዳዊያ ቤተሰብ ወገን የሆኑ ወንዶች ልጆቹም ሁሉ በአንድነት ተባብረው ቤተ መቅደሱን እንደገና የመሥራቱን ኀላፊነት ተረከቡ፤ የሔናዳድ ዘሮች የሆኑት ሌዋውያንም ይረዱአቸው ነበር።
10ሠራተኞቹ የቤተ መቅደሱን መሠረት ማኖር በጀመሩበት ጊዜ ካህናቱ ልብሰ ተክህኖአቸውን ለብሰው በእጃቸው እምቢልታ በመያዝ የአሳፍ ቤተሰብ ተወላጆች የሆኑ ሌዋውያንም ጸናጽል ይዘው በረድፍ ቆመው ነበር፤ እነርሱም ከንጉሥ ዳዊት ዘመን ጀምሮ ተያይዞ በመጣው መመሪያ መሠረት በመዝሙር እግዚአብሔርን አመሰገኑ። #1ዜ.መ. 25፥1።
11“እግዚአብሔር ቸር ነውና፥
ለእስራኤል ያለውም ፍቅር ዘለዓለማዊ ነው”
የሚለውን መዝሙር በመቀባበል ለእግዚአብሔር ክብር ዘመሩት፤ የቤተ መቅደሱ መሠረት የማኖር ተግባር ስለ ተጀመረም እያንዳንዱ ሰው ድምፁን ከፍ አድርጎ እልል በማለት እግዚአብሔርን ያመሰግን ነበር። #1ዜ.መ. 16፥34፤ 2ዜ.መ. 5፥13፤ 7፥3፤ መዝ. 100፥5፤ 106፥1፤ 118፥1፤ 136፥1፤ ኤር. 33፥11። 12ከሽማግሌዎቹ ካህናትና ሌዋውያን ብዙዎቹ እንዲሁም የጐሣ መሪዎች የቀድሞውን ቤተ መቅደስ አሠራር በዐይናቸው አይተው ስለ ነበር የዚህኛውን ቤተ መቅደስ መሠረት ሲጣል ባዩ ጊዜ ድምፃቸውን ከፍ አድርገው አለቀሱ፤ በዚያ የነበሩት የሌሎቹ እልልታ ግን አስተጋባ። 13የሚያሰሙት ከፍተኛ ድምፅ በስፋት እስከ ሩቅ ያስተጋባ ስለ ነበር ማንም ሰው የደስታውን እልልታና የለቅሶውን ጩኸት ድምፅ ለመለየት አልተቻለውም።

Highlight

Share

Copy

None

Want to have your highlights saved across all your devices? Sign up or sign in